ሞትን የሚያስከትሉትን ሕገወጥ የአልኮል መጠጦች እንዴት መለየት እንችላለን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መርዛማ አልኮል ጠጥታ በማገገም ላይ የምትገኘው ሕንዳዊቷ ሳትያ “አብረውኝ ከጠጡት ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ሞተዋል . . . እኔም በሕይወት የምትረፍ አልመሰለኝም ነበር” ብላለች።
ሙሩጋን ደግሞ ተመሳሳይ መጠጥ ከጠጣ በኋላ ሕክምና ተከታትሏል። “ያዳኑኝ ዶክተሮች ናቸው። እተርፋለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። ራሴን ስቼ ነበር። እንዳልሞት ፈርቼ ነበር” ብሏል።
ሳትያ እና ሙሩጋን ከጥቂት ወራት በፊት በደቡባዊ ሕንድ፣ ታሚል ናዱ ግዛት ከሜታኖል ጋር የተቀላቀለ አልኮል ጠጥተው ሆስፒታል ከገቡት 219 ሰዎች መካከል ይገኙበታል።
ሕገ-ወጡን መጠጥ ከጠጡ በኋላ ቢያንስ የ57 ሰዎች ሕይወት አልፏል።

የፎቶው ባለመብት, BBC Tamil
ሙሩጋል “ለ20 ዓመታት አልኮል ጠጥቻለሁ። በሆስፒታል ያሳለፍኩት እያንዳንዱ ቀን እንደ አንድ ዓመት ሆኖ ነበር የተሰማኝ። በእርግጠኝነት ዳግመኛ መጠጥ ወደ አፌ አይዞርም” ሲል ለቢቢሲ ታሚል ተናግሯል።
ልክ በሌላው ዓለም እንደሚሆነው ሁሉ በታሚል ናዱ ወደ ሆስፒታል የተወሰዱት ሰዎች መርዝ ሲጠጡ እንደነበር አልገመቱም።

ሩሲያ ውስጥ በየዓመቱ 900 ሰዎች ሐሰተኛ አልኮል መጠጥ ከጠጡ በኋላ ሕይወታቸው እንደሚያልፍ የአገሪቱ ብሔራዊ የሸማቾች መብት ማኅበር ይገልጻል።
በኢራን ውስጥ እአአ በ2020 ብቻ 44 ሰዎች በመርዛማ አልኮል መሞታቸው ተዘግቧል።
በኢንዶኔዥያ ውስጥ ደግሞ እአአ በ2018 ቢያንስ 45 ሰዎች በቤት ውስጥ የተዘጋጀ አልኮል ከጠጡ በኋላ ሞተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሜታኖል
አብዛኛዎቹ አደጋዎች ከሜታኖል ጋር የተገናኙ ናቸው። ሜታኖል በሕገ ወጥ የአልኮል ምርቶች ውስጥ በብዛት የሚጨመር መርዛማ ውህድ ነው።
ሜታኖል የሚጨመረው አልኮሉ በሚመረትበት ወቅት ሲሆን፣ በማጣራቱ ሂደት ደግሞ ክምችቱ ክፍ ይላል።
ሕጋዊ አምራቾች የሰዎችን ጤና በማይጎዳ መጠን እንዲሆን ይቆጣጠራሉ።
ሕገወጥ አምራቾች ግን ብዙውን ጊዜ የሚጨምሩት ለኢንደስትሪ አገልግሎት የሚውለውን ሜታኖልን ነው። በቀለም እና በቫርኒሽ ውስጥ የሚያገኙትን ሜታኖል ቤት ውስጥ የሚያመርቱትን ርካሽ አልኮል ጠንካራ ለማድረግ ይጠቀሙበታል።
አነስተኛ መጠን ያለው ይህ መርዛማ ውህድ ዐይነ ስውርነትን፣ የጉበት ጉዳትን እና ሞት ሊያስከትል ይችላል።
ሜታኖል ፖይዝኒንግ ኢኒሼቲቭ (ኤምፒአይ) እንደ ተባለው ተቋም ከሆነ እአአ በ2023 ብቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ 60 ከሜታኖል ጋር የተገናኙ ክስተቶች ሪፖርት ተደርገዋል። በዚህም 309 ሰዎች ሞተዋል።
