አርሰናል ከሊቨርፑል - ማን ያሸንፋል? የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ግምት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዘጠነኛው ሳምንት እንግሊዝ ፕሪሚር ሊግ ጨዋታዎች አርብ፣ ቅዳሜ እና እሑድ ይከናወናሉ።
የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ በአምሬትስ ሲከናወን አርሰናል ሊቨርፑልን ያስተናግዳል።
“የአርሰናል የአጥቂ እና የተከላካይ መስመር በጉዳት መሳሳት ያሳስበኛል” የሚለው የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን “ጁሪየን ቲምበር የማይሰለፍ ከሆነ ሞሐመድ ሳላህን ማን ሊያስቆመው ይችላል?” ሲል ጠይቋል።
ሱተን ይህንን ጨምሮ የሁሉንም ጨዋታዎች ግምት እንደሚከተለው አስቀምጧል።
አርብ
ሌስተር ከ ኖቲንግሃም ፎረስት
ሌስተሮች ከኋላ በመነሳት ሳውዝሃምፕተንን በማሸነፋቸው በጠንካራ በራስ መተማማን ላይ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
ብዙ ጎሎችን ባያስቆጥሩም ፎረስቶች ይህንን ጨዋታ እንደሚያሸንፉ እገምታለሁ።
ካለም ሃድሰን-ኦዶይ በጉዳት ካልተሰለፈ የሚጎዳቸው ቢሆንም የክሪስ ዉድ በጠንካራ አቋም ላይ መገኘት ግን ተስፋ ይሰጣቸዋል።
ግምት፡ 0 – 1
ውጤት፡ 1 - 3
ቅዳሜ
አስቶን ቪላ ከ በርንመዝ
አሁንም ጥያቄ እየሆነ የሚቀጥለው አስቶን ቪላ ከሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ በኋላ ምን ይመስል ይሆን ወይ የሚለው ነው።
የሚጫወቱት አርሰናልን ካሸነፈው በርንመዝ ጋር መሆኑ ደግሞ ጥያቄውን የበለጠ ሚዛን የሚደፋ ያደርገዋል።
ቪላ በዚህ ጨዋታ ያለመሸነፍ ክብረወሰኑን እንደሚያስቀጥል እና ጠንካራ ቡድን እንዳለው የሚያሳይበት ይሆናል።
ከቦሎኛ ጋር በርካታ ተጫዋቾችን ቀይረው መጫወታቸው ደግሞ ለዚህ ትልቅ ምክንያት ነው።
ግምት፡ 2 – 1
ውጤት፡ 1 - 1
ብሬንትፎርድ ከ ኢፕስዊች
ብሬንትፎርድ ጨዋታውን እንደሚያሸንፍ ምንም ጥርጥር የለውም።
እንደኢፕስዊች እና ሳውዝሃምፐተን ያሉ አዳጊ ቡድኖች ማሸነፍ ሳይችሉ በቆዩ ቁጥር የተጫዋቾቻቸው የራስ መተማመን እየቀነሰ መሄዱ ይጠበቃል።
ኢፕስዊች ከብሬንትፎርድ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ከባድ ይሆንበታል።
ከሁለቱ ብሬንትፎርድ ጠንካራው ቡድን ሲሆን በዚህ ጨዋታም ውጤት አያጡም።
ግምት፡ 2 – 0
ውጤት፡ 4 - 3
ብራይተን ከ ዎልቭስ
ዎልቭስ ባለፈው ሳምንት ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ጥሩ ለመፎካከር ቢችልም ባለቀ ሰዓት በተቆጠረበት ጎል ተሸንፏል።
ከብራይተን ጋር የሚያደርጉት የዚህ ሳምንት ጨዋታም ከባድ እንደሚሆንባቸው ይጠበቃል።
በዚህ ጨዋታም ለማሸነፍ ከጫፍ ደርሰው ውጤት ያጡ ይሆን?
ዎልቭሶች ጎል ማስቆጠር የሚችሉ ቢሆንም ብራይተን አሸንፎ ሦስት ነጥቦችን ይሰበስባል።
ግምት፡ 2 – 1
ውጤት፡ 2 - 2

