አገሬ አልመለስም ያለችው የቤላሩስ አትሌት ከፖላንድ ቪዛ ተሰጣት

ክሪስቲሲና ትሲማኑስካያ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ቤላሩስያዊቷ የአጭር ርቀት ሯጭ አሰልጣኞቿን በመተቸቷ ከኦሎምፒኩ ወደ አገሯ እንድትበር የተላለፈውን ውሳኔ ባለመቀበል ለደኅንነቷ ያላትን ፍራቻ ገልጻለች።

ይህን ተከትሎም ፖላንድ ለአትሌቷ ቪዛ መስጠቷን አስታውቃለች።

ክሪስቲሲና ትሲማኑስካያ ከእሷ ፈቃድ ውጭ ዕቃዋ ተዘጋጅቶ ወደ ቶኪዮ አውሮፕላን ማረፊያ እንድታቀና እንደተገደደች ትናገራለች።

የ24 ዓመቷ አትሌት አውሮፕላኑ ውስጥ ላለመግባት የፖሊስ ጥበቃን እንደጠየቀች ተናግራለች።

"ደህና ነኝ ብዬ አስባለሁ። ከፖሊስ ጋር ነኝ" ብላለች በፖሊስ መኮንኖች ተከባ።

ሰኞ በሴቶች 200 ሜትር ውድድር ላይ ለመወዳደር ስትዘጋጅ የነበረችው ሯጭ በአጭር ማሳሰቢያ ወደ ሌላ ውድድር ስለመግባቷ በማኅበራዊ ድር አምባዎች ላይ ቅሬታ አቅርባለች።

ወደ አገሯ እንድትመለስ በቡድኑ ኃላፊዎች "ጫና እንደተደረገባት" ተናገራ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴን (አይኦሲ) እርዳታ ጠይቃለች።

በፖለቲካ አመለካከታቸው የታሰሩ ወይም ከጎናቸው የቆሙ አትሌቶችን በሚደግፈው የቤላሩሳዊያን ስፖርት ሶሊዳሪቲ ፋውንዴሽን (ቢኤስኤፍኤፍ) ቴሌግራም ላይ በለጠፈችው ቪዲዮ "ያለ እኔ ፈቃድ እኔን ከአገር ለማስወጣት እየሞከሩ ነው" ብላለች።

አይኦሲ ከቤላሩስያዊ ባለሥልጣናት ማብራሪያ እንደሚፈልግ ተናግሯል።

ባለሥልጣናቱ ቀደም ሲል "በስሜታዊ እና በሥነ ልቦናዊ ሁኔታዋ" ምክንያት ከቡድኑ መቀነሷን ተናግረዋል።

በኋላ ላይ አይኦሲ ክሪስቲሲናን እንዳነጋገረ እና "ደኅንነት እንደሚሰማት ነግራኛለች" ብሏል።

ክሪስቲሲና ትሲማኑስካያ ሳትሳፈር በረራው ተካሂዷል። አሁን "ደህና" ስትሆን በፖሊስ ጥበቃ ሥር መሆኗን የቢኤስኤስኤፉ አናቶል ኮታው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ክሪስቲሲና ትሲማኑስካያ ቀደም ብላ ለዩሮፕያን ሬዲዮ ፎረ ቤላሩስ (ኢአርቢ) እንደገለጸችው ወደ አገሯ ለመመለስ ፈርታለች።

አንዳንድ የቡድን ጓደኞቿ ለመወዳደር ብቁ እንዳልሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ በሐሙሱ የ400 ሜትር የዱላ ቅብብሎሽ ውድድር በአጭር ጊዜ ማሳሰቢያ እንደገባች በቪዲዮ ክሷን አቅርባ ነበር።

ቪዲዮውን ከለጠፈች በኋላ የመንግሥት ሚዲያዎች የተቿት ሲሆን አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ 'የቡድን መንፈስ' የላትም ብሏል።

እሑድ ባለሥልጣናት ወደ ክፍሏ ገብተው ወደ ቶኪዮ አውሮፕላን ማረፊያ ከመሸኘቷ በፊት ዕቃዎቿን እንድታዘጋጅ አንድ ሰዓት መስጠታቸውን ገልጸዋል።

"የአሰልጣኞቻችንን ቸልተኝነት በኢንስታግራሜ ላይ በመናገሬ" ምክንያት ከቡድኑ እንደተወገደች ተናግራለች።

ቢኤስኤስኤፍ ባለፈው ዓመት በአወዛጋቢው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደገና በተመረጡት በፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ላይ በተደረገው ተቃውሞ ስፖርተኞችን ለመደገፍ እአአ ነሐሴ 2020 ተቋቋመ።

በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ምርጫውን ከተቃወሙ በኋላ የመንግሥት ኃይሎች አሰቃቂ እርምጃ ወስደዋል።

በተቃውሞ ከተሳተፉት መካከል አንዳንዶቹ ስፖርተኞች ሲሆኑ ድጋፍ ተቋርጦባቸዋል፣ ከብሔራዊ ቡድን ተቀንሰዋል ይባስ ሲልም ሰላማዊ ሰልፍ በማድረጋቸው ታስረዋል።

ከፖላንድ የጥገኝነት ቪዛ የተሰጣት ሯጯ ስለ ቤተሰቧ ደኅንነት "ፈርታለች" ሲሉ ኮታው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"በቤላሩስ ውስጥ በቤተሰቧ ላይ ስለሚደርሰው ጥቃት ትፈራለች። አሁን ለእሷ ዋነኛው ጉዳይ ይህ ነው።"