በኦስሎ ዩኒቨርሲቲ እና በድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) የተቋቋመው ይህ ተቋም አብዛኛዎቹ የመመረዝ ክስተቶች በእስያ አገሮች ውስጥ መከሰታቸውን ያሳያል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሜታኖል መመረዝ ምልክቶች
አነስተኛ መጠን ያለውን የኢንዱስትሪ ሜታኖል መጠጣት ጭምር በጣም አደገኛ ነው።
እንደ ዩናይትድ ኪንግደም የሕዝብ ጤና አገልግሎት ከሆነ ሜታኖል ሲሸተትም ሆነ ወደ ሰውነት ሲገባ ከባድ የጤና ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል። ከእነዚህም መካከል፡
- ራስን መሳት
- መንቀጥቀጥ
- የነርቭ ሥርዓት መጎዳት
- ዐይነ ስውርነት
- ሞት
በታሚል ናዱ ፑዱኮታይ የሚገኘው የመንግሥት የሕክምና ኮሌጅ ሆስፒታል ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ኤ ሙቱ በሜታኖል የሚመረተው አሲድ እንዴት ሰዎችን እንደሚገድል ለቢቢሲ አብራርተዋል።
“. . . አሲድ በኩላሊቶች ውስጥ ስለሚከማች ሽንት እንዳይወጣ ይዘጋል። ይህም የጨው መጠን መጨመርን እና የኩላሊት መድከምን ያስከትላል።”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዐይነ ስውርነት
በብሪቲሽ ጆርናል ኦፕቲሞሎጂ ላይ የወጣ አንድ ጥናት አነስተኛ መጠን ያለው ሜታኖል ጭምር ማዕከላዊውን የነርቭ ሥርዓት እንዲዛባ በማድረግ የማይድን ዐይነ ስውርነትን ሊያስከትል ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።
እንደ ጥናቱ ከሆነ በጣም ዘመናዊ የሚባሉ ሕክምናዎች ጭምር ሕገ-ወጥ አልኮል የጠጡ ታካሚዎችን ዕይታ ማዳን አይችሉም።
የሊንከን ካውንቲ ሆስፒታል አማካሪ የሆኑት ቪካስ ሶዲዋላ በ2012 ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ ታካሚዎች በማዞር፣ በማቅለሽለሽ፣ በሆድ ህመም፣ በማስታወክ እና በዐይን ብዥታ እየተሰቃዩ ወደ ሕክምና ተቋማት ያቀናሉ።
ተጎጂዎቹ መጠጡን ከሱቆች እና ከሚዘዋወሩ መኪኖች ላይ እንደገዙም ተናግረዋል።
“ሜታኖል በዐይን ጀርባ ላይ ያለውን ነርቭ ሊያጠቃ ይችላል። ይህ ደግሞ የሰውን ዕይታ የሚጎዳ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ዐይነ ስውር የሚያደርግ ነው” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዓለም አቀፍ ገጽታው
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሜታኖል መመረዝ የሚያጋጥመው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሰዎች ላይ ነው። ብዙውን ጊዜም ሪፖርት አይደረግም ሲል ኤምፒአይ ገልጿል።
ጥሩ ስም ያላቸው መጠጦች ዋጋቸው የማይቀመስ በመሆኑ፣ ቤት ውስጥ የሚዘጋጁ ርካሽ መጠጦች ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሰዎች ይመረጣሉ።
እአአ በ2011 በሕንዷ ምዕራብ ቤንጋል ግዛት ወደ 170 የሚጠጉ ሰዎች ሞተዋል። በ2009 ደግሞ በጉጃራት ከ100 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። ሙምባይ ውስጥ ደግሞ በ2015 አንድ መቶ ሰዎች ሞተዋል።
