የኳታሩ የዓለም ዋንጫ ከቀደሙት በተለየ ለምን በርካታ ውዝግቦች አጋጠሙት?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሚቀጥለው ሳምንት ከሚጀመረውን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ጋር በተያያዘ ፊፋ እና አዘጋጇ ኳታር እንዳይነሱ ከሚፈልጓቸው ርዕሶች መካከል አንዱ ወደ መድረክ ብቅ ብሏል።
ውድድሩ ሊጀመር ቀናት ብቻ ይቀሩታል። ውድድሩ ኦፊሴላዊ አምባሳደር የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን ጉዳይ “አዕምሮ ውስጥ የተፈጠረ ችግር ነው” ብለውታል።
ካሊድ ሳልማን የኳታር ብሔራዊ ቡድን እግር ኳስ ተጫዋች ናቸው። ዜድዲኤፍ ለተሰኘው የጀርመን መገናኛ ብዙኃን ነው ይህንን የተናገሩት። የሠራተኞች መብት፣ የመናገር ነጻነት እና የዩክሬን ጦርነት ሌሎቹ መነጋጋሪያ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው።
የውዝግቡ መቀጣጠል አንዳንዶች የኳታሩን የዓለም ዋንጫ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ጥላ ያጠላበት የዓለም ዋንጫ ውድድር ነው እንዲሉ አስገድዷቸዋል።
የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ጉዳይ
የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ እና ሃሳቡን ማቀንቀን በኳታር ወንጀል ነው። ከእስራት እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣትም ያስከትላል።
“ለስደተኛ ሠራተኞች ካደረጉት መሻሻል በኋላ በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን ላይም መሻሻል ያደርጋሉ የሚል ተስፋ ነበርኝ” ሲል ፖል አማን የተባለው የሊቨርፑል የተመሳሳይ ጾታ ደገፊዎች መስራች ይገልጻል።
እአአ በ2019 ከባለቤቱ ጋር ኳታርን እንዲጎበኝ በዓለም ዋንጫ አዘጋጆቹ ተጋብዞ ነበር።
አገሪቱን ለመጎብኘትም ሆነ የዓለም ዋንጫውን ለመከታተል ባለሥልጣናት ግን “ሁሉንም እንኳን ደህና መጣችሁ እንላለን” ብለዋል።
የካሊድ ሳልማን ዓይነቱ ቃለ መጠይቅ ግን ፖል ስለ ውድድሩ የነበረውን አዎንታዊ እይታ የሚያደበዝዝ ነው።
በተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ውስጥ ያሉትን ማሰር እና ይህንን የመቀየር ህክምና መደረጉ ፖል የዓለም ዋንጫውን ለመመልከት ለመሄድ እንዳያስብ ምክንያት ሆኖታል።
“ባለሥልጣናት የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያንን የሚይዙበት መንገድ መጥፎ በመሆኑ ይህንን መቀበል የማይታሰብ ነው” ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተጫዋቾች ተቃውሞ
በኳታር ላይ ከዓለም አቀፍ ፖለቲከኞች እና የመብት ተሟጋቾች ከሚነሳው ትችት ባለፈ ቅሬታዎች ከሜዳ ውስጥም እየተደመጡ ናቸው።
ዴንማርክ ቡድኗ በውድድሩ ላይ ሲሳተፍ በማሊያ ላይ ያለው የአገሪቱ እና የአምራቹ አርማ በግልጽ እንዳይታይ አድርጋለሁ ብላለች።
የቡድኑን አምበል ጨምሮ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን እና የቤልጂም ተጫዋቾች ባለቀስተ ደመና አርማውን ምልክት በክንዳቸው ላይ ያጠልቃሉ።
ቡድኖች በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ውሳኔያቸው ፊፋ ፖለቲካዊ ሃሳቦችን በጨዋታዎች ወቅት ማስተላለፍ አይፈቀድም የሚለውን የዓለም ዋንጫ ደንብ ስለመጣሱ ምላሽ አልተሰጣቸውም።
