ክርስትያኖ ሮናልዶ የማሕበራዊ ሚዲያ ተከታዮቹ ቁጥር 1 ቢሊዮን ደረሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ክርስትያኖ ሮናልዶ በተለያዩ ማሕበራዊ ሚዲያዎች ያሉት ተከታዮች ቁጥር 1 ቢሊዮን ደረሰ።
ይህ ቁጥር በፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ትዊተር፣ ዩቲዩብ፣ እንዲሁም የቻይና ማህበራዊ ሚድያዎቹ በዌይቦ እና ኳኢሾ ያሉት አንድ ላይ ተደምረው ነው።
ተመሳሳይ ሰዎች በተለያዩ ማሕበራዊ ሚዲያዎች ስለሚከተሉት እንዲሁም የተወሰኑት ቦትስ በመባል የሚታወቁ ሐሰተኛ ገጾች በመሆናቸው 1 ቢሊዮን ግለሰቦች ይከተሉታል ማለት አይደለም።
ይኹን እንጂ በፒፒ ፎርሳይት ማሕበራዊ ሚዲያ ኤክስፐርት የሆነው ፓውሎ ፔስካቶሬ፣ ሚዲያዎች እና ብራንዶች በትኩረት የሚከታተሉት “አጃሂብ የሚያሰኝ ቁጥር” መሆኑን ተናግሯል።
“የሚያስደንቅ ስኬት ነው፣ በተጨማሪ ደግሞ በሚድያው ላይ ያለውን ለውጥም ያሳያል”
“ምስጋና ለቴክኖሎጂ ይሁን፤ አዲስ እና ወጣት ተከታዮችን ለማግኘት ተችሏል"” ብሏል ለቢቢሲ።
በእግር ኳስ ሜዳ ላይ ሮናልዶ ከአርጀንቲናው ኮከብ ሌኦኔል ሜሲ ጋር ይፎካከራል።
ከሜዳ ውጪ ግን በማሕበራዊ ሚዲያ ተከታዮች ውድድር ማንም አጠገቡ የሚደርስ የለም።
ሜሲ 623 ሚሊዮን ተከታዮች ብቻ ነው ያሉት።
በማሕበራዊ ሚድያ ላይ በርካታ ተከታይ ካሏቸው ዝነኛ ሰዎች መካከል ድምጻዊት እና ተዋናይ ሴሊና ጎሜዝ 690 ሚሊዮን፣ ድምጻዊ ጀስቲን ቢበር 607ሚሊዮን፣ እንዲሁም ድምጻዊት ቴይለር ስዊፍት 574 ሚሊዮን ተከታይ ነው ያሏቸው።
ቢቢሲ የተመለከታቸው ሌሎች ስመ ገናና የሆኑ አርቲስቶች ዘ ሮክ (557ሚሊዮን)፣ ካይሊ ጄነር (551 ሚሊዮን) እንዲሁም አርያና ግራንዴ (508 ሚሊዮን) ተከታዮች ነው ያሏቸው።
የዓለማችን ዝነኛው ዩቲዩበር፣ ሚስተር ቢስት (MrBeast) አጠቃላይ ያሉት ተከታዮች ብዛት 543 ሚሊዮን ብቻ ነው።
1 ቢሊዮን
እግር ኳስ ተጫዋቹ ክርስቲያኖ ሮናልዶ 1 ቢሊዮን ተከታዮችን ካፈራባቸው ምክንያቶች መካከል አንደኛው ባለፈው ወር የከፈተው እና በሳምንት ውስጥ 50 ሚሊዮን ወዳጆች ያፈራው ዩቲዩብ ገጹ ነው።
ሜሲ በተቃራኒው እኤአ ከ2011 ጀምሮ የተለያዩ ቪዲዮችን ቢጭንም ያሉት ግን 3.5 ሚሊዮን ተከታዮች ብቻ ናቸው ።
ሜሲ ዩቲዩቡ ላይ አዲስ ቪዲዮ ከጫነ ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ ሲሆን፣ ቀሪዎቹም በአፍ መፍቻ ቋንቋው፣ ስፓኒሽኛ፣ የቀረቡ ናቸው።
