ኢትዮጵያ ውስጥ ለሠሯቸው ሥራዎች ከሕንድ መንግሥት ከፍተኛ ሽልማት የተቀበሉት ሕንዳዊ

ኢትዮጵያ ውስጥ ለሰሯቸው ስራዎች ከሕንድ መንግሥት ከፍተኛ የተባለውን ሽልማት የተቀበሉት የወለጋ ዩኒቨርስቲው ዶ/ር ካናን

የፎቶው ባለመብት, kanan

በወለጋ ዩኒቨርስቲ በቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ፋኩልቲ የሕዝብ አስተዳደር እና ልማት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ሕንዳዊው ካናን አምባላም (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ውስጥ ላከናወኗቸው ሥራዎች ከሕንድ መንግሥት ከፍተኛ የተባለው ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የሕንድ መንግሥት በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ዜጎቹ ማኅበረሰቡን ለመለወጥ የሚሰሩትን ሥራዎች በመመልከት በየሁለት ዓመቱ ሽልማትን ይሰጣል።

ጥር 02/2015 ዓ.ም. ከሕንድ መንግሥት እጅ ፕራቫሲ ባሃራቲያ ሳማን ሽልማት (PBSA) የተባለውን ከፍተኛ ሽልማት የተረከቡት ካናን አምባላም፣ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አዲስ አበባ የሚገኘው የሕንድ ኤምባሲም ዶ/ር ካናን አምባላም የተሰጣቸውን ሽልማት በመጥቀስ የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ ላይ አስፍሯል።

የወለጋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ሐሰን የሱፍ (ዶ/ር) በበኩላቸው “የየትኛውም አገር ዜጋ ቢሆንም በርትቶ ከሠራ እና መልካምነትን ካደረገ ሁሌ በበጎ ሽልማት ይመለሳል” ብለዋል።

ካናን አምባላም (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም በወለጋ ዞኖች እና በምዕራብ ጉጂ ዞን በገጠር የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ሕይወት ለመቀየር ባደረጉት ጥረት ከሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር የወርቅ ሜዳሊያ ሽልማት እና የእውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

ሚኒስቴሩ እሳቸው እና ተማሪዎቻቸው እንዲሁም ማኅበረሰቡ በመቀናጀት ያከናወኑትን ሥራ እውቅና በመስጠት ሌሎች ፕሮጀችቶችን ለመደገፍ የሚውል 25 ሺህ ብር በሽልማት መልክ ሰጥቷል።

“የተለያዩ ሽልማቶችን ከተለያዩ አካላት ተቀብለናል። አሁን ይህ በሕንድ መንግሥት የተሰጠን ግን የተለየ ነው። ሽልማቱ የበለጠ ኃላፊነት እንድንቀበል ያደርገናል” ብለዋል ዶ/ር ካናን።

ከሕንድ መንግሥት ለካናን አምባላም የተሰጠው ይህ ሽልማት ከፍተኛ የተባለ እና የተከበረ ሲሆን፣ በተለያዩ የዓለም ክፍል የሚኖሩ ሕንዳውያን በተለያዩ ዘርፎች ለኅብረተሰብ እድገት ላከናወኑት ሥራ በየሁለት ዓመቱ የሚሰጥ ነው።

ዶ/ር ካናን “ይህንን የኅብረተሰብ ችግርን የመፍታት ሥራ ላላፉት 10 ዓመታት ስንሰራ ቆይተናል። ይህ ሽልማት ደግሞ ለዚህ የተሰጠ እውቅና ስለሆነ የበለጠ ያበረታታናል። ለሽልማቱም የሕንድን መንግሥት ማመስገን እወዳለሁ” ብለዋል።

ዶ/ር ካናን በወለጋ ዩኒቨርስቲ በቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ፋክልቲ የሕዝብ አስተዳደር እና ልማት ውስጥ ከ12 ዓመት በላይ አስተምረዋል።

ከ10 ዓመታት በላይ ደግሞ ከማስተማር ጎን ለጎን የገጠሩን ማኅበረሰብ የሚጠቅሙ ፕሮጀክቶች ላይ ተሰማርተው ቆይተዋል።

በአነስተኛ ወጪ ድልድዮችን መገንባት፣ ምንጮችን ማጎልበት፣ የገጠር መንደሮች የኤሌትሪክ ብርሃን እንዲያገኙ ማድረግ እና የአርሶ አደሩ ማሳ ውሃ እንዲገባለት የመስኖ ሥራ ላይ ተማሪዎቻቸውን እና የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማሳተፍ የሚሰሯቸው ፕሮጀክቶች ናቸው።