ዓለም አቀፉ የአግር ኳስ አስተዳዳሪ ድንበሩን የት ማድረግ እንዳለበት የሚቸግረው ይመስላል፣ ሲሉ የዓለም አቀፉ የስፖርት ጠበቃ ዶ/ር ግሪጎሪ ሎንዲስ ይናገራሉ።
“የኖርዌይ ተጫዋቾች በቅርቡ ሃሳባቸውን ማልያቸው ላይ አስፍረዋል። ‘ይህ ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው ነው?’” ሲሉ ይጠይቃሉ።
“አላውቅም፣ የፖለቲካ መልዕክት ምን እንደሆነ ትነግሩኛላችሁ? ማንም ይህን አያስረዳኝም። ይህ ችግር ነው አሁን ፊፋን የገጠመው።”
ለፖል አማን ደግሞ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን ጉዳይ “መሠረታዊ ማኅበራዊ ጉዳይ እንጂ ፖለቲካዊ አይደለም” በዚህ ምክንያትም ተጫዋቾች ሊቀጡ አይገባም ባይ ነው።
ውድድሩ ሲጀመር ነው ተጫዋቾችም ሆኑ ደጋፊዎች ሕጉ እንዴት እንደሚፈጸም መጨረሻውን የሚያውቁት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሠራተኞች መብት
አንዳንዶች ደግሞ የውድድሩ ተሳታፊ ተጫዋቾች በኳታር የሚገኙ የኮንስትራክሽን ሠራተኞችን መብት ብቻ ቢያነሱ ያስደስታቸዋል።
“ለፊፋ ’ፖለቲካዊ በመሆኑ ቅጣት ይተላለፍባችኋል’ ማለት ስህተት ይመስለኛል” የሚለው ኢኩዊደም ተባለ የሰብዓዊ መብት እና የሠራተኞች መብት ምርመራ አማካሪን ያቋቋመው ሙስጠፋ ቃድሪ ነው።
ለዓለም ዋንጫው ዝግጁ የሆኑ ስታዲየሞችን የገነቡ ሠራተኞችን አነጋግረዋል። ሥራውን ለማግኘት ከመክፈል ባለፈ ደሞዝ የማግኘት እና በከፍተኛ አየር ሁኔታ መሥራት ዕጣ ፈንታቸው መሆኑን ይገልጻሉ።
እንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚገልጹት ከሆነ አገሪቱ የዓለም ዋንጫን የማስተናገድ ዕድሉን ካገኘችበት ከ2010 ወዲህ ስድስት ሺህ ሠራተኞች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
የኳታር መንግሥት ግን ይህንን አበክሮ ይሞግታል። ቁጥሩ አሳሳች ነው በማለት፣ በዓለም ዋንጫው ግንባታ ወቅት ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 37 ብቻ ነው ይላል።
ከእነዚህም መካከል “ከሥራ ጋር በተያያዘ” ሁኔታ የሞቱት ደግሞ ሦስት ብቻ ናቸው ሲል ያስቀምጣል።
በአገሪቱ “ካፋላ” የተባለ አሠራር አለ። በዚህ አሠራር መሠረት ሠራተኞች ሥራቸውን ለመልቀቅ ወይም ለመቀየር የስፖንሰራቸውን ፈቃድ ማግኘት አለባቸው። ይህ አሠራር በመቅረቱ መሻሻሎች አለ ይላሉ።
ሙስጠፋ ደግሞ አንዳንድ ለውጦች “የተወሰኑ ሠራተኞችን የጠቀሙ” ቢሆንም “ልውጦቹ የሚጠበቀውን ያህል አልተጓዙም” ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አወዛጋቢ አስተናጋጅ
የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን ጉዳይ እና የሠራተኞችን መብት በማንሳት ብዙዎች መጀመሪያም የአስተናጋጅነት ዕድል ለኳታር መሰጠት አልነበረበትም ይላሉ።
የአስተናጋጅነት መረጣ ሂደቱ በመልከ ብዙ ሙስና የታጀበ ነበር የሚል ተደጋጋሚ ክስ ሲቀርብ ቆይቷል። በዚህ ዙሪያ ስዊትዘርላንድ እና አሜሪካ ምርመራ የጀመሩት በ2015 ነበር።
ኳታር ግን ምንም ስህተት አልተሠራም ስትል ትከራከራለች። የአስተናጋጅነት መረጣው ሂደቱም ስህተት አልባ ተብሎ ከፊፋ ምርመራ በኋላ በ2017 ይሁንታን አግኝቷል።
