ኳታር ወጪያቸውን ሸፍና ከተለያዩ አገራት ከጋበዘቻቸው ደጋፊዎች ምን ትጠብቃለች?

የብራዚል ቡድን ደጋፊዎች በዶሃ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የብራዚል ቡድን ደጋፊዎች በዶሃ

በኳታሩ የዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ በአል ባይት ስታዲየም ውስጥ በርካታ ወንበሮች ክፍት ሆነው መታየታቸውንና የተከፈላቸው ናቸው የተባሉ “ሐሳዊ” የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች የዋና ከተማዋ የዶሃ ጎዳናዎችን ሞልተው መታየታቸው መነጋገሪያ ሆኗል።

ቢቢሲ እነዚህ የተከፈላቸው ናቸው የተባሉት ሐሰተኛ ደጋፊዎችን ጉዳይ ለማጣራት ባደረገው ምርመራ ወቅት ኳታር በዓለም ዋንጫ አማካይነት ገጽታዋን የበለጠ ለማጉላት እያደረገችው ያለውን ጥረት ለመረዳት ችሏል።

በዚህም ኳታር ከበርካታ አገራት ጎልተው ለሚታዩ የእግር ኳስ ደጋፊዎች ነጻ የአየር ቲኬት እና የሆቴል ቆይታ ወጫቸውን በመሸፈን ወደ አገሯ እንዲገቡ ጋብዛለች።

እንደሚባለውም በምላሹም እነዚህ ተጋባዦች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ስለውድድሩ አውንታዊ መረጃዎችን እንዲያጋሩ እንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ መረጃዎችን ላይክ እና ሼር እንዲያደርጉ ይጠበቃል።

የመክፈቻው ሥነ ሥርዓት እና የመጀመሪያው ጨዋታ ከመደረጉ ቀደም ብሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች የዓለም አገራትን ሰንደቅ ዓላማዎችን እያውለበለቡ እና እየዘመሩ በዶሃ ጎዳናዎች ላይ ታይተው ነበር።

በፊፋ የዓለም ዋንጫ ይፋዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጽ ላይ በወጣ ቪዲዮ ላይ አንዳንድ ሰዎች የሚታዩት አብዛኞቹ ደጋፊዎች ከመካከለኛው ምሥራቅና ከደቡብ እስያ የሚመስሉ ሆነው ሳለ፣ ድጋፋቸውን የሚሰጡት ግን ከዓለም ዙሪያ ለመጡ የተለያዩ ቡድኖች እንዴት ሊሆን ቻለ የሚል ጥያቄ አንስተው ነበር።

በዚህም ሳቢያ አንዳንዶች እነዚህ ደጋፊዎች የእውነት ሳይሆኑ ተከፍሏቸው የሚሳተፉ ይሆን እንዴ? የሚል ጥያቄን አንስተዋል።

የደጋፊዎች ፕሮግራም

ቤተሰቦቹ ከሕንድ የሆኑት አሮን ፈርናንዴዝ የተባለው የኳታር ነዋሪ እንዲህ አይነቶቹ አስተያየቶች የአካባቢውን አገራት ተጨባጭ ሁኔታ ካለመረዳት የመነጨ ነው ይላል።

ይህንንም ሲያስረዳ በርካታ ሰዎች ከተለያዩ አገራት መጥተው ኳታርን እንደ አገራቸው በመቁጠር የሚኖሩ በስደት ስለሚኖሩ የተለያዩ ቡድኖችን ቢደግፉ ብዙም የሚያጠያይቅ ነገር ሊሆን አይገባም ይላል።

ምንም እንኳን በደቡብ እስያ ያሉ አገራት ዜጎች ለክሪኬት ስፖርት ባላቸው ፍቅር ቢታወቁም፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ደግሞ እግር ኳስን በጣም ይወዳሉ።

ለዚህም ማሳያ ሕንድን የመሰሉ አገራት በዓለም ዋንጫ ተሳትፈው ባያውቁም በርካቶች ሌሎች የሚወዷቸውን ቡድኖች ለመደገፍና ጨዋታዎችን ለመመልከት ይጓዛሉ።

አሮን እራሱ የሁለት ክለቦች የደጋፊዎች አባል ሲሆን፣ በፊፋ የደጋፊዎች እንቅስቃሴ እና በኳታር የደጋፊዎች ፕሮግራም ውስጥ ይሳተፋል። እነዚህ ቡድኖች በፊፋ እና በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴ አማካይነት የተቋቋሙ ናቸው።

አሮን በፊፋ የደጋፊዎች ፕሮግራም ውስጥ ለመሳተፍ ስምምነት ፈርሞ እንደሆነ በተጠየቀበት ጊዜም “በእንዲህ ያለ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ ሲኮን ኃላፊነቶች የማይቀሩ ናቸው፣ ነገር ግን ሁሉም ነገር ከስፖርት ጋር የተያያዘ ነው። ይህም ለዓመታት ሲደረግ የነበረ በመሆኑ እንደ ትልቅ ነገር መታየት የለበትም” ብሏል።

የኳታር የዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኳታር የዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት

ነጻ የአየር ትኬት እና ሆቴል

ምንም እንኳን አሮን ግልጽ ያለ መልስ ባይሰጥም በደጋፊዎች ፕሮግራም ውስጥ የሚሳተፉ አባላት ስምምነት የሚፈርሙ ሲሆን፣ ከውድድሩ አዘጋጆች ጥቅማ ጥቅሞችን እንደሚያገኙ ቢቢሲ መረጃ አግኝቷል።

ቢቢሲ የተመለከታቸው ሰነዶች እና ከበርካታ የውድድሩ አዘጋጅ ባለሥልጣናት ማረጋገጥ እንደተቻለው በርካታ የውጭ አገር ደጋፊዎች ወደ ኳታር ለመጓዝ ነጻ የአውሮፕላን ትኬት እና የሆቴል ወጪያቸው ተሸፍኗል። ይህም “ደጋፊዎች የሚኖራቸውን ቆይታ አመቺ ለማድረግ” በሚል በአዘጋጆቹ የተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

በምላሹም ደጋፊዎች “ተገቢ የሆኑ የውድድሩ ዝግጅት የበላይ ኮሚቴው የሚያሰናዳቸውን ይዘቶች በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው ላይ ለማውጣት” እና የሌሎችን ይዘቶችን ላይክ እና ሼር ለማድረግ የሚስማሙበትን ሰነድ እንዲፈርሙ ይደረጋል።

የበላይ ኮሚቴ የሚባለው በኳታር እየተካሄደ ያለውን የዘንድሮውን የፊፋ የዓለም ዋንጫ የሚያስተናግደው ኮሚቴ ነው።

ነገር ግን የተጋበዙት ደጋፊዎች “የበላይ ኮሚቴውን ወይም የፊፋ 2022 የኳታር የዓለም ዋንጫን የሚያሳጡ ድርጊቶችን እንዳይፈጽሙ” የሚስማሙ ሲሆን፣ “የኳታር አፈ ቀላጤ” መሆን እንደማይጠበቅባቸው ግን ተነግሯቸዋል።

የቤልጂየም እግር ኳስ ማኅበር የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያ የሆነው ፒየር ኮርኔዝ እንዳለው፣ በተጨማሪም ለደጋፊዎች “አንድ ነጻ ቲኬት እና በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲገኙ ተደርጓል።”

ጨምሮም ይህ ስጦታ የተበረከተው ለቤልጂየም የእግር ኳስ ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን “በዓለም ዋንጫው ላይ ለሚወዳደሩ ለሁሉም አገራት ነው” መሆኑን ገልጿል።

እንዲሁም በዚህ ሁኔታ ግብዣው የተደረገላቸው ሁሉም ተሳታፊዎች ስምምነቱን እንዲፈርሙ አለመደረጉንም ተናግሯል።

የአርጀንቲና ደጋፊዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአርጀንቲና ደጋፊዎች

“እንግዶቻችን ናቸው”

የዓለም ዋንጫ አስተናጋጅነት ለኳታር መሰጠቱን በተመለከተ አገሪቱ ባላት ዝቅተኛ የውጭ አገር ሠራተኞች አያያዝ፣ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን ላይ ባላት አቋም እና ከመናገር ነጻነት ጋር ተያይዞ ትችት ሲቀርብባት ነበረ።

በዚህም ኳታር የተሰነዘሩባትን ወቀሳዎች ወደ ጎን በማድረግ የውድድሩን ገጽታ የበለጠ ያማረ ለማድረግ ያደረገችው ሙከራ መሆኑን አንዳንዶች ይናገራሉ።

የአውሮፓ ደጋፊዎች የቦርድ አባል የሆነችው ማርታ የንስ እንደምትለው፣ እንዲህ አይነት ነገር ከዚህ በፊት በተካሄዱ ታላላቅ ውድድሮች ላይ ስለመደረጋቸው ፈጽሞ ሰምታ አታወቅም።

“ይህ የደጋፊዎች እንቅስቃሴ ሳይሆን፣ የደጋፊዎች ማጭበርበር ነው” በማለት “ይህ እንግዳ ነገር ነው፤ ትክክልም አይደለም” ብላለች።

ነገር ግን የውድድሩ አዘጋጅ አካል የሆነው የበላይ ኮሚቴ ግን “ይህ ግብዣ በ59 የተለያዩ አገራት ውስጥ ያሉ ደጋፊዎችን ፍላጎትና ጥያቄዎችን ለመረዳት አስችሎናል” በማለት ምላሽ ሰጥቷል።

ጨምሮም “ደጋፊዎቹ የተለያዩ ይዘቶችን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ለማውጣት እና ለማጋራት በምንም አይነት አስገዳጅ ውል ውስጥ አይደሉም።

“ኳታርን የሚጎበኙት ሁሉም ደጋፊዎች እንደ እንግዶቻችን ስለምንመለከታቸው ምንም ሳይከፈላቸው በራሳቸው ፈቃድ የሚያደርጉት ነው የሚሆነው” ሲል ተጋባዦች ግዴታ እንደሌለባቸው አስተባብሏል።