ሸዋ ሮቢት ከተማ የደኅንነት ማስጠንቀቂያ ካወጣች በኋላ ከንቲባዋ ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Shewa Robit City
በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ የምትገኘው የሸዋ ሮቢት ከተማ ለነዋሪዎቿ ፀጥታ እና ደኅንነት ጥብቅ መመሪያዎችን ማውጣቷን ተከትሎ ከንቲባዋ ተገደሉ።
የሸዋ ሮቢት ከተማ ሐሙስ ቀን የሰዓት እላፊ ገደብ እና ሌሎች መመሪያዎችን ካወጣች በኋላ ምሽት ላይ ተቀዳሚ ከንቲባዋ ባልታወቁ ሰዎች በተተኮሰባቸው ጥይት ተመትተው መገደላቸው ተነግሯል።
የሰሜን ሸዋ ዞን የሰላምና ደኅንነት ምክትል ኃላፊ አቶ ሰለሞን አልታዬ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ከንቲባው አቶ ውብሸት አያሌው ሐሙስ ነሐሴ 26/2014 ዓ.ም. ምሽት ሦስት ሰዓት ገደማ ነው ተተኩሶባቸው የተገደሉት።
ሟቹ ወጣት እና ታታሪ የሕዝብ አገልጋይ እንደነበሩ የተናገሩት አቶ ሰለሞን፣ ባልታወቁ ሰዎች ግድያው የተፈጸመባቸው ከሥራቸው ተመልሰው ወደ ቤታቸው ሲገቡ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
በአገሪቱ ከተከሰተው ወቅታዊ ሁኔታ ውጪ በከተማው ውስጥም ሆነ በከንቲባው ላይ ምንም አይነት የፀጥታ ስጋት እንዳልነበረ ያመለከቱት የዞኑ ምክትል የፀጥታ እና የደኅንነት ኃላፊ፣ ስለግድያው ምርመራ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የሸዋ ሮቢት ከተማ ከዚህ ቀደም በዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች በሚነሱ ግጭቶች አለመረጋጋት በተደጋጋሚ ያጋጠማት ሲሆን፣ በዚህ ዓመትም በኅዳር ወር ላይ የህወሓት ኃይሎች ተቆጣጥረዋት እንደነበር ይታወሳል።
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መልሶ ካገረሸ በኋላ በምሥራቅ አማራ ያሉት የሰሜን ወሎ፣ የደቡብ ወሎ እና የሰሜን ሸዋ አካባቢዎች የደኅንነት ጥበቃቸውን እያጠናከሩ ባሉበት ወቅት ነው ከንቲባው የተገደሉት።
ከንቲባው አቶ ውብሸት አያሌው ምሽት ላይ ከመገደላቸው በፊት ቀን ላይ የሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት የከተማዋን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ እና ሰርጎ ገቦችን ለመከላከል ያስችላሉ ያላቸውን ውሳኔዎች ለሕዝቡ ይፋ አድርጓል።
በዚህም በከተማ ውስጥ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ እስከ ምሽት ሁለት ሰዓት፣ የሰው እንቅስቃሴ ደግሞ እስከ ምሽት አምስት ሰዓት እና በከተማዋ ተጠልለው የሚገኙ የተፈናቀሉ ሰዎች እንቅስቃሴ እስከ ምሽቱ 12 ድረስ እንዲሆን መገደቡን አስታውቋል።
እንዲሁም ሆቴሎች እና መኝታ ቤቶች አስፈላጊውን መረጃ ለፖሊስ እንዲሰጡ በተጨማሪም ምግብ እና መጠጥ ቤቶች ለደንበኞቻቸው አገልግሎት መስጠት የሚችሉት እስከ አራት ሰዓት ድረስ እንዲሆን ገድቧል።
በተጨማሪም ከመንግሥት የፀጥታ አካላት ውጪ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንዲሁም ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ይዞ መገኘት በጥብቅ የተከለከለ ሲሆን፣ ከመንግሥት እውቅና ውጪ ስብሰባ ማድረግ መከልከሉንም ገልጿል።
በሸዋ ሮቢት ከተማ ከንቲባ ላይ የተፈጸመው ግድያ በከተማዋ ከተላለፈው ጥብቅ የደኅንነት ቁጥጥር ጋር የሚያያዝ አይደለም ያሉት የሰሜን ሸዋ ዞን የሰላምና ደኅንነት ምክትል ኃላፊ አቶ ሰለሞን አልታዬ፣ ከተማዋ አሁን በተለመደ እንቅስቃሴ ላይ መሆኗን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የከተማው ፖሊስ ከከንቲባው ግድያ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ስለመኖራቸው ያለው ነገር የለም። ነገር ግን ገዳዮቹን ለመያዝ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
ሟቹ የሸዋ ሮቢት ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ ውብሸት አያሌው በኃላፊነት ወደ ከተማዋ አስተዳደር ከመምጣታቸው በፊት በቀወት ወረዳ አስተዳደር ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች ላይ መሥራታቸውን የከንቲባው ጽህፈት ቤት አመልክቷል።
አቶ ውብሸት አያሌው ባለትዳር እና የአንድ ሴት እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት የነበሩ ሲሆን፣ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው አርብ ነሐሴ 26/2014 ዓ.ም እዚያው ሸዋ ሮቢት ከተማ መፈጸሙ ተነግነሯል።












