የቀድሞ የፊፋ ፕሬዝዳንት ኳታር የዓለም ዋንጫን እንድታዘጋጅ መፍቀዱ ስህተት ነው አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞ የፊፋ ፕሬዝዳንት ሴፍ ብላተር የ2022 የዓለም ዋንጫን ኳታር እንድታዘጋጅ መፍቀዱ “ስህተት” ነው አሉ።
ፊፋ የባህረ ሰላጤዋ አገር ውድድሩን እንድታዘጋጅ ፊፋ ሲመርጣት የ86 ዓመቱ ብላተር የተቋሙ ፕሬዝዳንት ነበሩ።
በወቅቱ የፊፋ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ 14 ለ 8 በሆነ ድምጽ ኳታር አሜሪካን በልጣ የዓለም ዋንጫውን እንድታዘጋጅ መርጧታል።
ኳታር ካላት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሪኮርድ በተደጋጋሚ ስትብጠለጠል ቆይታለች። የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት አለመፍቀዷ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና የሠራተኞች አያያዝ የሚያስወቅሷት ተጨማሪ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
ብላተር በወቅቱ ውድድሩ ወደ ኳታር ‘መሄድ የለበትም’ ማለታቸው ‘ትክክል’ እንደነበረ ተናግረዋል።
ብላተር ከስዊትዘርላንድ ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኳታር ትንሽ አገር በመሆኗ ዓለም ዋንጫን የሚያክል ትልቅ ዝግጅት “ለትንሿ አገር ይተልቅባታል” ብለዋል።
የዓለም ዋንጫ በ92 ዓመት ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በመካከለኛው ምሥራቅ ይካሄዳል።
ብላተር አሜሪካ ውድድሩን እንድታዘጋጅ ድምጽ መስጠታቸውን ገልጸው፤ ኳታር ውድድሩን ለማዘጋጀት እንድታሸንፍ ያስቻሉት የወቅቱ የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ፕሬዝዳንት ሚሼል ፕላቲኒን ተጠያቂ አድርገዋል።
“የፕላቲኒ እና የእርሱ ቡድን አባላት የሰጡት 4 ድምጽ የዓለም ዋንጫ ከአሜሪካ ይልቅ ወደ ኳታር እንዲሄድ አድርጓል” ብለዋል ብላተር።
ጨምረው እንደተናገሩት በኳታር የስታዲየም ግንባታዎች ላይ የተሳተፉ ሠራተኞ አያያዝን በተመለከተ ጥያቄዎች መነሳታቸውን ተከትሎ ፊፋ አዘጋጅ አገራትን የሚመርጥበትን መስፍርት ማሻሻሉን ጨምረው ተናግረዋል።
“ከዚያ በኋላ ማኅበራዊ ዕሴቶች እና የሰብዓዊ መብት አያያዝ ከግምት ገብተዋል” ብለዋል።
ብላተር ለ17 ዓመታት የፊፋ ፕሬዝዳንት የነበሩ ሲሆን እአአ 2015 ላይ ግን ለፕላቲኒ 2.19 ሚሊዮን ዶላር ሕጋዊ ባልሆነ መልኩ አስተላልፈዋል ተብለው ተገደው ሥልጣናቸውን አስረክበዋል።
ብላተር የተለያዩ የፊፋ የሥነ-ምግባር ሕጎችን ጥሰዋል ተብለው እስከ 2028 ከእግር ኳስ ታግደዋል።
ሩሲያ የ2018 እንዲሁም ኳታር የ2022 አዘጋጅነት የተሰጣቸው ትክክለኛ መንገድ ባልተከተለ መልኩ ነው የሚሉ ክሶች በስፋት ወጥተው የነበረ ሲሆን የስዊትዘርላንድ ዐቃቤ ሕግ እና የአሜሪካ ፍትሕ ቢሮ ጉዳዩን ሲመረምሩ ነበር።
ተመራጭ አገራቱ ኳታር እና ሩሲያ የውድድሩን አዘጋጅነት ለማግኘት ያጠፋነው ጥፋት የለም የሚሉ ሲሆን ፊፋ ባከናወነው ምርመራ ነጻ ተብለዋል።












