ሙዚቀኛ አንዱዓለም ጎሳ በእጮኛው ቀነኒ ሞት ተጠርጥሮ ፍርድ ቤት ቀረበ

 አንዱዓለም ጎሳ

የፎቶው ባለመብት, @AndualemGosa

ከእጮኛው ቀነኒ አዱኛ ሞት ጋር በተያያዘ ከሁለት ቀናት በፊት በቁጥጥር ስር የዋለው ሙዚቀኛው አንዱዓለም ጎሳ ፍርድ ቤት ቀረበ።

አንዱ ዓለም በግድያ ተጠርጥሮ ዛሬ፣መጋቢት 4/ 2017 ዓ.ም አራዳ በሚገኘው የፌደራል ፍርድ ቤት መቅረቡን የድምጻዊው ጠበቃ ሊበን አብዲ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዛሬ የዋለው ችሎት አንዷለም በዋስትና እንዲወጣ የቀረበውን ጥያቄ፣"በነፍስ ግድያ የተጠረጠረ በመሆኑ" ውድቅ እንዳደረገም ጠበቃው ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ሞዴል እንዲሁም የማስታወቂያ ባለሙያ የሆነችው ቀነኒ አዱኛ መጋቢት 01/2017 ዓ.ም. ሌሊት 10 ሰዓት አካባቢ ከእጮኛዋ ጋር ከሚኖሩበት ውዳሴ ከተሰኘው ሕንጻ 5ኛ ፎቅ በረንዳ ላይ ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ መውደቋ ለህልፈቷ ምክንያት መሆኑን ፖሊስ አመልክቷል።

ፖሊስ ይህንን ካለ በኋላ ማክሰኞ ዕለት መጀመሪያ ላይ እጮኛዋ ተጠርጥሮ ለምርመራ መያዙን አስታውቆ ነበር።

በዛሬው ችሎት ቀነኒ መጋቢት 1 ቀን ለሊት 10፡00 ሰዓት ገደማ ከምትኖርበት አፓርታማ አምስተኛ ፎቅ ላይ ወድቃ ህይወቷ ማለፉን ፖሊስ አስረድቷል።

"ከሱ ጋር ስለምትኖር... ጠርጥረን አስረነዋል።" ሲል ፖሊስ ደንበኛቸውን በቁጥጥር ስር ያዋለበትን ምክንያት መናገሩን ጠበቃው ገልጸዋል።

ምርመራ ለማድረግ 14 ቀናት የጠየቀው ፖሊስ እስካሁን ድረስ አሻራ ማንሳት እና የአስከሬን ምርመራ ማድረግ እንዲሁም የሰው ማስረጃ ማሰባሰብ ላይ እንዳለ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

"አሁን ለምርመራው ፎቶግራፎችን ከመዝገቡ ጋር ለማያያዝ፣የሰዎችን ምስክርነት ለመሰብሰብ እና የአስከሬን ምርመራ ውጤት እስኪመጣ ድረስ ምርመራ ለማድረግ 14 ቀናት እንጠይቃለን" ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የድምጻዊ አንዱዓለም ጠበቃ የፖሊስን ጥርጣሬ በዚህ ችሎት መቃወማቸውን ገልጸዋል።

"በመካከላቸው ምንም ችግር አልነበረም። በዚያን ቀንም በሰላም ውለው እርሷ ፎቶ ስትነሳ፣ እርሱም ከጓደኞቹ ጋር ለኮንሰርት ሲዘጋጅ ነበር። ወደ ቤት ቤት ሲገቡም በመካከላቸውም ምንም ጸብ አልነበረም። ጾም [በክርስቲያኖች ዘንድ የሚጾመው የሁዳዴ ጾም] ከተፈታ በኋላ ሽምግልና ልኮ ለመጋባት ተስማምተው ዝግጅት ላይ ነበሩ። ስለዚህ በመካከላቸው እርሷን ለመግደል የሚያበቃ ምክንያት አልነበረም" ሲሉ ጠበቃው መከራከራቸውን ገልጸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አክለውም " ፖሊስም አሁን ወድቃ ተገኘች አለ እንጂ እርሱ እንደገፈተራት የሚያሳይ ነገር ስለሌለ አሁን ባለው ሁኔታ ቀነኒ ራሷን መግደሏ እንጂ በሌላ ግለሰብ ወይንም በእኔ ደንበኛ መሞቷን አላስረዳም" በማለት በዋስትና እንዲለቀቅ መጠየቃቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በተጨማሪም አርቲስት አንዱዓለም "ቋሚ አድራሻ ስላለው እና በማንኛውም ሰዓት መቅረብ ስለሚችል እንዲሁም አሁን ሐዘን ላይ ስላለ ወጥቶ እንዲያስተዛዝን የዋስትና መብቱ እንዲጠበቅ" መጠየቃቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሆኖም ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ አድርጓል።

