የቀነኒ አባት ከአርቲስት አንዷለም ጎሳ ጋር ሲካሄድ የነበረውን ሽምግልና ለምን ሳይቀበሉ ቀሩ?

የፎቶው ባለመብት, FB
የቀነኒ አዱኛን ሞትን ተከትሎ በአባ ገዳዎች እና በሀገር ሽማግሌዎች የተጀመረው የእርቅ ሂደት ላለፉት ወራት ምን ውጤት አለማምጣቱ ታውቋል።
በአርቲስት ቀነኒ ግድያ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር ውሎ የነበረው ሙዚቀኛ አንዷለም ጎሳ ባለፈው ጥቅምት ከሦስት ወራት እስር በኋላ በዋስ ተለቋል።
ሙዚቀኛው በ50 ሺህ ብር ዋስ የተለቀቀው ዐቃቤ ሕግ በተሰጠው ጊዜ ክስ መመሥረት አለመቻሉን ተክተሎ መሆኑን ጠበቃው መናገራቸው ይታወሳል።
የቀነኒ ቤተሰቦች አንዷለም በዋስ መለቀቁ እንዳላስደሰታቸው እና በልጃቸው ሞት ጉዳይ እንደሚጠረጥሩት ተናግረዋል።
"የልጃችንን ፍትሕ አላገኘንም። እውነታውንም አላወቅንም። [አንዷለም በዋስ ሲለቀቅ] ልጃችን ለሁለተኛ ጊዜ ነው የተገደለችው" ሲሉ አባቷ አዱኛ ዋቆ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አንዷለም ጎሳ በቀነኒ አዱኛ ሞት እጁ እንደሌለበት ሲናገር ቆይቷል።
የቀነኒ ቤተሰብ በበኩላቸው ልጃቸው ራሷን ትጎዳለች ብለው እንደማያስቡ ይናገራሉ።
የሽምግልና ሒደት
የኢትዮጵያ ሕግ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን እንደሚል ግልፅ ባይሆንም አባ ገዳዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች በሁለቱ ቤተቦች መካከል ያለውን ጉዳይ በሽምግልና ለመፍታት ሙከራ ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
የቱላማ አባ ገዳ ጎበና ሆላ ይህ ጉዳይ ለሦስት ወራት ያህል "በጋዲሳ" (በባህላዊ ጥላ) ስር ሲታይ መቆየቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ይህ ጉዳይ በኦሮሞ ገዳ ስርዓት እንዲታይ እንዲፈቀድልን ጠየቅን። ሁለቱም ወገኖች በኦዳ ቡልቱም እና በቱላማ ገዳ ሥርዓት እንዲታይ ፈቃደኛ ሆነው ስንመለከተው ቆይተናል። ሦስት ጊዜ ተቀመጥን። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ወደ መጨረሻው የሚያደርሱን ዋና ዋና እውነታዎችን ካየን በኋላ፣ አራተኛውን ቀጠሮ ጭሮ ላይ አደረግን። በዚህ አራተኛው ቀጠሮ ላይ የሟች አባት አቶ አዱኛ ዋቆ 'ጋዲሳውን' (ጉዳዩን) ጥለውብን ቀሩ" ይላሉ።
ይህ የሆነው ባለፈው ጥቅምት ወር ነው።
የሟች አባት የሽምግልና ሒደቱን ካቋረጡ በኋላ "ሁለት ጊዜ ተቀምጠናል" ይላሉ አባ ገዳ ጎበና። አክለው "ጥሪ ቢደረግላቸውም አልቀረቡም፤ ለሦስተኛ ጊዜ ጭሮ ላይ እንዲገኙ ቢነገራቸውም ለመምጣት ፈቃደኛ አልሆኑም" ይላሉ።
ቢቢሲ አቶ አዱኛ የቀሩበትን ምክንያት ጠይቋል። እሳቸውም በሂደቱ ላይ "ጥርጣሬ ስላላቸው እና የልጃቸው እውነት ይወጣል ብለው ስላላሰቡ መቅረታቸውን" ገልጸዋል።
"ሽማግሌዎች ወደ ጭሮ ይመላለሱ ነበር፣ እኛ እንደ ቤተሰብ ይህን አናውቅም ነበር። 'እኛን እምቢ ካሉ ዘመዶቻቸውን እናመጣለን' እያሉ ሲያወሩ ሰምቻለሁ" በማለት በሂደቱ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ገልጸዋል።
ማክሰኞ ዕለት የነበረውን ቀጠሮም እንደማያውቁ እና እንዳልሄዱ ተናግረዋል።
"እኛ አልሄድንም፣ 'ጉማ' (የደም ካሳ) ተቀበሉ ይሉናል። ምን ዓይነት ጉማ ነው የምንቀበለው? 'ገድያለሁ' ካለ ፊት ለፊት ይውጣ፣ ካልገደለ ደግሞ ለምን ጉማ (ካሳ) ይከፍላል? ደግሞም ጉማ የሚቀበለው በዚህ መንገድ አይደለም።"
እንደ የሀገር ሽማግሌዎች ገለጻ፣ ለቃለ መሐላ ሥርዓቱ አንዱዓለም፣ እህቱ እና አንዲት ሠራተኛ ተገኝተው ነበር። "እውነቱ ሊወጣ ሲል ሂደቱ ተቋረጠ" ያሉት አባ ገዳ ጎበና፣ ቤተሰቦቸ ተጸጽተው ወደ ገዳ ሥርዓቱ ካልተመለሱ በስተቀር ጉዳዩ "በዘመን እና በገዳ ይፈታል" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, @Andualem Gosa
የቀነኒ ቤተሰቦች ቅሬታ ምንድነው?
