ማንቸስተር ዩናይትድ ከአርሰናል፡ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ግምት

ሼሽኮ እና ጊዮኬሬሽ

የ2025/26 የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታ ከሁለት ወራት እረፍት በኋላ ነሐሴ 9/2017 ዓ.ም. ይጀመራል።

የዓመቱ የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታ መርሃ ግብር ሲጀመር የአምናው ሻምፒዮፒን ሊቨርፑል በሜዳው ቦርንመዝን ያስተናግዳል።

ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በሁለተኝነት ያጠናቀቀው አርሰናል ከሜዳው ውጪ ማንቸስተር ዩናይትድን ይገጥማል።ቼልሲ የኤፍ ኤ ካፕ ሻምፒዮኑን ክሪስታል ፓላስን ሲያስተናግድ፤ ማንቸስተር ሲቲ ከሜዳው ውጪ ከዎልቭስ ጋር ይጫወታል።

የቢቢሲው የስፖርት ፀሐፊ ክሪስ ሱተን እንደተለመደው በዚህ ዓመትም የሁሉንም ጨዋታዎች ግምት አስቀምጧል።

ተጠባቂውን የማንቸስተር ዩናይትድ እና የአርሰናል ጨዋታን ጨምሮ አብዛኞቹ ጨዋታዎች በጠባብ ልዩነት እንደሚጠናቀቁ ሱተን ገምቷል። የውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ግምቶቹ የሚከተሉት ናቸው።

አርብ
ሊቨርፑል ከቦርንመዝ

ሊቨርፑል ከቦርንመዝ

በዚህ ጨዋታ የሁሉንም የሊቨርፑል አዳዲስ ተጫዋቾች እንመለከታለን። ነገር ግን በቅርቡ በመኪና አደጋ ሕይወቱን ያጣውን የቡድን ጓደኛቸው ዲያጎ ጆታን በማሰብ የሐዘን ድባብ ይኖርባቸዋል።

ቦርንመዝ ብዙዎቹን ተከላካዮቻቸውን ቢሸጡም አሁንም በጥሩ ሁኔታ እንደተራጁ አምናለሁ። ቢሆንም ግን በዚህ ጨዋታ ግቦች ይቆጠራሉ ብዬ እጠብቃለሁ።

ቦርንመዝ አንፊልድ ላይ ግብ ያስቆጥራል። ነገር ግን ባለሜዳው ሊቨርፑል ተጨማሪ ግቦችን አስቆጥሮ ጨዋታውን ያሸንፋል።

ግምት፡ 3 -1

ቅዳሜ

አስቶንቪላ ከኒውካስል

የኒውካስትል ትልቁ ችግር የአጥቂው አሌክሳንደር አይዛክ ጉዳይ እልባት አለማግኘቱ ነው። ይህም ማለት በሊጉ ምርጥ ከሚባሉ አንዱ የሆነውን አጥቂያቸውን ሳያሰልፉ ይጫወታሉ ማለት ነው።

በዚህም ምክንያት አንቶኒ ጎርደንን ሐሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር አድርገው ይሰለፋሉ ማለት ነው። ይህ ደግሞ የሚሠራ አይመስልም።

አስቶን ቪላም የራሳቸው ጣጣ አለባቸው። ኦሊ ዋትኪንስ ሊለቅ ይችላል የሚሉ መረጃዎች በስፋት ይሠራጫሉ።

ሌላ አጥቂም አስፈርመዋል። ኒውካስል ከእነ ውዝግቦቹም ቢሆን አሁንም ጠንካራ ቡድን ነው። እንዲያም ሆኖ አስቶን ቪላ በሜዳው እንደማይደፈር እገምታለሁ።

ግምት፡ 2 - 1

ብራይተን ከ ፉልሃም

ፉልሃሞች በዚህ ዓመት የጨመሩት አዲስ ተጫዋች ባይኖርም አሁንም ጠንካሮች ናቸው።

ባለፈው ዓመት ለፉልሃም የሰጠኋቸው ግምቶች ያልተጠበቁ ቢሆንም አልፎ አልፎ ባልተጠበቀ ሁኔታ በርካታ ነጥቦችን ሰብስበዋል።

የጃኦ ፔድሮ መልቀቅ ተጽዕኖ ቢኖረውም ብራይተኖች አሁንም ጠንካራ ሆነው ሊጉን ይጀምራሉ። ጨዋታውን ለማሸነፍ የተሻለ ዕድል አላቸው።

