በፈተና ወቅት የተማሪዎችን መኮራረጅ ማስቀረት ይቻል ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የ2014 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ተፈታኝ ተማሪዎችን እና ወላጆቻቸውን ብቻ ሳይሆን የትምህርት ሚኒስትሩንም ጭምር ያስደነገጠ ነው።
የተመዘገበውን ውጤት “አስደንጋጭ” ያሉት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ ፈተናውን ከወሰዱት ከ980 ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከል ወደ 30 ሺህ የሚጠጉት ብቻ ናቸው ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ማግኘት የቻሉት ብለዋል።
ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?
በተደጋጋሚ በብሔራዊው ፈተና ይከሰታል ሲባል የቆየውን የፈተና ስርቆት ለማስወገድ በሚል የትምህርት ሚኒስቴር ባዘጋጀው ዕቅድ መሠረት ተማሪዎቹ ፈተናውን ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ መውሰዳቸው ይታወሳል።
በ2014ቱ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወቅት ኩረጃን በመቀነስ አልያም በማስቀረት ረገድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ውጤታማ ሥራ መስራቱን በርካቶች ይናገራሉ።
ኩረጃ በአገር አቀፍ ፈተናዎች ብቻ ሳይሆን በዕለት ተዕለት የትምህርት ሥርዓት ወቅት የሚያጋጥም መሆኑን የትምህርት ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ቢቢሲ ለዚህ ጽሑፍ ሲል ያነጋገራቸው ተማሪዎችም ቢሆን በፈተና ወቅት የምዘና ወረቀቶች ተሰርቀው እንደሚወጡ እና በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ በሰፊው እንደሚሰራጩ ያላቸውን ልምድ በመጥቀስ ተናግረዋል።
ትምህርት ሚኒስቴርም ቢሆን የአገር አቀፍ ፈተናው በቴክኖሎጂ ተደግፎ በበይነ መረብ (ኦንላይን) ታግዞ ካልተሰጠ የምዘናው ሥርዓት አደጋ ውስጥ መሆኑን በአንድ ወቅት ገልጾ ነበር።
የትምህርት ሚኒስትሩ ኩረጃን የማይጠየፍ ተማሪ ስለመፈጠሩ ተናግረው ለዚህ ደግሞ “ሁላችንም ኃላፊነት መውሰድ አለብን” ካሉ በኋላ፣ የመንግሥትም ሆኑ የግል ትምህርት ቤቶች፣ መምህራን፣ ወላጆች እንዲሁም መንግሥት ለተማሪዎቹ ውድቀት ተጠያቂነት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በ2014 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል ከ95 በመቶ በላዩ፣ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚያስገባቸውን ነጥብ ማምጣት እንዳይችሉ ያደረጓቸው በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ ይታወቃል።
ከእነዚህም መካከል አንዱ በስፋት ይከናወን ነበር የተባለው የመኮራረጅ ድርጊት መቀነስ ወይም በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱ አንዱ እንደሆነም ይነገራል።
ስለዚህም በትምህርቱ ዘርፍ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በበርካታ አገራት ውስጥ ትልቁ የራስ ምታት ስለሆነው ስለኩረጃ ጥቂት እንበል።
ኩረጃን እንደ መልካም ተግባር የሚረዱት ተማሪዎች
ወንድይፍራው ደጀኔ (ዶ/ር) በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ በኢዱኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር ናቸው። በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል ስላለ ኩረጃ ጥናት አድርገዋል።
ከዚህ ቀደምም በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የሚማሩ ተማሪዎች ስለኩረጃ ያላቸው አመለካከት ምን ይመስላል? የሚለውን ጥናት ሰርተው እንደነበር ይናገራሉ።
በዚህ ጥናታቸውም ተማሪዎች ኩረጃን “ጉዳት የሚያስከትል ነው” ብለው እንደማያምኑ መረዳታቸውን ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስረድተዋል።
ማስኮረጅን “ጓደኛን እንደመርዳት አድርገው ስለሚያስቡ እንደመልካም ተግባር” እንደሚረዱት ይናገራሉ።
ወንድይፍራው (ዶ/ር) እንደሚናገሩት ከሆነ ኩረጃ በትምህርት ሥርዓት ውስጥ የዕለት ተዕለት ክስተት እንደሆነ በጥናታቸው ወቅት መገንዘባቸውን ያስረዳሉ።
ተማሪዎች ለመኮረጃቸው አልያም ለማስኮረጃቸው የሚያቀርቡት ምክንያት የተለያየ ቢሆንም፣ በቀዳሚነት የሚያነሱት ግን ወደ ቀጣዩ ክፍል ለማለፍ፣ ሰውን ለመርዳት፣ መምህሩ በሚገባ ስለማያስተምር የሚል እንደሆነም ጨምረው ገልፀዋል።
እንደ ወንድይፍራው (ዶ/ር) ገለፃ በግልም ሆነ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች በኩረጃ ረገድ ልዩነት የሌለው ተሳትፎ ያደርጋሉ።
ኩረጃ ምንድን ነው?
