ክርስቲያኖ ሮናልዶ በዓለም ዋንጫው ላይ አዲስ ታሪክ ጻፈ

ፖርቹጋል በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ ጋናን 3 ለ 2 ስታሰንፍ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በአምስት የዓለም ዋንጫዎች ጎል በማስቆጠር የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኗል።
አጥቂው ከማንቸስተር ዩናይትድ በስምምነት እንዲለቅ ካደረገው አነጋጋሪ ቃለ መጠይቅ በኋላ ሲጫወት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
የ37 ዓመቱ ተጫዋች ጎሏን ያስቆጠረው በፍጹም ቅጣት ምት ነው።
የፖርቹጋሉ አጥቂ ቀደም ብሎ ያገኛቸውን ሁለት ዕድሎች ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል።
ጋና ጎሉ ከተቆጠረባት በኋላ ባሳየችው መነሳሳት በአንድሬ አዬው ማካይነት አቻ ለመሆን በቅታለች።
ጆአኦ ፌሊክስ እና ራፋኤል ሊአኦ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ፖርቹጋል 3 ለ 1 ለመምራት ችላለች።
ኦስማን ቡካሪ ለጋና ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ቻለ።
አፍሪካዊቷ ሃገር ባለቀ ሰዓት አቻ ለመሆን ያደረገችው ከፍተኛ ጥረት አልተሳካም።
በምድቡ የሚገኙት ኡራጓይ እና ደቡብ ኮሪያ ያለምንም ጎል አቻ ተለያይተዋል።
በኤጁኬሽን ስታዲም በተደረገው ጨዋታ ደቡብ ኮሪያዎች የተሻለ ቢንቀሳቀሱም የጎል ዕድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።
ትላንት የተደረጉት ጨዋታዎች የተጀመሩት ስዊዘርላንድ እና ካሜሩን ባደረጉት የምድብ ሰባት ፍልሚያ ነው።
ስዊዘርላንድ ጨዋታውን 1 ለ 0 ማሸነፍ ችላለች።
ብሪል ኤምቦሎ ብቸኛዋን ጎል ከመረብ ያሳረፈ ተጫዋች ሆኗል።
ካሜሩን ተወልዶ ለስዊዘርላንድ የሚጫወተው አጥቂ ጎሉን ካስቆጠረ በኋላ ደስታውን ከመግለጽ ተቆጥቧል።
የማይበገሩት አንበሶች ካሳዩት እንቅስቃሴ አንጻር ተሸንፈው መውጣት አልነበረባቸውም ተብሏል።
በሌላ የምድብ ሰባት ጨዋታ ለዋንጫው ትልቅ ግምት የተሰጣት ብራዚል ሰርቢያን 2 ለ 0 ማሸነፍ ችላለች።
ጥንቃቄ የተሞላበትን የሰርቢያን አጨዋወት ሰብሮ ለመግባት ብራዚሎች 62 ደቂቃ ለመጠበቅ ተገደዋል።
ሪቻርልሰን ደግሞ ጎሏን ያስቆጠረው ተጫዋች ነው።
ከደቂቃዎች በኋላ ቄንጠኛ ጎል ከመረብ አሳርፎ ቡድኑን ለአሸናፊነት አብቅቷል።
አሌክስ ሳንድሮ እና ካሰሚሮ በጎሉ ብረት የተመለሰባቸውን ጨምሮ ብራዚሎች በርካታ ዕድሎችን አምክነዋል።
ኔይማር ተግድቶ የወጣ ሲሆን ብራዚሎች የህክምና ውጤቱን በተስፋ እየጠበቁ ነው።
የዓለም ዋንጫው ቀጣይ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይካሄዳሉ።
በምድብ ሁለት የሚገኙት ዌልስ እና ኢራን ቀን ሰባት ሰዓት በአህመድ ቢን አኪ ስታዲየም ይገናኛሉ።
ኢራን በእንግሊዝ ተሸንፋ ዌልስ ደግሞ ከአሜሪካ አቻ ተለያይታ ነው የሚገናኙት።
አዘጋጇን ኳታርን እና ሴኔጋልን የሚያገናኘው ጨዋታ ቀን 10 ሰዓጥ ይከናወናል።
ሁለቱም ቡድኖች የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በመሸነፋቸው ዛሬ የሚሸነፈው ቡድን ከምድቡ እንደማያልፍ ያረጋግጣል።
ኔዘርላንድ እና ኢኳዶር ደግሞ ምሽት አንድ ሰዓት ይገናኛሉ።
ሦስት ሦስት ነጥብ ስላላቸው የሁለቱ አሸናፊ በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፉ መግባቱን ያረጋግጣል።
በዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ እንግሊዝ እና አሜሪካ ይጫወታሉ፥
እንግሊዝ ሦስት አሜሪካ ደግሞ አንድ ነጥብ ይዘው ነው ሁለተኛ ጨዋታቸውን የሚያከናውኑት።