ማንቸስተር ሲቲ ከ ሳውዝአምፐተን
ሳውዝሃምፐተን በዚህ ጨዋታ ምንም ነጥብ አያገኝም።
ኧርሊንግ ሃላንድ ባለፉት 3 ጨዋታዎች ኳስ እና መረብ አላገናኘም።
በዚህ ሳምንትም ሃላንድ ጎል አያስቆጥርም። ሲቲ ግን አራት ጎሎችን አስቆጥሮ መረቡን ሳያስደፍር ይወጣል።
ግምት፡ 4 – 0
ውጤት፡ 1 - 0
ኤቨርተን ከ ፉልሃም
በመጀመሪያዎቹ አራት ጨዋታዎች የተሸነፉት ኤቨርተኖች ባለፉት አራት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥቦችን እየሰበሰቡ ነው።
ቡድኑ ሾን ዳይሽን አጨዋወት ከመከተሉም በላይ ድዋይት ማክኔይልም በድንቅ አቋም ላይ ይገኛል።
ፉልሃም ጥሩ ከተንቀሳቀሰ የትኛውንም ቡድን ለማሸነፍ እንደሚችል በማሳየቱ ለሰማያዊ ለባሾቹ ፈተና መሆኑ ግልጽ ነው።
ሁለቱም ቡድኖች ሊያሰንፉ ቢችሉም ጨዋታው አቻ ሊጠናቀቅ ይችላል።
ግምት፡ 1 – 1
ውጤት፡ 1 - 1

እሑድ
ቼልሲ ከ ኒውካስል
ኒውካስሎች ካለፈው ዓመት አጨዋወታቸው ባይቀየሩም ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች ስምንት ጎሎችን ብቻ ነው ያስቆጠሩት።
አጥቂ መስመራቸው መሳሳቱ ደግሞ ነገሩን ይበልጥ ያባብሰዋል።
ኒውካስሎች በዚህ ጨዋታ ጎል ያስቆጥራሉ። ኮል ፓልመርን የያዘው ቼልሲ ግን የበለጠ ውጤታማ እሆናል።
ግምት፡ 2 – 1
ክሪስታል ፓላስ ከ ቶተንሃም
ያለፉትን ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች የተሸነፉት ፓላሶች የመጀመሪያውን የውድድር ዓመቱን ድል ለማስመዝገብ ይፈልጋሉ።
አሰልጣኝ ኦሊቨር ጋልስነርም ጫና ውስጥ ይገኛሉ።
ከጉዳት የተመለሰው የሰን ሁንግ-ሚን አቋም አስተማማኝ ባይሆንም ጨዋታውን ስፐርስ ያሸንፋል።
በከፍተኛ የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚጫወተው ስፐርስ ምን ያህል በዚህ መልኩ ይቀጥላል የሚለው አጠያያቂ ነው።
የቡድኑ አጨዋወትም ለፓላስ አጨዋወት የተመቸ ነው።
ፓላስ በርካታ አደገኛ ሙከራዎችን ኢያደርግም ስፐርስ ሦስት ነጥቦችን ይሰበስባል።
ግምት፡ 1 – 2

ዌስት ሃም ከ ማንቸስተር ዩናይትድ
ይህ ጨዋታ ከዌስትሃም ይልቅ ማንቸስተር ዩናይትድ ምን ያህል ተሻስሎ ይቀርብበታል ለሚለው ምላሽ የሚሰጥ ነው።
ዩናይትድ ባለፈው ሳምንት ከብሬንትፎርድ ጋር በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ነበር። ይህን ማስቀጠል እና ለ90 ደቂቃ ማሳየት ያስፈልጋል።
ማንቸስተር ሊያሳከው ይችላል? አይታወቅም።
ዩናይትድ አቋሙ ከመዋዠቁም በላይ ሐሙስ ምሽት በዩሮፓ ሊግ በመጫወቱ ድካም ሊኖር ይችላል።
ሱተን ልጁ ሶፊያ ያላትን የሂሳብ ቀመር ተጠቅማ ጨዋታውን እንድትገምት አድርጓል።
የሶፊያ ሱተን ግምት፡ 1 – 2

አርሰናል ከ ሊቨርፑል
ሊቨርፑል ከዚህ ጨዋታ በፊት ወደ አርቢ ሌፕዢግ መጓዙ ችግር ነው ቢባልም የአርሰናል ግን ከዚህም ይልቃል።
ሪካርዶ ካላፊዮሪ በሻምፒዮንስ ሊግ ከደረሰበት ጉዳት ተሽሎት የሚመለስ አይመስለም።
ከሁሉም የከፋው ደግሞ ዊሊያም ሳሌባ ደግሞ በቅጣት ከዚህ ጨዋታ ውጭ መሆኑ ነው።
ጁሪየን ቲምበር በዚህ ጨዋታ የማይሰለፍ ከሆነ ቦታውን ሚተካው ኦሌክሳንደር ዚቼንኮ ሞሐመድ ሳላህን የማቆም ከባድ ኃላፊነት ይኖርበታል።
ጋብሪኤል ጂሰስ ደግሞ ጎል በማግባት ቡድኑን መጥቀም እየቻለ አይደለም።
ሳሊባ ከተሰለፈ ሊቨርፑል አያሸንፍም። ካላፊዮሪ እና ቲምበር ካልተሰለፉ ደግሞ አርሰናል በቂ ተተኪዎች አይኖሩትም።
ግምት፡ 0 – 1