እአአ በ2022 በደቡብ አፍሪካ በሚገኝ የምሽት ክበብ ሲዝናኑ በሞቱ 21 ታዳጊዎች አስከሬን ላይ በተደረገ ምርመራም ሜታኖል ተገኝቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአልኮል እገዳ
በአንዳንድ የሙስሊም አገራት አልኮል መጠጣት የተከለከለ ነው። ምክንያቱም ሃራም (ክልክል) ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ነው።
እንደ ኢራን ወይም ኢንዶኔዢያ ባሉ ሙስሊም አገራት በሕገወጥ መጠጥ ምክንያት የሚከሰት ሞትን ለመከላከል እየሞከሯቸው ካሉ መንገዶች አንዱ ሃይማኖታዊ ትዕዛዝ ነው ይላሉ ባለሙያዎች።
ይህ ግን በእፍረት ወይም በወንጀልን መጠየቅን በመፍራት ሰዎች ከታመሙ በኋላ እርዳታ እንዳይጠይቁ ሊያደርጋቸው ይችላል።
እአአ በ2014 ቢያንስ 40 ሰዎች በፓኪስታኗ ሲንድ የተበከለ አልኮል ጠጥተው ሞተዋል።
ቱሪስቶች የሚጎበኟቸው እና የአልኮል መጠጦችን በብዛት የሚወስዱባቸው ቦታዎችን የሚጎበኙ ሰዎችም ሜታኖል የተቀላቀለበት መጠጦችን የመጠጣት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአልኮል መጠጥ መመረዙን እንዴት ማወቅ ይቻላል?
የትም አገር ቢሆኑ የሕገወጥ አልኮል ሻጮች ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ።
ዓለም አቀፉ የፖሊስ ኤጀንሲ ኢንተርፖል ከታዋቂ ሻጮች ብቻ መጠጥ መግዛትን ይመክራል። “ምርቱ ከመደበኛው ዋጋ በታች እየተሸጠ ከሆነ ወይም በአልኮሉ መደበኛ ታክሶች ካልተካተቱ ሕገወጥ ሊሆን ይችላል” ብሏል።
“ጥራት የሌለው ማሸጊያ፣ የፊደል ስህተቶች እና ያልተለመደ ቅርጽ ያላቸው ጠርሙሶች መሆናቸውን ይፈትሹ” ሲል ያክላል።
“መጥፎ ጠረን ካለውም ይጠንቀቁ! እንደ ቀለም ወይም የጥፍር ቀለም ማስለቀቂያ ዓይነት ሽታ ካለውም ሜታኖል ሊሆን ይችላል!” ብሏል።
ጥሩ ስም ያላቸው ቦታዎች ላይም ባለማወቅ መርዛማ መጠጡ እየተሸጠ ሊሆን ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈለግ ኤጄንሲው አሳስቧል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ናይጄሪያ
ናይጄሪያዊው የምግብ ባለሙያ ኦፔዬሚ በዋና ከተማዋ ከሚገኝ የምሽት ክበብ “ሐሰተኛ” የሆነ ጥሩ ስም ያለው ውስኪ ከጠጣ በኋላ በጠና መታመሙን ለቢቢሲ ተናግሯል።
“አስቂኝ ነበር። እየተዝናናህ ከሆነ ግድ አይሰጥህም። ግን ለአምስት ቀናት በጠና ታምሜ ነበር” ሲል አክሏል።
ልምዱን በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ካጋራ በኋላ በናይጄሪያ በሚገኙ በርካታ ከተሞች ውስጥ “ተንሰራፍቷል” ከሚባለው ሐሰተኛ አልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ ብዙ ሰዎች ተመሳሳይ ልምዳቸውን አካፍለዋል።
