ሮናልዶ ዕውቅና ባላቸው ጨዋታዎች 900 ጎል ያስቆጠረ ቀዳሚ ተጨዋች ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትላንት ሐሙስ ክሮሺያ ከፖርቹጋል ጋር ባደረጉት ‘የኔሽንስ ሊግ’ ጨዋታ ክርስቲያኖ ሮናልዶ 900ኛ ጎሉን አስቆጥሮ አዲስ ታሪክ ጽፏል።
ተጫዋቹ ዕቅና ባላቸው ጨዋታዎች ከፍተኛ የሆነውን 900 ጎሎች ያስቆጠረ ብቸኛ ተጨዋች ሆኗል።
በትናንት ምሽቱ ጨዋታ የ39 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ 900ኛ ጎሉን ካስቆጠረ በኋላ በደስታ ስሜት ሆኖ በአግሮቹ ተንበርክኮ እና ፊቱን በእጆቹ ሸፍኖ በደስታ ሲያባ ታይቷል።
ላለፉት 20 ዓመታት ለፖርቹጋል ተስልፎ የተጨወተው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ትላንት 131ኛ ጎሉን ለሀገሩ ማስቆጠር ችሏል።
የሮናልዶ ለፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን ካስቆጠራቸው ጎሎች በተጨማሪ ለስፖርቲነግ ሊዝበን፣ ለማንቸስትር ዩናየትድ፣ ሪያል ማድሪድ፣ ጁቬንቱስ እና አሁን እየተጫወተ ለሚገኝበት ለአል ናስር በርካታ ኳሶችን ከመረብ አገናኝቷል።
ለፖርቹጋል በሔራዊ ቡድን እና ለሳዑዲ አረቢያው ክለብ አልናስር እየተጫወተ የሚገኘው ሮናልዶ ላለፉት 21 ዓመታት በእግር ኳስ ህይወት ቆይቷል።
ሮናልዶ ለመጀመሪያ ክለቡ ስፖርቲንግ ሊዝበን 5 ጎሎችን አስቆጥሯል። በመቀጠል ወደ ማንችስተር ዩናይትድ በማምራት በ293 ጨዋታዎች 118 ኳሶችን ከመረብ አገናኝቷል።
በመቀጠል በአውሮፓውኑ 2009 ‘ሪከርድ’ በነበረ 94 ሚሊዮን ዩሮ ሪያል ማድሪድን ተቀላቅሎ በ9 ዓመት ቆይታው በ438 ጨዋታዎች 450 ጎሎችን አስቆጥሯል።
በመቀጥል ወደ ጣልያኑ ክልብ ጁቬንትስ አቅንቶ በሶስት ዓመት ውስጥ 101 ጎሎች ማስቆጠር ችሏል። ከጁቬንትስ በኋላ ወደ ቀድሞ ክልቡ ማንችስተር ዩናትድ ተመልሶ በ54 ጨዋታዎች 27 ጎሎችን አስቆጥሯል።
ሆኖም ከማንችስተር ዩናትድ ጋር በአውሮፓውያኑ 2023 በውዝግብ ተለያይቷል። ከዚያም የሳዑዲውን አል-ናስር ተቀላቅሎ እየተጫወተ ሲሆን እስካሁን 68 ጎሎች አሉት።
በዓለም ላይ የሚገኙ ተጨዋቾች የሚያስቆጥሯቸው ማዕከላዊ የመረጃ ቋት ባይኖርም ሮናልዶ በይፋዊ እና በከፍተኛ ውድድሮች ያስቆጠራቸው ጎሎች ተመዝግበዋል። ይህም ቁጥር በዓለም ላይ ከፍተኛ ጎል ያለው ተጫዋቾች አድርጎታል።
ብራዚላውያኑ አንጋፍ ተጫዋቾች ፔሌ እና ሮማሪዮ እያንዳንዳቸው 1000 ሺህ ጎሎች አስቆጥራናል ብለው ይከራከሩ ነበር። ሆኖም የወዳጅነት ጨዋታዎች እና እውቅና በሌላቸው ጨዋታዎች ላይ ያስቆጠሯቸው ጎሎች ሲቀነሱ እያንዳንዳቸው ያስቆጠሯቸው ጎሎች ብዛት ወደ 700 ዝቅ ይላል።
የክርስትያኖ ሮናልዶ የርዥም ጊዜ ተቀናቃኝ ሊዮና ሜሲ እስካሁን 867 ጎሎች አሉት።
ሮናልዶ ወደ 40ኛ ዓመቱ እየገሰገሰ ቢሆንም 1ሺህ ጎል ሳላስቆጥር ከእግር ኳስ ህይወት አልርቅም ብሏል።
ከቀድሞ የቡድን አጋሩ ሪዮ ፈርዲናንድ በዩቲዩብ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ይህንን ስኬት በመጪው ሁለት ዓመታት እንደሚያሰካው በእርግጠኝንት ተናግሯ።
“አንድ ሺህ ጎል ላይ መድረስ እፈልጋለሁ። ጉዳት ካላጋጠመኝ ያንን ማድረግ እፈልጋለሁ” ብሏል።












