ዝነኛው አሜሪካዊ ቲክቶከር ሲኒማ ቤት በተከፈተበት ተኩስ ተገደለ

አንቶኒ ባራጃስ

የፎቶው ባለመብት, Anthony Barajas

አሜሪካዊው ቲክቶከር እና አንድ ጓደኛው በደቡባዊ ካሊፎርኒያ ሲኒማ ቤት በጥይት እንደተገደሉ ከፖሊስ እና ከሟች ቤተሰብ ተረጋግጧል።

በቲክቶክ በሚሠራው ቪዲዮ ዝናን ያተረፈውና አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተከታዮች የነበሩት የ19 ዓመቱ አንቶኒ ባራጃስ እና የ18 ዓመቱ ራይሊ ጉድሪክሪች የተባለው ጓደኛው በኮሮና ግዛት በሚገኝ ሲኒማ ቤት ውስጥ ጭንቅላታቸው ላይ በተተኮሰባችው ጥይት ለህልፈት ተዳርገዋል።

ራይሊ ከጥቃቱ በኋላ ወዲያው የሞተ ሲሆን አንቶኒ ግን በሕይወት ቆይቶ የነፍስ ማዳን ክትትል ሲደረግለት ነበር። ሆኖም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሕይወቱ ማለፉን ቤተሰቡ አስታውቋል።

የኮሮና ፖሊስ ጥቃቱ "ፍፁም ምክንያታዊ አይደለም" ብሏል።

ዝነኛውን ቲክቶከርና ጓደኛውን ተኩሶ እንደገደለ የተጠረጠረው የ20 ዓመቱ ጆሴፍ ጂሜኔዝ ባለፈው አርብ በአካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ የነበረ ሲሆን፤ በግድያና በግድያ ሙከራ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶበታል። ተከሳሹ ወደ ችሎት ባለመግባቱ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል።

ፖሊስ ተከሳሹን በሁለተኛ ደረጃ የግድያ ወንጀል ክስ ለመጠየቅ ከዓቃቤ ሕግ ጋር እየሠራ እንደሆነም ተነግሯል። ተጠርጣሪው በዚህ ወንጀል ጥፋተኛ የሚባል ከሆነ ያለበት የዕድሜ ክልል ቅጣቱን ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችል ነው።

ሟቾችና ገዳይን ለዚህ ድርጊት የሚጋብዝ ምንም አይነት ግንኙነት እንዳልነበረ ተሰምቷል።

አንቶኒዮኒኬሚካኤል በመባል የሚታወቀው አንቶኒ በቲክቶክ ላይ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተከታዮች ነበሩት። እንደ አውሮፓውያኑ ከ2019 ጀምሮ በቲክቶክ የተለያዩ ቪዲዮዎችን ይሠራም ነበር።

"ከፈገግታው እስከ ሩህሩህ ልቡ ድረስ የአንቶኒ መኖር እሱን ለሚያውቁት ሁሉ ስጦታ ነበር" ሲሉ የአንቶኒ ቤተሰቦች በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።