በበለጸጉ አገራት ደግሞ በተመሳሳይ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ወንጀለኞች አሉ።
ግሪክ

ሃና ፓውል በግሪኳ ዛንቴ ከጓደኞቿ ጋር የምሽት ክለቦችን ስትጎበኝ ከቆየች በኋላ ደክሟት ነበር። የወሰደችው ምግብም አልረጋ ብሏት ነበር።
ከመጠጥ በኋላ የሚከሰት ህመም ግን አልነበረም።
የ23 ዓመቷ ወጣት ሳታውቀው ከገዳዩ ሜታኖል ጋር የተቀላቀለ ቮድካ ጠጥታ ነበር። ይህም ኩላሊቶቿን አዳክሞ፣ ዐይነ ስውር አደረጋት።
እአአ በ2019 ለቢቢሲ ኒውስቢት እንደተናገረችው ከሆነ “የማፊያ ቡድኖች ጫካ ውስጥ አምርተው በርካሽ ዋጋ ይሸጣሉ። መጠጥ ቤቶችም መደርደሪያቸውን በዚህ መጠጥ ይሞሉታል።”
እአአ በ2009 ደግሞ ባሊ ውስጥ ሜታኖል የተደባለቀበት ወይን ጠጅ ከጠጡ በኋላ 25 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። አራቱ የውጭ ዜጎች ናቸው።
“መብራቱን ለማብራት ተነሳሁ። ያኔ ነው መደናገጥ የጀመርኩት ምክንያቱም መብራቱ እንደበራ እና ምንም ነገር ማየት እንዳልቻልኩ የገባኝ ያኔ ነው” ብላለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩሲያ
ሐሰተኛ ቮድካ በቀላሉ ወደ ሩሲያ ግሮሰሪዎች ይገባል። እስከ 2000 ዎቹ አጋማሽ ድረስ በሱፐርማርኬቶች ከሚሸጠው አልኮል ግማሽ ያህሉ ሐሰተኛ ነበር።
እአአ በ2023 በሱፐርማርኬቶች ውስጥ በሕጋዊ መንገድ የተሸጠውን “ሚስተር ሳይደር” የተባለ አልኮል ከጠጡ በኋላ 30 ሰዎች በበርካታ የሩሲያ ክልሎች ሕይወታቸው አልፏል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የሩሲያ መንግሥት ሕጋዊ አምራቾች ብቻ ማመልከት እንደሚችሉ ለማረጋገጥ የአልኮል አምራቾች የፍቃድ አሰጣጥ ደንቦቹን አጠናክሯል።
የተጎዱት ሰዎች ብቻ አይደሉም
እንደ ስሪላንካ ባሉ አንዳንድ አገሮች ሕገወጥ የአልኮል ምርት በአካባቢ እና በዱር እንስሳት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው።
እአአ በ2022 የዱር አራዊት ጠባቂዎች ኩምቢው ሕገ-ወጥ አልኮል ለማምረት በሚውል በርሜል ውስጥ የተቀረቀረ ዝሆንን ለማዳን ችለዋል።
ዝሆኖች በሚዘዋወሩባቸው አካባቢዎች ሕገ ወጥ የአልኮል ምርታቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ዝሆኖችን ገድለዋል በማለት የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ይከሳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሜታኖል እና የኤታኖል ልዩነት
ኤታኖል እና ሜታኖል ለነዳጅነት እና ነገሮችን ለማሟሟት የሚያገለግሉ የአልኮል ዓይነቶች ናቸው።
ኤታኖል ውድ ኬሚካል ሲሆን እንደ ቢራ፣ ወይን እና በመሳሰሉት የአልኮል መጠጦች ውስጥም ይገኛል።
አልኮል መጠጣት ራስ ምታት እና ማቅለሽለሽ ሊያስከትል ቢችልም ይህ ግን ጊዜያዊ ነው።
ይሁን እንጂ አነስተኛ የአልኮል ሽታ ያለው እና በአንጻራዊነት ርካሽ የሆነው ሜታኖል ግን በጣም መርዛማ እና ለምግብነት የማይሆን ነው።