በኢትዮጵያ ከቴክኖሎጂ መርቀቅ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ኩረጃዎችን ለማስቀረትም በብሔራዊ ፈተና ወቅት የበይነ መረብ አገልግሎት እንዲቋረጥ የተደረገበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።
ይህ ብቻም ሳይሆን የፈተና ወረቀቶች እንደገና የተዘጋጁበት ጊዜም አይዘነጋም።
ከዚህ ቀደም ቢቢሲ በሠራው አንድ ዘገባም በአማራ ክልል ተማሪዎች ለኩረጃ ይመቻቸው ዘንድ ከጎበዝ ተማሪዎች ጋር በማመሳሰል ስማቸውን በፍርድ ቤት አስለውጠዋል።
ኩረጃ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ሥርዓቱን የሚፈታተን ማነቆ እንደሆነ እኚሁ ምሁር ይስማማሉ።
ኩረጃ በአንድ የፈተና ክፍል ውስጥ ብቻ የሚካሄድ ሳይሆን በዕለት ተዕለት ትምህርት ሂደት ውስጥ የሚዳብር መሆኑን ጨምረው ያስረዳሉ።
የራስ ያልሆነን ሥራ እንደራስ አድርጎ ማቅረብ፣ ትክክለኛ ምክንያት ባለመስጠት መምህሩን ማሳሳት እና የማይገባን ውጤት ለማግኘት የሚደረግ ጥረት፣ ያልተገባ ውጤት ለማግኘት መምህርን ማታለል በአጠቃላይ ኩረጃ ነው ይላሉ ወንድይፍራው (ዶ/ር)።
ጓደኛ እንዲኮርጅ መርዳት፣ በግል የተሰጠ ምዘናን ወይንም የቤት ሥራ በቡድን መስራት ሁሉ በኩረጃ ስር እንደሚጠቃለሉ ጨምረው ይገልጻሉ።

የፎቶው ባለመብት, FaceBook
በትምህርት ቤት ሕይወታቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ በኩረጃ ላይ የተሳተፉ ግለሰቦች በርካታ መሆናቸውን በተለያዩ አገራት የተሰሩ ጥናቶች ያሳያሉ።
ተማሪዎች የሚኮርጁት ለፈተናው ወይንም ደግሞ ምዘናው በቂ የሥነልቦና ዝግጅት ሳይኖራቸው ሲቀር መሆኑን ይናገራሉ።
ተማሪዎች በተገቢው መጠን ራሳቸውን ካለመዘጋጀት ውጪ፣ ትምህርትን በአግባቡ አለመከታተል፣ ኩረጃ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሌለው ግንዛቤ መያዝ ወደ ኩረጃ የሚገፉ ሌሎች ምክንያቶች ናቸው ይላሉ።
ከዚህም በተጨማሪ ወንድይፍራው (ዶ/ር) እንደሚሉት የወላጆች “ልጆቼ ተምረው፣ ሕይወቴን ይለውጡኛል” የሚለው ገለጻ ልጆች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳርፋል።
ይህ ቤተሰብ የሚያደርገው ጫና ተማሪዎችን ለማበረታታት የተደረገ ነገር ቢሆንም፣ ለኩረጃ እንደሚገፋም ያስረዳሉ።
በራሱ ጥረት ወላጆቹ ወዳሰቡለት ስኬት መድረስ ያልቻለ ተማሪም የወላጆቹን ጫና ለመሸሽ ጎበዝ በሚባሉ ተማሪዎች ስር ጥገኛ በመሆን ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ይሞክራል በማለት ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።