አቶ አዱኛ ሽማግሌዎቹ "እውነትን ፈልገን ዕርቅ እናወርዳለን" ብለው ሲመጡ መቀበላቸውን ይናገራሉ። "ነገሩን ደግማችሁ አጣሩ አልናቸው። ሲያጣሩ ግን 'አልገደልኩም ግን ደም አለብኝ' የሚል ሐሳብ አነሳ። 'አልገደልኩም ግን ደም አለብኝ' ማለት ምን ማለት ነው? ካልገደለ መሐላ ለምን አስፈለገ?" ይላሉ።
በተጨማሪም "ልጃችን ብቻዋን እንደነበረች አድርገው ነው የነገሯቸው። የሞተች ዕለት ግን ቤት ውስጥ ቤተሰቦች ነበሩ። እሱን ብቻ ተጠርጣሪ አድርጎ መያዝ ችግር ነው" በማለት ሂደቱን ተችተዋል።
"ፊቷ እንዲህ እስኪሆን ድረስ ማን ይደበድባት ነበር? ማን ጥይት ይተኩስባት ነበር? ይህ ሳይለይ መሐላ መግባት አያስፈልግም" ይላሉ አቶ አዱኛ። "ራስዋን ገደለች የሚለው የማይመስል ነገር ነው" በማለት አባ ገዳዎች ጉዳዩን በጥልቀት እንዲመረምሩት ጠይቀዋል።
አንዷለም ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ "በዐይናችን አይተነው አናውቅም" የሚሉት አቶ አዱኛ፤ እሱ ጋር ያለው የቀነኒ ንብረት በሕግ እንዲመለስም ጠይቀዋል።
"ንብረቷንም እንኳ ይዞ እውነቷን ቢያወጣ ለኛ ትልቅ ነገር ነው።"
አባ ገዳ ጎበና ሆላ "እውነቱ ያለበትን አይተናል፣ ነገር ግን እውነቱን ማን ይቀበል?" ይላሉ። ስለ እውነቱ ሲጠየቁ "ባለቤቱ [የልጅቷ አባት] ሳይመጣና ሳይቀበል በዝምታ አይወጣም። ይህ መሐላ ነው" ብለዋል። በኦሮሞ ገዳ ሥርዓት የማይፈታ ነገር የለም የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ገልጸዋል።
ቢቢሲ አንዷለም እና በቅርበት ያሉ ቤተሰቦቹን ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
በቀነኒ ግድያ ተጠርጥሮ ለሦስት ወራት ያህል ታስሮ በዋስ የተለቀቀው አንዷለም አሁንም ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ ነው።
አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ መረጃዎች አንዷዓለም ነፃ መውጣቱን ቢናገሩም፣ አባ ገዳ ጎበና ግን "እውነቱን ሽማግሌዎች ተረክበው 'አንተ ነፃ ነህ፣ እጅህ ንጹህ ነው' ብለው እስካልታወጀ ድረስ ነፃ ነው አላልንም" ብለዋል።
ቀነኒ ማናት?
በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ዳሮ ላቡ ወረዳ በሚጨታ ከተማ የተወለደችው ቀነኒ ከልጅነቷ ጀምሮ በትምህርቷ ጠንካራ እንደነበረች የሕይወት ታሪኳ ያስረዳል።
በ2011 ዓ.ም ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሃይድሮሊክ እና ዋተር ኢንጅነሪንግ ተመርቃለች።
ከዚያ በኋላም በኦሮሚያ ክልል ውሃ እና ኢነርጂ ቢሮ ለተወሰነ ጊዜ ሠርታለች።
ቀነኒ በሞዴሊንግ፣ በማስታወቂያ እና በመዝናኛ ሥራዎቿ ትታወቃለች።
ሞዴል እንዲሁም የማስታወቂያ ባለሙያ የሆነችው ቀነኒ አዱኛ መጋቢት 01/2017 ዓ.ም. ሌሊት 10 ሰዓት አካባቢ ከእጮኛዋ ጋር ከሚኖሩበት ውዳሴ ከተሰኘው ሕንጻ 5ኛ ፎቅ በረንዳ ላይ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ መውደቋ ለኅልፈቷ ምክንያት መሆኑን ፖሊስ አመልክቷል።