ግምት፡ 1 - 0

ሰንደርላንድ ከዌስትሃም

ሰንደርላንድ ብዙ ለውጦችን አድርጓል። ካለፈው ዓመት በብዙ መልኩ የተለየ ቡድን ይዞ ነው የመጣው። ራዕያቸውን ብውደውም ዘላቂ ነው ብዬ ግን አላምንም። ከታች ለሚመጣ ቡድን ጅማሮው ቢያምርለት ሊጉ ላይ ለመፋለም ተስፋ ይሰጣል።

በዌስትሃም ላይ ጥያቄዎች አሉ። ለአሠልጣኙ ግራሃም ፖተር ትልቅ የውድድር ዓመት ነው። በጥሩ ሁኔታም ይጀምራል ብዬ አስባለሁ። በመሆኑም ሰንደርላንድን በጠባብ ልዩነት ያሸንፋሉ።

ግምት፡ 0 - 1

ቶተንሃም ከበርንሌይ

አዲሱን የቶተንሐም አሠልጣኝ ቶማስ ፍራንክን አደንቃቸዋለሁ።

ቶተንሐም በዚህ ክረምት ማንንም ቢያስፈርምም ቀድሞውንም ጥሩ ተጫዋቾች አሏቸው።

ከአምናው ደረጃቸው ከፍ ብለው ለመጨረስ ጠንክረው ይጫወታሉ። በርንሌይ ደግሞ በሊጉ ለመቆየት ይታገላል።

በርንሌይ ባለፈው ዓመት በሻምፒዮንሺፕ ሲጫወት ከ46 ጨዋታ በ30ው መረቡን አላስደፈረም። አሁን ግን ጨዋታው ከትልልቅ ተጫዋቾች ጋር ነው። በመሆኑም ቶተንሃም በቀላሉ ያሸንፋል።

ግምት፡ 3 - 0

ዎልቭስ ከማን ሲቲ

ዎልቭስ ከማንቸስተር ሲቲ

ዎልቭስ ባለፈው ዓመት በጣም የተጠናከረ ቡድን ነበር። ነገር ግን ዘንድሮ ትልቅ አስተዋጽኦ የነበረውን ማቲያስ ኩኒያን አጥተዋል። ያንን ክፍተት እንዴት ይሞሉታል?

የሮድሪ እንደገና መጎዳት ለማንችስተር ሲቲ በጣም ፈታኝ ነው። ቢሆንም ግን የተወሰኑ ሳምንታትን ያለ ሮድሪ መጋፈጥ ግድ ይላቸዋል።

ምን ዓይነት ተጫዋቾችን ይዘው እንደሚገቡም መገመት ይከብዳል። በመሆኑም ውጤቱ በጠባብ ልዩነት የሚጠናቀቅ ይሆናል።

ግምት፡ 1 - 2

እሑድ

ቼልሲ ከክሪስታል ፓላስ

በአሁኑ ወቅት ቼልሲ ውስጥ ብዙ አስደሳች ነገሮች አሉ።

የዓለም የክለቦች ዋንጫን አሸንፈዋል። አጥብቀው የሚፈልጉት ግን ፕሪሚየር ሊጉን ማሸነፍ ነው።

ነገር ግን ያንን ለማሳካት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ይህ ጨዋታ ማሳያ ይሆናል።

ምክንያቱም ክሪስታል ፓላስ በደንብ የተደራጀ እና አስቸጋሪ ቡድን ነው። ፉክክሩ ከባድ ቢሆንም ቼልሲ ያሸንፋል ብዬ አስባለሁ።

ግምት፡ 2 - 1

ኖቲንግሐም ከብሬንትፈርድ

ብዙ ሰዎች ሁለቱም ቡድኖች የምናውቀው ጥናካሬያቸውን አያሳዩም እያሉ ይጽፋሉ።

ብሬንትፎርዶች አሠልጣኛቸውን ለቶትንሃም ሰጥተዋል፣ ምቡዌሞ ወደ ማንችስተር ዩናይትድ አምርቷል።

ከዚህም በተጨማሪ ዊሳም ክለቡን መልቀቅ እንደሚፈልግ እየተነገረ ነው። ስለዚህ ማን ነው ግብ የሚያስቆጥረው?

