በኬንያ አልኮል እንዳይሸጥ የተጣለን ዕገዳ ጥሰው ሲጠጡ የነበሩ ፖሊሶች ተያዙ

የፎቶው ባለመብት, PRESS ASSOCIATION
በኬንያ አንድ ግዛት ውስጥ በርካታ ሰዎች በአልኮል መጠጥ ምክንያት ለሞት ከተዳረጉ በኋላ የተጣለውን ክልከላ ጥሰው ሲጠጡ የተገኙ የፖሊስ መኮንኖች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
በማዕከላዊዋ የኬንያ ግዛት ኪሪኒያጋ ውስጥ ኤታኖል ከተባለው ኬሚካል ጋር የተደባለቀ የአልኮል መጠጥ የጠጡ ከ20 በላይ ሰዎች ሕይወት ከጠፋ በኋላ ነው በግዛቲቱ ያሉ መጠጥ ቤቶች እንዲዘጉ የተወሰነው።
የግዛቲቲ አስተዳዳሪ አን ዋይጉሩ በርካታ ሰዎች በመጠጥ ምክንያት መሞታቸውን ተከትሎ ባለፈው ቅዳሜ ሁሉም የመጠጥ መሸጫ ቤቶች እንዲዘጉ አዘዋል።
አስተዳዳሪዋ መጠጥ ቤቶች እንዲዘጉ የወሰኑት በመጠጥ ንግድ ላይ በተሰማሩት ድርጅቶች ላይ ምርመራ ለማድረግ እና ተገቢው ፈቃድ እንዳላቸው ለማጣራት መሆኑ ተገልጿል።
የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ዋይጉሩ በአልኮል መጠጡ ምክንያት ሕይወታቸው ካለፈ ሰዎች መካከል የተወሰኑት በአንድ ላይ በተቀበሩበት ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር አስተዳደራቸው ጠንካራ እርምጃ እንሚውስድ ተናግረዋል።
“ፈቃድ ሳይኖራቸው መጠጥ ሲሸጡ የነበሩ ወይም ከዚህ በፊት ደኅንነታቸው ያልተረጋገጡ የአልኮል ውጤቶችን ሲሸጡ የነበሩ መጠጥ ቤቶች ድጋሚ ወደ ሥራ እንዲመለሱ አይፈቀድላቸውም።”
ነገር ግን ይህንን የአስተዳዳሪዋን ትዕዛዝ እንዲያስፈጽሙ ከተሰማሩት የፖሊስ መኮንኖች መካከል አራቱ አንድ መጠጥ ቤት ውስጥ አልኮል ሲጠጡ ተይዘዋል።
የፖሊስ አባላቱ የበርካታ ሰዎች ሞትን ተከትሎ የተጣለውን መጠጥ የመሸጥ እገዳ መተላለፋቸው በአካባቢው ባለሥልጣናት ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል።
ፖሊሶቹ እሁድ ዕለት ሊያዙ የቻሉት የአካባቢው ነዋሪዎች ለባለሥልጣናት የሰጡትን ጥቆማ ተከትሎ በአንድ መጠጥ ቤት ላይ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ነው።
በመጠጥ ቤቱ ውስጥ ከተያዙት ከአራቱ ፖሊሶች በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ጠጪዎች የነበሩ ሲሆን፣ ፖሊሶቹ እና የቤቱ ባለቤት ሲያዙ ሌሎቹ ማምለጣቸው ተዘግቧል።