የውሳኔው ደጋፊዎች ችግር አለባቸው የሚባሉ አገራትን በስፖርት በማሳተፍ እንዲለወጡ እና ግልጽ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል ይላሉ።
“ያለውን የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ይበልጥ ቢያጋልጥም በሚፈለገው ልክ ግን አልተሠራም” ሲል ሙስጠፋ በሌላ ወገን ይሞግታል።
ፊፋ ውድድሩን ከኳታር እንድታዘጋጅ ያደረገበት አንደኛው ምክንያት ለውጥን ፍለጋ ሊሆን ይችላል ሲሉ ዶ/ር ግሪጎሪ ይገልጻሉ።
“እነሱን የሚያካትት ከባቢ መፍጠር ይፈልጋሉ። ያቺን አገር ለዓለም ክፍት በማድረግ የግለሰብ ነፃነት እና የመሳሰሉትን እንድታስተካክል ማሳመን ይችላሉ።”
ነገር ግን በተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት እና በሠራተኞች መብት ላይ የቀጠለው ትችት ብዙዎች ፊፋ የተሳሳተ ውሳኔ እንዳደረገ እንዲያስቡ አድርጓቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያ መታገድ
ከዚህ ውድድር ጋር በተያያዘ ፊፋ በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆትን ያገኘበትን ውሳኔ አሳልፏል። ይህም ሩሲያን ከምድብ ማጣሪያው ለማባረር መወሰኑ ነው።
አገራት በሜዳ ላይ ሕግን በመጣስ ወይም በአስተዳደራዊ ቅጣት መታገዳቸው የተለመደ ነው። ነገር ግን ከኳስ ጋር ባልተያያዙ ጥፋት ቡድኑ መታገዱ ጉዳዩን ያልተለመደ ያደርገዋል።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጀርመን እና ጃፓን ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሟቸው ነበር። በአፓርታይድ ዘመን ደቡብ አፍሪካም እንዲሁ ማዕቀብ ተጥሎባት ነበር።
“ፊፋ የፖለቲካ ይዘቶችን ከስፖርቱ ለማራቅ እየሞከረ ነው። ነገር ግን ፊፋ በራሱም የፖለቲካ ድርጅት ነው” ሲሉ ዶ/ር ግሪጎሪስ ስለ ውሳኔው ተናግረዋል።
“ፊፋ የፖለቲካ ውሳኔዎችን ማሳለፉ የማይቀር ነው።”
ሩሲያን የማባረር እርምጃ የተወሰደው ከአገሪቱ ጋር ሊጫወቱ የነበሩት ፖላንድ፣ ቼክ ሪፐብሊክ እና ስዊዲን የዩክሬንን ወረራ በመቃወም ከሩሲያ ጋር ለመጫወት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው።
ፊፋ ካልወሰነ “ሌሎች ተሳታፊ አገራትም ተመሳሳይ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ የሚል ስጋት ተፈጥሯል” ሲሉ ዶ/ር ግሪጎር ጨምረው ገልጸዋል።

የተደረጉ ለውጦች
የኳታር አሚር ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ አገራቸው የዓለም ዋንጫን በማዘጋጀቷ የሚቀርበውን ትችት በመቃወም “ለአሥርት ዓመታት የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በመድሎ ሲሰቃዩ ቆይተዋል። ይህም መድልዎ በአብዛኛው የተመሠረተው እኛን በማያውቁ ሰዎች እና በአንዳንድ አጋጣሚዎች እኛን ለማወቅ ፈቃደኛ ባልሆኑት ነው” ብለዋል።
“በተለያዩ አህጉራት የሚገኙ ታላላቅ ስፖርታዊ ዝግጅቶች በሌሎች አገራት በተዘጋጁበት ወቅት ግለሰቦች ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት ጥቃት ይፈጽማሉ። እናም ኳታር ባደረገችው ልማት፣ ማሻሻያ እና መሻሻል ኩራት ይሰማኛል” ሲሉም ተናግረዋል።
ውድድሩ ሲቃረብ ተቃውሞው እና ውዝግቡ ከሜዳ ውስጥም ሆነ ከሜዳው ውጪ ሊቀጥል ይችላል። ይህ የዓለም ዋንጫ ከእግር ኳስ ውጪ ባሉ ምክንያቶች ርዕሰ ዜናዎችን መቆጣጠሩን የሚቀጥል ይመስላል።