ኩረጃ ከክፍል ክፍል ሲኬድ እያደገ የሚሄድ ብቻ ሳይሆን፣ በሕይወት ውስጥ ዘላቂ የሆነ ተጽዕኖ እንዳለውም ጨምረው ምሁሩ ይጠቅሳሉ።
“ጥናቶች በትምህርት ዓለም የነበረን የኩረጃ ሕይወት ወደ ሥራ ዓለም ስንገባም ያንኑ የመተግበር ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ እና ተያያዥነት እንዳለው ያመለክታሉ። አንድ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በኩረጃ ታግዞ ወደ ከፍተኛ ተቋም ሲገባ፣ እዚያም በኩረጃ ታግዞ ቢመረቅ በሥራው ዓለም መደለያ ለመቀበል አያቅማማም።”
ተማሪዎች በጓደኞቻቸው ዘንድ ሰነፍ ሆኖ ላለመታየት፣ በውጤት አንሶ ላለመታየት ወደ ኩረጃ እንደሚገቡም አክለው ተናግረዋል።
ኩረጃን የሚፀየፍ ተማሪ የለም?
በዓለማችን ላይ ከ1940ዎቹ ጀምሮ የተረደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ኩረጃ በመላው ዓለም እያደገ እና ስልቱን እየቀየረ የመጣ ተግባር ነው።
በ1940ዎቹ የኩረጃ መጠን 42 በመቶ ሲሆን አሁን 92 በመቶ ደርሷል።
አሁን ደግሞ ከመቶ ተማሪ ዘጠና ሁለቱ ኩረጃ ላይ መሳተፋቸውን ጥናቶች ያሳያሉ።
ኩረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩን እየቀየረ መምጣቱን ተማሪዎች ይናገራሉ። በፈተና ወቅት መልስ በቁራጭ ወረቀት ጽፎ መቀባበል አሁን አይታሰብም።
ተንቀሳቃሽ ስልክን ተጠቅሞ መልዕክት በመጠቀም መኮራረጅ የዘመኑ ዋነኛው መንገድ ነው።
ወንድይፍራው (ዶ/ር) በሰሩት ጥናት ተማሪዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚያጠፉት “እንዴት አድርጌ እኮርጃለሁ” የሚለው ላይ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ተማሪዎች በተለይ የፈተና ወቅት ሲደርስ፣ የአገር አቀፍ እና ክልላዊ ፈተናዎች ባሉባቸው ክፍሎች (8ኛ እና 12ኛ) የኩረጃ ስልት በአግባቡ እስከመንደፍ ይደርሳሉ።
ወንድይፍራው(ዶ/ር) ጥናታቸውን በመጥቀስ ለኩረጃ በክፍል ውስጥ አንድ ጎበዝ የሚባል ተማሪ ካለ በቂ ነው ይላሉ።
ተማሪዎቹ ወደ መፈተኛ ክፍል ከመግባታቸው በፊት፣ ለኩረጃ ሲዘጋጁ ኔትወርክ ፈጥረው፣ የመጀመሪያው እቅድ ባይሳካ በሚል ሁለት እና ሦስት ዕቅዶችን ነድፈው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Education
ከዚህ በተጨማሪ የነደፉት ስልት በፈተና የመጀመሪያ ቀን ካልሰራ፣ ለቀጣዩ ፈተና ቀን ሌላ ስልት ነድፈው እንደሚመጡም ይናገራሉ።
