የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ትግራይ በረራ ለመጀመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ

የኢትዮጵያ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, ethiopian/fb

በጦርነት ሳቢያ ተቋርጠው የቆየውን ወደ ትግራይ የሚደርገውን በረራ መልሶ ለመጀመር የሚያስችለውን ሙሉ ዝግጅት ማጠናቀቁን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለቢቢሲ ገለጸ።

ከሁለት ዓመታት በፊት በትግራይ ጦርነት ሲቀሰቀስ ለአጭር ጊዜ ተቋርጦ የነበረው በረራ የፌደራል መንግሥቱ ክልሉን ከተቋጣጠረ በኋላ መልሶ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ የመንግሥት ሠራዊት ትግራይን ለቆ ሲወጣ መልሶ የኢትዮጵያ አየር መንግድ በረራ ተቋርጦ መቆየቱ ይታወሳል።

በቅርቡ በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ አየር መንገዱ የንግድ በረራዎችን መልሶ ለመጀመር ሙሉ ዝግጀቱን እንዳጠናቀቀ የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ለማ ያደቻ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ኃላፊው በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ እና በኬንያ ናይሮቢ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ “በመሬት ላይ ያለው ሁኔታ መሻሻል ስላሳየ” የኢትዮጵያ አየር መንገድ በክልሉ ሥራውን የሚያከናውነበት “ሁኔታ እየተስተካከለ መምጣቱን” ጠቅሰው በረራዎችን ለመጀመር የፀጥታ አካላትና የሲቪል አቪዬሽንን የመጨረሻ ፍቃድ እየተጠበቀ ነው ብለዋል።

እየተካሄደ በነበረው ጦርነት ምክንያት ከአንድ ዓመት በላይ ወደ ትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች የሚደረጉ በረራዎች ተቋርጠው ቆይተዋል።

አቶ ለማ እንዳሉት ከሰላም ስምምነቱ በኋላ አየር መንገዱ በክልሉ ያሉ አየር ማረፊያዎች በረራዎችን ለማስናገድ ያላቸውን ዝግጁነት የሚቃኙ ሠራተኞችን ወደ ትግራይ ክልል ማሰማራቱን ገልጸዋል።

በዚህም በክልሉ ያሉ የአውሮፕላን ማረፊያዎች መንደርደሪያዎች እና መቆሚያዎችን ደኅንነት እንዲሁም የመገናኛ መሳሪያዎችን ሁኔታ መቃኘትን ጨምሮ ለበረራ የሚያስፈልጉ አጠቃላይ የደኅንነት ሁኔታ መኖሩን ምልከታ እያደረጉ ነው ብለዋል።

“ከሞላ ጎደል አሁን ያለው ሁኔታ በረራ ሊያስጀምር የሚችል ነው...የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሁሉም መልኩ ዝግጁ ሆኖ እየጠበቀ ነው” ሲሉም አክለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በረራው የሚጀመረው የፀጥታ አላት እና የሲቪል አቪዬሽን በሚሰጡት “ይጀመር” የሚል ፍቃድ ላይ የሚመረኮዝ እንደሆነ ያነሱት ኃላፊው “ከመንግሥትም ጋር በቅርበት እየሰራን ነው። በማንኛውም ቀን ልንጀምር እንችላለን። ነገ ሊሆን ይችላል ከነገ ወዲያ፣ በማንኛውም ሰዓት ‘ጀምሩ’ ስንባል እንጀምራለን” በማለት አየር መንገዱ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም አየር መንግዱ በሽሬ አየር ማረፊያ ያሉትን የእርዳታ በረራዎችን እየተከታተለ ነው ብለዋል።

የአክሱም አየር ማረፊያ ግን ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት አሁን ላይ ሥራ ለመጀመር ዝግጁ እንዳልሆነም የንግድ ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አመልክተዋል።

ከጦርነቱ በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ትግራይ የሚያደርገው በረራ ብዛት ከአገር ውስጥ ከሚደረጉት ቀዳሚው የነበረ ሲሆን፣ ወደ መቀለ በቀን ከ10 እስከ 14 በረራዎች ይደረጉ እንደነበር አቶ ለማ ጠቅሰዋል። ወደ ታራካዊቷ የአክሱም ከተማም በቀን እስከ ሁለት በረራዎች እንዲሁም ወደ በሽረ ደግሞ አንድ በረራ ይደረግ ነበር።

ጦርነቱ ምክንያት የቱሪስቶች ፍስት መስተጓጎሉ እና ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ሲደረግ የነበረው በረራ ተቋርጦ መቆየቱ አየር መንገዱ ላይ ተጽእኖ መፈጠሩንም ኃላፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“የትግራይ ወንደሞቻችን ወደዚህ ይመጣሉ። እኛም ቤተሰቦቻችንን ለመጠየቅ ወደ እዚያ እንሄዳለን። [የበረራው መጀመር] አንደኛ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ያሳልጣል። ሁለተኛ እንደ አገር የቱሪዝሙን መስክ ያነቃቃወል።

“የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል ታሪካዊ የጉዞ መስመር ስለሆነ...የበረራዎች መጀመር የቱሪስት ፍሰትን ይጨምራል። በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቂ ገቢ ያገኛል። ኢትዮጵያም እንደ አገር ተገቢውን ጥቅም ታገኛለች” ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ20 በላይ የአገር ውስጥ የበረራ መዳረሻዎች ያሉት ሲሆን፣ በትግራይ ውስጥም ዋና ከተማዋን መቀለን ጨምሮ ወደ በርካታ ቦታዎች በየዕለቱ በረራ ሲያደርግ ቆይቷል።

ለሁለት ዓመት ሲካሄድ የነበረውን ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ለማብቃት በተደረሰው ስምምነት ውስጥ ተቋርጠው የቆዩ መሠረታዊ አገልግሎቶች በአስቸኳይ ሥራ እንዲጀምሩ ማድረግ አንዱ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም ወደ ትግራይ የአየር ትራንስፖርትን መልሶ ለመጀመር ያደረገው ዝግጅት ከዚሁ ጋር የሚያያዝ ነው።