የፊሊፒንስ ተማሪዎች የጸረ-ኩረጃ ባርኔጣዎች መነጋገሪያ ሆነዋል

የፎቶው ባለመብት, MARY JOY MANDANE-ORTIZ
የፊሊፒንስ ተማሪዎች ኩረጃን ለመከላከል በሚል ወደ መፈተኛ ክፍሎቻቸው አድርገዋቸው የገቡት ባርኔጣዎች ወይም ፊት መሸፈኛዎች በመላው ፊሊፒንስ ግርምትን ጭረዋል።
ሌጋዝፒ በተሰኘች አንዲት ከተማ በሚገኝ ኮሌጅ ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች የጓደኞቻቸውን የፈተና ወረቀት እንዳያዩ የሚጋርድ ባርኔጣ ፈጥረው ይዘው እንዲመጡ ተጠይቀው ነበር።
በዚሁ መሠረት ተማሪዎቹ በየቤታቸው ካሉ ቁሳቁሶች ባርኔጣቸውን አዘጋጅተዋል። አንዳንዶቹ ከእንቁላል መያዣ ሌሎቹ ከካርቶን ኮፊያቸውን አዘጋጅተው በፈተና ክፍል ውስጥ ተገኝተዋል።
ተማሪዎቹ ይህንን እንዲያደርጉ ያዘዙት መምህርት ''ተማሪዎቼ በሚያዝናናቸው መንገድ ታማኝነትን እንዲያረጋግጡ ስለፈለግኩ ነው ይህንን እንዲያደርጉ የጠየኩት'' ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, MARY JOY MANDANE-ORTIZ
በቢኮል ዩኒቨርሲቲ የምህንድስና ኮሌጅ የመካኒካል ምህንድስና ፕሮፌሰር የሆኑት ሜሪ ጆይ ማንዳኔ ሃሳባቸው "በእርግጥ ውጤታማ" ነበር ብለዋል።
በጥቅምት ወር ውስጥ በሚደረገው በዚሁ ፈተና በመቶዎች የሚቆጠሩ የኮሌጁ ተማሪዎች ይህንኑ ጸረ ኩረጃ እርምጃ ተግብረዋል።
ፕሮፌሰር ማንዳኔ ከዓመታት በፊት በታይላንድ ተመሳሳይ ርምጃ ተወስዶ መመልከታቸውን እና ይህም ለእርሳቸው ሃሳብ መነሻ እንደሆነ ተናግረዋል።
የፊሊፒንሷ ፕሮፌሰር ማንዳኔ ይህንን ሃሳብ ለምህንድስና ተማሪዎቻቸው ካቀረቡ በኋላ ተማሪዎቹ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ በአቅራቢያቸው ከሚያገኟቸው ቁሳቁሶች ሠርተው መምጣታቸውን ተናግረዋል። እንዲሁም የአንዳንድ ተማሪዎች መሸፈኛ ውስብስብ ፈጠራ የታየበት መሆኑንም ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, MARY JOY MANDANE-ORTIZ
ሌሎች ተማሪዎች ደግሞ ግዴታቸውን ለማሟላት በማሰብ መደበኛ ኮፊያዎቻቸውን ጨምሮ እንብዛም ፈጠራ ያልታየባቸውን መሸፈናዎች ይዘው መጥዋል።
መምህሯ የተማሪዎቹን ፎቶ የያዘው የፌስቡክ ልጥፋቸው በጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻ በርካታ ሺ ሰዎች በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተቀባበሉት ሲሆን በፊሊፒንስ መገናኛ ብዙሃንም መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።
በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች የጸረ ኩረጃ የፊት መሸፈኛ እንዲያዘጋጁ አነሳስቷቸዋል ተብሏል።
ፕሮፌሰሯ እንዳሉት ታማሪዎቻቸው በዚህ ዓመት የተሻለ ውጤት አስመዝግበዋል። ይህም ጠንክረው በማጥናታቸው እና በፈተናዎች ወቀት በተደረጉ ጥብቅ ፍተሻዎች አማካኝነት ነው።
መምህሯ በዚህ አመት አንድም ተማሪ ለመኮረጅ ሲሞክር አልተያዘም ሲሉ ተናግረዋል።