የሞባይል ቴክኖሎጂን ተጠቅመው በሚያደርጉት ኩረጃም ከትምህርት ቤት ውጪ ያሉ ግለሰቦችን እንደሚያካትቱ ጨምረው ያስረዳሉ።
አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ተማሪዎቻቸውን የመደገፍ ነገር ማስተዋላቸውን የሚናገሩት ወንድይፍራው (ዶ/ር)፣ በትምህርት ቤቶች መካከል ያለው ውድድር ለዚህ አስተዋጽኦ ማድረጉንም ይጠቅሳሉ።
ለፈተና ስርቆት እና ኩረጃ መስፋፋት እገዛ የሚያደርገው ቴክኖሎጂ ብቻ ሳይሆን የመምህራን እና የትምህርት ቤት አስተዳደሮች ቁርጠኛ አለመሆን ጭምር መሆኑንም አክለዋል።
በኩረጃ ሲሳተፉ የተገኙ ተማሪዎች ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች ምን ያህል ፈጣን እና አስተማሪ ናቸው? ሲሉ የሚጠይቁት ምሁሩ፣ የተወሰደ እርምጃ ቢኖር እንኳ ለተማሪዎች በፍጥነት አለመንገር ለኩረጃ መስፋፋት አስተዋጽኦ ያደርጋል ይላሉ።
ኩረጃን ማስቀረት ይቻላል?
ኩረጃን ማጥፋት ሳይሆን መቀነስ ይቻላል የሚሉት ወንድይፍራው (ዶ/ር)፣ ለዚህም ከመጀመሪያ ደረጃ አንስቶ ተማሪዎች ስለታማኝነት እየተማሩ መምጣት እንዳለባቸው ይመክራሉ።
ታዳጊዎች ከታች ክፍል ጀምሮ መኮረጅ አስፀያፊ መሆኑን እየነገሩ ማሳደግ በኋላ በከፍተኛ ትምህርት ተቋምም ሆነ በሁለተኛ ደረጃ ላይ በሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድ እንዲኖር ይረዳል።
ከሥርዓተ ትምህርት አንጻርም ስለኩረጃ፣ ስለታማኝነት በየትምህርት ዓይነቶቹ ላይ ማካተት እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።
መምህራንም ቢሆኑ ኃላፊነት ተሰምቷቸው በትክክል ተማሪዎቻቸውን መመዘን የሚያስችል ፈተና ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል።
ፈተና በሚሰጥበት ክፍል ውስጥም ቢሆን መምህሩ በአግባቡ መፈተን መቻሉ ኩረጃን ለመቀነስ የራሱ አስተዋጽኦ አለው ሲሉ ያስቀምጣሉ።
የትምህርት አስተዳደሮችም ቢሆኑ ለተማሪዎች በሚያወጧቸው መመሪያዎችን እና መተዳደሪያ ደንቦችን በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ለተማሪዎቹ በሚገባ ማስተዋወቅ እንደሚያስፍልጋቸው ይገልጻሉ።
የወጡ መመሪያ እና ደንቦችን ተከትሎም ለሚፈፀሙ ጥፋቶች የተቀመጡ ተገቢ ቅጣቶችን ሳይዘገዩ ተፈጻሚ ማድረግ ወሳኝ ነው ይላሉ።
ተማሪው ያጠፋውን ጥፋትን እና ቅጣቱን ለማገናኘት እንዲችል፣ ሲኮርጅ እንደተያዘ ወዲያውኑ እርምጃ መውሰድ ለትምህርት ቤቱ ተማሪዎችም ማሳወቅ ይገባል።