ዶ/ር ካናን ከዚህ ቀደምም የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ከሰሩላቸው የማኅበረሰብ አካላት እና ከወለጋ ዩነኒቨርስቲ ሽልማቶችን ተቀብለዋል።

በወለጋ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ካናን (ዶ/ር) እና ተማሪዎቻቸው ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን የሰሩት ድልድይ

የፎቶው ባለመብት, KANNAN AMBALAM

በአነስተኛ ድልድይ የተጀመረው የማኅበረሰብ አገልግሎት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአነስተኛ ወጪ በአካባቢ በሚገኝ የሰው ሀብት እና ቁሳቁስን በመጠቀም በምሥራቅ ወለጋ ውስጥ የጀመሩት የልማት ሥራ፣ አሁን ወደ ቄለም ወለጋ፣ ምዕራብ ጉጂ እንደዚሁም ደግሞ በደቡብ ክልል ሃድያ ተስፋፍቷል።

በአዲስ አበባ እና አዲስ አበባ ዙሪያ በተለይ በአስኮ እና በቡራዩ ፕሮጀክቶች እንዳሏቸው ዶ/ር ካናን ተናግረዋል።

በተለያዩ ጊዜ ከተማሪዎቻቸው ጋር በየገጠሩ እየሄዱ አስቸጋሪውን የገጠሩን ማኅበረሰብ ኑሮ በማየት ይህንን የማኅበረሰብ አገልግሎት እንዲጀምሩ መነሻ እንደሆናቸው ሕንዳዊው መምህር ይናገራሉ።

ከተማሪዎቻቸው ጋር መረጃ ለመሰብሰብ ወደ አንዲት የገጠር መንደር በሄዱበት ወቅት ለሥራቸው መጀመር መልካም አጋጣሚ የተፈጠረው ተማሪዎች ለጥናት በተሰማሩበት ጊዜ ነው።

“ወለጋ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ አስተዳደር እና የልማት አመራር ክፍል በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ ትምህርት ለመስጠት ማሰቡን ተከትሎ ተማሪዎች በአካባቢው ተንቀሳቅሰው የሕዝቡን ችግር እንዲያጠኑ አደረግን። ከተማሪዎቹ ጋር ተጉዘን ማኅበረሰቡ በጣም የሚያሰስፈልጉት ነገሮች ምንድን ናቸው በሚለው ላይ መረጃ ሰበሰብን።”

በዚያ ወቅት ወደ ገጠራማው ክፍል ከተማሪዎቻቸው ጋር ባቀኑበት ጊዜ፣ በአነስተኛ ወንዝ አካባቢ የሚኖሩ አንዲት እናት ዕቃ ተሸክመው ለመሻገር ሲሞክሩ ተመለከቱ።

 ውሃው እየገፋቸውና ጭቃው እያዳለጣቸው በጣም ተቸግረው ወንዙን ተሻገሩ።

 “አንድ ሴት ድልድይ ያልተዘረጋባት ትንሽ ወንዝ ለመሻገር ስትቸገር አየኋት። ወድያውኑ ተማሪዎቹን አነሳስቼ ለምን ድልድይ አንሰራም? አልኳቸው። ለሁለት ቀናት እዚያ ቆይተን ምስማር፣ እንጨት ድንጋይ ሰብስበን ድልድይ ሰርተን ገባን።”

ይህ መነሻ ሆኖን ከዚያ በኋላ የድልድይ ችግር ባለበት እየሄድን መስራት ቀጠልን በማለት ስለጅማሯቸው ይገልጻሉ።

ዶ/ር ካናን ከተማሪዎቻቸው እና ከአካባቢው ማኅብረሰብ ጋር በመሆን እስካሁን 93 ድልድዮችን ገንብተዋል። 55 የምንጭ ውሃዎችን አጎልብተዋል። እንደዚሁም አርሶ አደሮች ለሚገለገሉባቸው መስኖዎች የሚሆን ሦስት አነስተኛ ግድብ ሰርተዋል። አንድ ገጠር ቀበሌም ኤሌትሪክ እንዲያገኝ ድጋፍ አድረገዋል።

“ብዙውን ጊዜ ራቅ ያለ ገጠር ውስጥ ሄጄ ኅብረተሰቡ እንዴት እንደሚኖር ሳይ፣ ማታ ወደ ቤቴ ገብቼ እንቅልፍ አይወስደኝም። ይህ ደግሞ ምሽትን ጨምሮ ቅዳሜ እና እሁድም እረፍት እንዳይኖረኝ አድርጎኛል” ይላሉ የወለጋ ዩኒቨርስቲ መምህሩ ካናን አምባላም (ዶ/ር )።