ኖቲንግሃም ፎረስትም እንደ አምናው ጠንካራ ሆኖ ይቀጥላል ማለት ከባድ ነው። አንቶኒ ኢላንጋን ሸጠዋል፣ ክሪስ ውድ በመጪው ታኅሣሥ 34 ዓመት ይሆነዋል።

መልካሙ ነገር ሞርጋን ጊብስ ዋይት በክለቡ እንዲቆይ አድርገዋል። ጨዋታው ፈታኝ ቢሆንም ኖቲንግሃም ፎረስት ድል ያደርጋል ብዬ አስባለሁ።

ግምት፡ 1 - 0

ዩናይትድ ከአርሰናል

ማንቸስተር ዩናይትድ ከአርሰናል

የውድድር ዓመቱን ለመጀመር ይህኛው ድንቅ ጨዋታ ነው የሚሆነው። በማንቸስትር ዩናይትድ አዳዲስ ተጫዋቾች በጣም ተደምሜያለሁ። በተለይ በማቲያስ ኩንያ እና ብራያን ምቡዌሞ። በዩናይትድ ምን ዓይነት ጥሩ ጨዋታ እንደሚኖራቸው አይተናል።

ስለሁሉም ተጫዋቾች በቂ እውቀት አለኝ ማለት አልችልም። ስለዩናይትድ አዲሱ አጥቂ ቤንጃሚን ሴስኮ ያለኝ እውቀት ውስን መሆኑን መደበቅ አልፈልግም። ነገር ግን እምቅ አቅም ያለው ተጫዋች ይመስላል። የእርሱ መምጣትም ራስመስ ሆይሉንድ በኦልትራፎርድ የነበረውን ቆይታ እንዲቋጭ የሚያስገድድ ነው።

አርሰናልም አዲስ አጥቂ አስፈርሟል፤ ሩበን አሞሪምም ቪክቶር ጊዮኬረስ ጋር ስለሠራ ስለተጫዋቹ በቂ እውቀት አለው።

ጊዮኬሬስ ከሳካ እና ከማርቲን ኦዴጋርድ ጋር እንዴት ሊዋሃድ እንደሚችል ለማየት ጓጉቻለሁ።

ሁለቱ ቡድኖች ሲጫወቱ አንዱ ሌላውን ማሸነፍ ትልቅ ድል ስለሆነ ጨዋታው በሰፊው ይጠበቃል።

ጨዋታው በጣም ጠባብ ውጤት ይኖረዋል። ምንም እንኳ ለዩናይትድ መልካም ነገር ቢሰማኝም፤ በዚህ ጨዋታ ግን ይሸነፋሉ። ጊዮኬሬስም ለቀድሞ አሠልጣኙ መልዕክት ያስተላልፋል ብዬ አስባለሁ።

ግምት፡ 1 - 2

ሰኞ

ሊድስ ከኤቨርተን

ሰኞ በሊድስ እና ኤቨርተን ይጋጣመሉ፤የሊድስ አሠልጣኝ ዳንኤል ፋርኬ ብዙ ያልተወራለት ጎበዝ አሠልጣኝ ነው። ኤቨርተንን ያስጨንቁታል።

የኤቨርተኑ አለቃ ዴቪድ ሞይስ በጥር ወር ብዙ ስኬት ስላስመዘገቡ ብዙ የሚጠብቃቸው ይኖራል።

ኤቨርተኖች የማንቸስተር ሲቲውን ጃክ ግሪልሽን ጨምሮ አዳዲስ ተጫዋቾችን ቢያስፈርሙም መሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት አይችሉም።

ግምት፡ 1 - 1