ፍርድ ቤቱ "በነፍስ ግድያ የተጠረጠረ በመሆኑ ለጊዜው የዋስትና ጥያቄውን አንመለከትም። የአስከሬን ምርመራ ውጤት ይምጣ። ማስረጃ ይሰብሰብ እና በቀጣይ ቀጠሮ የዋስትና ቀጠሮውን የምናይ ይሆናል" ማለቱን ጠበቃው አስረድተዋል።

በተጨማሪም አንዷለም ከእስር ቢፈታ "በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ቁጣ ስላለ እና በመጀመሪያ ችሎት የዋስ መብቱን ለመጠበቅ ትንሽ አስቸጋሪ ነው" በማለት ፍርድ ቤቱ ምላሽ መስጠቱን ጠበቃው አስረድተዋል።

በዚህም መሰረት ፖሊስ ለምርመራው ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ 13 ቀን ተፈቅዶለት ቀጣዩ ቀጠሮ ለመጋቢት 7 ቀን 2017 ተሰጥቷል።

የአርቲስት አንዱአለም ጠበቃ፣ "አብረው ስለኖሩ ለማጣራት በቁጥጥር ስር አዋሉት እንጂ፣ እርሱ ነው የገደለው ያሉት ነገር የለም። በችሎቱ እንደጠረጠሩት ተናግረዋል። ነገር ግን እሱን እንደገደለ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም" ብለዋል።

በ25 ዓመቷ ህይወቷ ያለፈው ቀነኒ የቀብር ስነ ስርዓት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ረቡዕ ዕለት ተፈጽሟል።

አንዱዓለም በትናንትናው ዕለት በቀነኒ የቀብር ስነስርዓት ላይ ከፖሊስ ጋር በመሆን መገኘቱን ቢቢሲ በስፍራው ከነበሩ ሰዎች አረጋግጧል።

የቀነኒ አባት አዱኛ ዋቆ ከቢቢሲ ኦሮምኛ ጋር ባደረጉት ልዩ ቃለ ምልልስ ልጃቸው ከፎቅ ወድቃ ሞታለች ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል።

" ደውለው ልጅቷ ከፎቅ ወድቃለች ብለው ተናገሩ። ... ልጅቱ ከፎቅ ላይ አትወድቅም። የተረጋጋች፣ ለለውጥ የምትሠራ፣ ራሷን የምትቀይር፣ ቤተሰቧን ለመለወጥ የምትሠራ ናት። ስለ ነገ ታስባለች፤ እንደዚህ አይነት ተልካሻ ነገሮችን አታደርግም"

ከቢቢሲ ኦሮምኛ ጋር በነበራቸው ቃለምልልስ ወቅት "ራሷን ከፎቅ ወረወረች የሚለው ነገር አይዋጥልኝም . . . ሰው ጎድቷት፤ እንድታደርርግ ገፋፍቷት ካልሆነ በስተቀር ካልሆነ በስተቀር" ብለዋል።

"እኛ የምንፈልገው ፍትህ ብቻ ነው። እኛ የምንፈልገው የልጃችንን ደም እንጂ ሌላ አይደለም" ሲሉም አክለው ተናግረዋል።

አስከትለውም ሆኖም አንዱዓለም እና ቀነኒ "ጥሩ ግንኙነት እንዳላቸው አውቃለሁ" ብለዋል።

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ዳሮ ላቡ ወረዳ በሚጨታ ከተማ የተወለደችው ቀነኒ ከልጅነቷ ጀምሮ በትምህርቷ ጠንካራ እንደነበረች የሕይወት ታሪኳ ያስረዳል።

በ2011 ዓ.ም ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሃይድሮሊክ እና ዋተር ኢንጅነሪንግ ተመርቃለች።

ከዚያ በኋላም በኦሮሚያ ውሃ እና ኢነርጂ ቢሮ ለተወሰነ ጊዜ ሰርታለች።

ቀነኒ በሞዴሊንግ፣ በማስታወቂያ እና በመዝናኛ ስራዎቿ ትታወቃለች።