አራተኛ ዲግሪያቸውን እየሠሩ ያሉት የ85 ዓመቷ የዕድሜ ባለጸጋ

የእድሜ ባለጸጋዋ ሉሲል ቴሪ ክሬንስተር

የፎቶው ባለመብት, The Cotswold PR Company

የምስሉ መግለጫ, የእድሜ ባለጸጋዋ ሉሲል ቴሪ ክሬንስተር

ሉሲል ቴሪ ክሬንስተር ይሰኛሉ።

የዩናይትድ ኪንግደም ነዋሪዋ ሉሲል ዕድሜያቸው 85 ነው።

የዕድሜ አቻዎቻቸው ከዕድሜ ጋር በተያያዙ እክሎች አልጋ ላይ ሲውሉ ወይም በአረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከላት ባሉበት ወቅት እሳቸው ግን አራተኛ ዲግሪያቸውን እየሠሩ ነው።

“ዝም ብሎ መቀመጥ አልችልም” ይላሉ ሉሲል።

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የያዙት በፋርማሲ ትምህርት ከማንችስተር ዩኒቨርስቲ ነው።

ይህንንም ትምህርታቸውንም ያጠናቀቁት በአውሮፓውያኑ 1962 ነበር።

በአሁኑ ወቅት አራተኛ ዲግሪያቸውን ለመያዝ በኦፕን ዩኒቨርስቲ ትምህርት ጀምረዋል።

የሚያጠናቅቁትም በ90ዎቹ ዓመታቸው መጀመሪያ ላይ ይሆናል። ከዚሁ ዩኒቨርስቲ ቀደም ሲል ሦስት ዲግሪዎችን አግኝተዋል።

ለዚህ ትጋታቸውም በቤተክርስቲያናቸው በነበረ ሥነ ሥርዓት ላይ በቅርቡ ተሸልመዋል።

ለረጅም ዘመናት በመምህርነት ያገለገሉት የዕድሜ ባለጸጋዋ በአሁኑ ወቅት በሃይማኖት ጥናት፣ በፍልስፍና እና በሥነ ምግባር በዲግሪ ፕሮግራም ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።

በዩናይትድ ኪንግደም ሲዲንግተን ፓርክ ነዋሪ የሆኑት ሉሲል በሂውማኒቲስ፣ በሥነ ልቦና እና በሃይማኖታዊ ጥናቶች ዲግሪ አላቸው። በተጨማሪም የመምህርነት ሰርቲፊኬታቸውን በአውሮፓውያኑ 1972 ከማግኘታቸው በፊት የሳይንስ መሠረታዊ ኮርስ የተሰኘ ትምህርትም ተምረዋል።

ሉሲል ጡረታ ከወጡ በኋላ ቁጭ ብለው በአብዛኛው በዕድሜ የገፉ ሰዎች የሚያዘወትሩትን የክሮስወርድ ፐዝል [ቃላትን በማገጣጠም የሚደረገው ጨዋታ] መጫወት አልፈለጉም።

ሉሲል ቴሪ ክሬንስተር ከኦፕን ዩኒቨርስቲ የተላከላቸውን ደብዳቤ ይዘው

የፎቶው ባለመብት, The Cotswold PR Company

የምስሉ መግለጫ, የዕድሜ ባለጸጋዋ ሉሲል ቴሪ ክሬንስተር ከኦፕን ዩኒቨርስቲ የተላከላቸውን ደብዳቤ ይዘው
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“ምንም ሳልሠራ ዝም ብዬ መቀመጥ እና ሁልጊዜ ቴሌቪዥን መመልከት አልፈለግኩም” ይላሉ።

“ሴት ልጄ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ምን ማድረግ ትፈልጊያለሽ? ስትል ጠየቀችኝ፤ እኔም መማር፣ ማጥናት እወዳለሁ። በጣም የሚያስደስተኝ ነገር ነው። ለእኔ ምንም አስቸጋሪ አይደለም አልኳት” ይላሉ።

የዕድሜ ባለጸጋዋ አራተኛ ዲግሪያቸውን እየተማሩ ስለሆነ በርካቶች በጣም “የላቀ አዕምሮ እንዳላቸው” አድርገው ይቆጥሯቸዋል።

እሳቸው በዚህ አይስማሙም “ጎበዝ አይደለሁም” ይላሉ።

“በትምህርት ቤት እያለሁ ይሄን ያህል የላቀ ውጤት የማመጣ አልነበርኩም። ብዙ ጊዜ ኤ ማይነስ ነበር የማመጣው። ብዙም ኤ አላመጣም ነበር። መካከለኛ ተማሪ ነበርኩ” ይላሉ።

“በኦፕን ዩኒቨርስቲ ከወሰድኳቸው ኮርሶች አንድ ወይም ሁለቱን የማዕረግ ክብር አግኝቼ ይሆናል” የሚሉት የዕድሜ ባለጸጋዋ ነገር ግን ትምህርት ለመማር “በጣም ጎበዝ መሆን አያስፈልግም” ሲሉ አጽንኦት ይሰጣሉ።

ለዚያም ነው ቤተ ክርስቲያናቸው በቅርቡ ትጋታቸውን እና አስደናቂ ግኝቶችን የሚገልጽ የዕውቅና ሽልማት የሰጣቸው።

እንዲሁም የኦፕን ዩኒቨርስቲ ምክትል ዩኒቨርስቲ ኢያን ፒክ አፕ ለዕድሜ ባለጸጋዋ በጻፉት ደብዳቤ “የእርስዎ እውቀት መሻት እና ፍለጋ በሁሉም ዕድሜ ላሉ ሰዎች የተስፋ ብርሃን እና ማበረታቻ ነው።ጽናት እና ቁርጠኝነት ካለ ሁሉ ነገር ይቻላል የሚለውንም ማሳያ ነው” ብለዋቸዋል።

ዲግሪያቸውን በርቀት እየተማሩ ያሉት ሉሲል በዕድሜ ለእሳቸው ቅርብ የሆኑ ሌሎች ሰዎችን እንደሚያበራታቱ ተስፋ አድርገዋል።

ቤተ ክርስቲያናቸው በሰጣቸውም ዕውቅናም ሆነ በዩኒቨርስቲው ሙገሳ የተደሰቱት ሉሲል “በጣም ተደስቻለሁ። አረጋውያን ጭንቅላታቸውን የሚያሠራ ነገር እና በሕይወታቸው አንድ ነገር እንዲያደርጉ ለማበረታት ማስቻል ትልቅ ነው” ይላሉ።

“አንድ ቀን ካልተማርኩ ወይም ካላጠናሁ በሌላኛው ቀን ሳጠና የበለጠ የተሻለ ስሜት ይሰማኛል። በርካቶች ይህንን አያውቁም የሚሉት የዕድሜ ባለጸጋዋ መማር እና ማጥናት “ለአዕምሮ ጥሩ ነገር ነው” ሲሉም ምክራቸውን አስተላልፈዋል።