ሕንዳዊው መምህር ከሩቅ አገር እና ከሌላ ባሕል መጥተው ከገጠሩ ማኅበረሰብ ጋር ቅርበት ስለ ፈጠሩበት ምክንያት ሲያስረዱ “ለእኔ ሰብዓዊነት ይበልጥብኛል። ከሩቅ አገር ወይንም ከሌላ ቋንቋ እና ባሕል መምጣት ወደ ማኅበረሰቡ ቀርቦ መረዳዳትን አይከለክልም” ይላሉ።

በየገጠሩ በእግራቸው በርካታ ኪሎ ሜትሮችን ከተማሪዎቻቸው ጋር በመሆን የተለያዩ ፕሮጀክቶችን የሚሰሩት ሕንዳዊው መምህር “የአንድ መምህር ድርሻ ክፍል ገብቶ ማስተማር ብቻ አይደለም። አስተማሪዎች በዩኒቨርስቲ ውስጥ ተወስነው ከመቀመጥ ኅብረተሰቡ ውስጥ እየሄዱ ችግሮችን ለይተው መፍታት አለባቸው” ብለዋል።

ይህንን በማድረግም ተማሪዎቻቸው ችግር ፈቺ እንዲሆኑ በተግባር ማስተማር እንደሚቻል አክለዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ለሰሯቸው ስራዎች ከሕንድ መንግሥት ከፍተኛ የተባለውን ሽልማት የተቀበሉት የወለጋ ዩኒቨርስቲው ዶ/ር ካናን

የፎቶው ባለመብት, Dr. Kanaan Ambalam

“የሕዝቡ ጥያቄ የበለጠ እንድንሰራ አድርጎናል”

በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ አስተዳደርና የልማት አመራር ክፍል መምህር የሆኑት እኚህ ግለሰብ ለማኅበረሰቡ አንድ ፕሮጀክት በሰሩ ቁጥር ከአጎራባች ቀበሌ ነዋሪዎች በርካታ ጥያቄዎች እነደሚቀርብላቸው ይናገራሉ።

ይህ የሕዝብ ጥያቄም “የበለጠ እንድንሰራ አድርጎናል” ያሉት ዶ/ር ካናን ለዚህ ሥራቸው የሚሆን ገንዘብ ከየት እንደሚያገኙ ተጠይቀው፣ ፕሮጀክቶቻቸው ትንሽ ወጪ የሚጠይቁ ሆነው፣ ብዙውን ጊዜ በጋራ ትብብር የሚሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እርሳቸው እና ተማሪዎቻቸው የተወሰነ ሲያዋጡ በአብዛኛው ግን ፕሮጀክቱ የሚሰራለት የኅብረተሰብ ክፍል የቁሳቁስ እና የሰው ኃይል ድጋፍ ያደርጋል።

እንደ ሆሳዕና፣ ቡሌ ሆራእንዲሁም ደምቢዶሎ ራቅ ያሉ ስፍራዎች ሄደው በሚሰሩበት ወቅት ደግሞ፣ ለፕሮጀክቶቹ ከሚያወጡት ወጪ በተለየ ለትራንስፖርት ተማሪዎቹ እና እርሳቸው ተጨማሪ እንደሚያወጡ ይናገራሉ።

በሥራቸው ውስጥ የሕብረተሰቡ ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን የሚናገሩት መምህሩ፣ የተለያዩ አስፈላጊ ቁሳቁሶች እና የሰው ጉልበት ከሕብረተሰቡ እደሚያገኙ ይናገራሉ።

“የወለጋ ዩኒቨርስቲ በሚመለከተው ጉዳይ ከጎናችን ነው ያለው። የመንግሥት አካላትም በአብዛኛው ጊዜ ነገሮችን በማመቻቸት ያግዙናል።”

በአሁኑ ወቅት ድልድይ፣ ምንጭ ማጎልበት እና የመስኖ ሥራ በአጠቃላይ 25 ፕሮጀክቶች በእጃችን ላይ አሉ የሚሉት ዶ/ር ካናን የወደፊት ትኩረታቸው ደግሞ መስኖ እንደሚሆን ይናገራሉ።

“አርሶ አደሩ በመስኖ በማልማት በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ በማምረት በቂ የምግብ እህል እንዲያገኝ እንሰራለን”

የአስተማሪው እውቀት በዩኒቨርስቲ ውስጥ ተወስኖ መቅረት የለበትም የሚሉት መምህሩ፣ ኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ችግር በተጨባጭ የማይፈታ ከሆነ የእውቅት ትርጉሙ ምንድን ነው በማለት ይጠይቃሉ።