ሮናልዶ ግን ከባለቤቱ ጆርጂና ሮድሪጌዝ፣ እንዲሁም ከቀድሞ የማንችስተር ዩናይትድ ባልደረባው ሪዮ ፈርዲናንድ ጋር በእንግሊዘኛ ያደረጋቸው ጨዋታዎች ናቸው በገጹ ላይ የተለቀቁት።
ሮናልዶ በእነዚህ ቪዲዮዎች በስፓኒሽኛ ወይንም በፖርቹጊዝ ሲያወራ የእንግሊዘኛ ትርጉማቸው ከስር ለተመልካች መቀመጡ የበለጠ ተከታይ እንዲያፈራ አድርጎታል።
በተጨማሪም ዩቲዩብ ገጽ መክፈቱን በተለያዩ የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቹ ላይ ማስተዋወቁም ለቁጥሩ መጨመር አግዞታል።
ክርስትያኖ ሮናልዶ በርካታ ሪከርዶችን በመስበር ስም ያተረፈ እግር ኳሰኛ ነው።
ባለፈው ሳምንት ክሮሺያ ከፖርቹጋል ጋር ባደረጉት ‘የኔሽንስ ሊግ’ ጨዋታ ክርስቲያኖ ሮናልዶ 900ኛ ጎሉን አስቆጥሮ አዲስ ታሪክ ጽፏል።
ተጫዋቹ ዕቅና ባላቸው ጨዋታዎች ከፍተኛ የሆነውን 900 ጎሎች ያስቆጠረ ብቸኛ ተጨዋች ሆኗል።
ሮናልዶ ለመጀመሪያ ክለቡ ስፖርቲንግ ሊዝበን 5 ጎሎችን አስቆጥሯል። በመቀጠል ወደ ማንችስተር ዩናይትድ በማምራት በ293 ጨዋታዎች 118 ኳሶችን ከመረብ አገናኝቷል።
በመቀጠል በአውሮፓውኑ 2009 ‘ሪከርድ’ በነበረ 94 ሚሊዮን ዩሮ ሪያል ማድሪድን ተቀላቅሎ በ9 ዓመት ቆይታው በ438 ጨዋታዎች 450 ጎሎችን አስቆጥሯል።
በመቀጥል ወደ ጣልያኑ ክልብ ጁቬንትስ አቅንቶ በሶስት ዓመት ውስጥ 101 ጎሎች ማስቆጠር ችሏል። ከጁቬንትስ በኋላ ወደ ቀድሞ ክልቡ ማንችስተር ዩናትድ ተመልሶ በ54 ጨዋታዎች 27 ጎሎችን አስቆጥሯል።
ሆኖም ከማንችስተር ዩናትድ ጋር በአውሮፓውያኑ 2023 በውዝግብ ተለያይቷል። ከዚያም የሳዑዲውን አል-ናስር ተቀላቅሎ እየተጫወተ ሲሆን እስካሁን 68 ጎሎች አሉት።
በዓለም ላይ የሚገኙ ተጨዋቾች የሚያስቆጥሯቸው ማዕከላዊ የመረጃ ቋት ባይኖርም ሮናልዶ በይፋዊ እና በከፍተኛ ውድድሮች ያስቆጠራቸው ጎሎች ተመዝግበዋል። ይህም ቁጥር በዓለም ላይ ከፍተኛ ጎል ያለው ተጫዋቾች አድርጎታል።
ሮናልዶ አሁንም እየተጫወተ ያለ በመሆኑ ከተፎካካሪዎቹ በላቀ የማሕበራዊ ሚዲያ ተከታዮቹ ቁጥር ሊያድግ ይችላል።
ሮናልዶ እስካሁን በቲክቶክ ወይንም ትሬድ ማሕበራዊ ድረገጾች ላይ የለም።
እንደ ፎርብስ መጽሔት ከሆነ የሮናልዶ አጠቃላይ ገቢ ከአትሌቶች ሁሉ ከፍተኛው ሲሆን 260 ሚሊዮን ዶላር ሆኖም ተመዝግቧል።












