በሕንድ የተመረዘ አልኮል የጠጡ ቢያንስ 34 ሰዎች ሞቱ

በሕንድ ደቡባዊ ግዛት ታሚል ናዱ፣ በሕገ ወጥ መንገድ የተዘጋጀ የተመረዘ የአልኮል መጠጥ የጠጡ ቢያንስ የ34 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ባለሥልጣናት ተናገሩ።
አደጋው ያጋጠመው በካላኩሩቺ ወረዳ ሲሆን፣ በርካታ ነዋሪዎች ማክሰኞ ምሽት ላይ የአልኮል መጠጡን ከጠጡ በኋላ ታመው ነበር።
ለህመም የተዳረጉ ቢያንስ 80 ሰዎችም ደግሞ በሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ባለሥልጣናቱ ገልጸዋል።
እስካሁን ከክስተቱ ጋር ተያይዞ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን ሰፊ ምርመራም እየተካሄደ ነው ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ ያልተፈቀደ መጠጥ በግዛቱ ሲዘዋወር ዝም ብለው ተመልክተዋል የተባሉ አንድ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንን እና አስር የደንብ አስከባሪ አባላት ከሥራቸው ታግደዋል።
በሕንድ በየዓመቱ በሕገ ወጥ መንገድ በሚዘጋጁ የአልኮል መጠጦች ሳቢያ በርካታ ሰዎች ይሞታሉ።
እነዚህ መጠጦች በብዛት ሜታኖል የተባለ መርዛማ ንጥረ ነገር የሚጨመርባቸው ሲሆን፣ ይህም መጠጡን እንዳይቀዘቅዝ በማድረግ የአልኮል ይዘቱን እንዳይቀንስ ያደርገዋል።
ሆኖም ሜታኖል በትንሽ መጠን ቢወሰድ እንኳን ዐይነ ስውርነት፣ የጉበት ጉዳት እና ሞት ያስከትላል።
የአልኮል መጠጡን የጠጡ ሰዎች ማዞር፣ ራስ ምታት፣ ማስታወክ፣ ማቅለሽለሽ፣ የሆድ ህመም እና የዐይን ማሳከክ ምልክቶች ታይተውባቸዋል።
የታሚ ናዱ አስተዳዳሪ ለሟች ቤተሰቦች 12 ሺህ ዶላር የገንዘብ ካሳ እንዲሁም በሆስፒታል በህክምና ላይ ላሉት ደግሞ ለእያንዳንዳቸው 50 ሺህ ሩፒ ካሳ እንደሚከፍሉ አስታውቀዋል።
ባለሥልጣኑ በኤክስ (በቀድሞው ትዊተር) ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ “በወንጀሉ ላይ የተሳተፉ ታስረዋል። ይህንን ለመከላከል ኃፊነታቸውን ያልተወጡ ባለሥልጣናት ላይም እርምጃ ተወስዷል።” ብለዋል።
ሆኖም ተቃዋሚ ፓርቲዎች የግዛቲቱ አስተዳደር ይህን መርዛማ የአልኮል መጠጥ ማስቆም አልቻለም ሲሉ ተችተዋል።
የብሃራቲያ ጃናታ ፓርቲ መሪ ኬ አናማሊያ “በግዛቲቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሕገ ወጥ መልኩ በሚዘጋጅ መጠጥ ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ታሚል ናዱን አራት አስርተ ዓመታት ወደ ኋላ ወስዷታል።” ብለዋል።
በዚህም በግዛቷ የአልኮል ሽያጭን የሚቆጣጠሩት ሚኒስትር ከሥልጣናቸው እንዲለቁ አናማሊያ ጠይቀዋል።












