ሮናልዶ የመጀመርያው ቢሊየነር እግር ኳስ ተጫዋች ሆነ- ብሉምበርግ

ክርስቲያኖ ሮናልዶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ክርስትያኖ ሮናልዶ ለፖርቹጋል 223 ዋንጫዎችን በማሸነፍ የዓለም ክብረ ወሰንን ይዟል

ክርስቲያኖ ሮናልዶ በብሉምበርግ ዘገባ መሠረት የመጀመርያው እግር ኳስ ተጫዋች ቢሊየነር ሆነ።

የዓለምን ሀብታም ሰዎች የተጣራ ገቢ የሚከታተለው ብሉምበርግ ቢሊየነር ኢንዴክስ የ40 ዓመቱን ፖርቹጋላዊ እና የአል ናስር አጥቂ ሀብት ለመጀመርያ ጊዜ ተመልክቷል።

የሀብት ምዘናው በተጫዋችነት ዘመኑ የሚያገኘውን፣ ያሉትን ኢንቨስትመንቶች እና የማስታወቂያ ክፍያዎች የተመለከተ ሲሆን የሮናልዶ የተጣራ ሀብት 1.4 ቢሊዮን ይሆናል ብሏል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2002 እስከ 2023 ባሉት ዓመታት ብቻ ከደመወዝ ከ550 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘቱን እንዲሁም ከንግድ ስምምነቶች እና ናይኪን ጨምሮ ከሌሎች ስፖንሰሮች በዓመት 18 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያገኝ ተዘግቧል።

ሮናልዶ የሳዑዲ አረቢያውን አል ናስር እአአ በ2022 ሲቀላቀል በእግር ኳስ ታሪክ ከፍተኛ ነው የተባለውን 177 ሚሊዮን ፓውንድ በመቀበል ምርጡ ተከፋይ መሆን ችሏል።

የኮንትራት ጊዜው ሰኔ 2025 የሚጠናቀቅ ቢሆንም ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ስምምነት ኮንትራቱን ለሁለት ዓመት አራዝሟል።

በዚህም የተነሳ 42 ዓመት ከሞላውም በኋላ በክለቡ መቆየት ይችላል ማለት ነው።

በስፔን በነበረበት ወቅት ከሮናልዶ ጋር በተፎካካሪነት የተጫወተው እና የአርጀንቲና እና የኢንተር ሚያሚው ሊዮኔል ሜሲ በተጫዋችነት ዘመኑ ከግብር በፊት ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ደመወዝ ተከፋይ መሆኑን ብሉምበርግ ዘግቧል።

ይህ ከ2023 ጀምሮ 20 ሚሊዮን ዓመታዊ ቋሚ ክፍያን የሚጨምር ሲሆን በተመሳሳይ ወቅት ሮናልዶ ከሚያገኘው 10 በመቶ ብቻ ማለት ነው።

የ38 ዓመቱ ሜሲ ጫማውን ሲሰቅል በኢንተር ሚያሚ ድርሻ ይኖረዋል ተብሏል።