ኢራቃዊቷ የቲክቶክ ኮከብ ኦም ፋሃድ ባግዳድ ውስጥ በተተኮሰባት ጥይት ተገደለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢራቃዊቷ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪ ኦም ፋሃድ በባግዳድ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቷ ውጭ በተተኮሰባት ጥይት ተገደለች።
የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ጥቃቱ የተፈፀመው ከዋና መዲናዋ በስተ ምሥራቅ በሚገኘው ዛይን ሰፈር አርብ ዕለት ነው።
የኢራቅ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ዝነኛ የሆነችው ግለሰብ ‘ባልታወቁ ታጣቂዎች’ መገደሏን ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል።
የግለሰቧን አሟሟት ለመመርመርም ልዩ የምርመራ ቡድን መሰማራቱን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በመዝገብ ስሟ ጉፍራን ሳዋዲ የተባለችውና በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቿ ፋሃድ በሚል መጠሪያ የምትታወቀው ሴት ብቻውን ሞተር ሳይክል እያሽከረከረ በነበረ ግለሰብ መኪናዋ ውስጥ ሳለች በተተኮሰባት ጥይት እንደተገደለች ተዘግቧል።
አንድ የኢራቅ የደኅንነት ምንጭ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ጥቃት ፈፃሚው ምግብ አድራሽ እንደሆነ ሲያስመስል ነበር።
ባለቤትነቱ የአሜሪካ የሆነው አል ሁራ የዜና ወኪል በበኩሉ በዚህ ጥቃት ሌላ ሴትም ላይ ጉዳት መድረሱን ዘግቧል።
ፋሃድ በፖፕ ሙዚቃ እየደነሰች በምትለቃቸው ቪዲዮዎች ዝነኛ የሆነች ሲሆን በዚህም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮችን አፍርታለች።
ፋሃድ ባለፈው ዓመት “ግብረ ገብነትን እና የሕዝብን የሞራል ልዕልና የሚጥሱ” ቪዲዮዎችን አጋርታለች በሚል የስድስት ወር እስር ተላልፎባት ነበር።
የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾችን ይዘት የሚቆጣጠር እና ተጠያቂ የሚያደርግ የመንግሥት ኮሚቴ መቋቋሙን ተከትሎ ነበር ይህ ውሳኔ የተላለፈባት።
በወቅቱ ገለልተኛ የሆነው የአውሮፓ- ሜድትራኒያን የሰብዓዊ መብት ተቆጣጣሪ “የኢራቅ ባለሥልጣናት ተፈጥሯዊ የሆኑ መብቶችን በመገደብ ግልጽ ባልሆኑ ውንጀላዎች ” በበርካታ የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጣሪዎች ላይ የሚፈፅሙት እስር እና የሚበይኑት ፍርድ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ገልጾ ነበር።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በፋሃድ እና በተፎካካሪዋ ዳይላ ናኤም መካከል ያለው ፍጥጫ ተካሮ ነበር።
ብዙ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምናዎችን በማድረጓ ምክንያት ‘የኢራቅ አሻንጉሊት’ በሚል የምትታወቀው ናኤም፣ ፋሃድ ከከፍተኛ የኢራቅ ባለሥልጣናት ጋር አላት ያለችውን ግንኙነት ለማጋለጥ ስትዝት እንደነበር መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።












