ፖሊስ፤ ቀነኒ ክትትል ስታደርግባቸው ከነበሩ የጤና ተቋማት የሰነድ ማስረጃዎች እያሰባሰበ እንደሆነ ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, KeneniAdugna
ፖሊስ ከአንድ ወር ገደማ በፊት በ25 ዓመቷ ሕይወቷ ያለፈው ቀነኒ አዱኛ የሕክምና ክትትል ስታደርግባቸው ከነበሩ የጤና ተቋማት የሰነድ ማስረጃዎችን እያሰባሰበ መሆኑን ገለጸ።
ፖሊስ ይህንን ያስታወቀው ዛሬ፣ መጋቢት 27/2017 ዓ.ም. ለዋለው ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ነው።
በዛሬው ችሎት ሞዴል እንዲሁም የማስታወቂያ ባለሙያ የሆነችው ቀነኒ አዱኛ ሞት፣ ፖሊስ ከ15 ተጨማሪ ሰዎች መረጃ ሰብስቤያለሁ ብሏል።
ሞዴል እንዲሁም የማስታወቂያ ባለሙያ የሆነችው ቀነኒ አዱኛ መጋቢት 01/2017 ዓ.ም. ሌሊት 10 ሰዓት አካባቢ ከእጮኛዋ ጋር ከሚኖሩበት ውዳሴ ከተሰኘው ሕንጻ 5ኛ ፎቅ በረንዳ ላይ ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ መውደቋ ለህልፈቷ ምክንያት መሆኑን ፖሊስ ማመልከቱ ይታወሳል።
ከቀነኒ ሞት ጋር ተያይዞ በግድያ ተጠርጥሮ የታሰረው እጮዋ አንዷለም ጎሳ ከዚህ ቀደም በዋስትና እንዲወጣ የቀረበው ጥያቄ "በነፍስ ግድያ የተጠረጠረ በመሆኑ" ውድቅ መደረጉ ይታወሳል።
ፖሊስ ዛሬ በዋለው ችሎት ስትከታተልባቸው ከነበሩ የጤና ተቋማት ማስረጃዎች ላይ የሕክምና ባለሙያዎችን ማብራርያ እንዲሁም የሰነድ እና ሌሎች የሰው ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ ተጨማሪ የቀጠሮ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።
ፖሊስ ከዚህ በፊት የምስክርነት ቃላቸውን የተቀበላቸው 13 ሰዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ28 ሰዎች የምስክርነት ቃል መቀበሉን ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።
በተጨማሪም በሟች እና በተጠርጣሪው ስልኮች ላይ የተደረገው የምርመራ ውጤት ባለመድረሱ ተጨማሪ ቀናት እንዲፈቀድለት እንዲሁ በዛሬው ዕለት ጠይቋል።
የድምጻዊ አንዱዓለም ጎሳ ጠበቃ በበኩላቸው ፖሊስ አሁንም በተመሳሳይ ምክንያት ተጨማሪ ቀናት እየጠየቀ ነው ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
ጠበቃው አክለውም የአስከሬን ምርመራ ውጤቱ ተጎጂዋ በሕይወት እያለች ከሕንጻው ላይ ወድቃ መሞቷን እንጂ፣ ተገድላ ከሕንጻው እንደተወረወረች የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ እንደሌለ በመጥቀስ ተከራክረዋል።
በተጎጂዋ የተጻፈ ማስታወሻ ደብተር መገኘቱን የተናገሩት የድምጻዊው ጠበቃ፣ ተጎጂዋ "ለቤተሰቦቿ፣ ለዘፋኙ እና ለጓደኞቿ ራሷን ልታጠፋ እንደሆነ ጽፋለች" ብለዋል።
ጠበቃዋ አክለውም ተጎጂዋ ከዚህ ቀደም ራሷን ለማጥፋት በተደጋጋሚ መድሃኒት መውሰዷን በመጥቀስ ተከራክረዋል።
በተጨማሪም ደንበኛቸው እንደ ፌደራል ፖሊስ እና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ያሉ ተቋማትን ማስረጃ የማጥፋት አቅም ስለሌለው የዋስትና መብት እንዲፈቀድለት ጠይቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተጠርጣሪው ጠበቃ ግለሰቦች እና መገናኛ ብዙኃን በችሎቱ ያልተነገሩ ነገሮችን ዘግበዋል ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል።
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ የመገናኛ ብዙሃን የግራ እና የቀኝ ክርክርን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ከማስተላለፍ በስተቀር ሀሰተኛ እና ሚዛናዊ ያልሆኑ መረጃዎችን ከማሰራጨት እንዲቆጠቡ አስጠንቅቋል።
በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ያቀረበውን የቀጠሮ ጥያቄ እና የጠበቃውን ክርክር ለመመርመር ለመጋቢት 30/ 2017 ቀጠሮ ተሰጥቷል።
በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ዳሮ ላቡ ወረዳ በሚጨታ ከተማ የተወለደችው ቀነኒ ከልጅነቷ ጀምሮ በትምህርቷ ጠንካራ እንደነበረች የሕይወት ታሪኳ ያስረዳል።
በ2011 ዓ.ም ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሃይድሮሊክ እና ዋተር ኢንጅነሪንግ ተመርቃለች።
ከዚያ በኋላም በኦሮሚያ ውሃ እና ኢነርጂ ቢሮ ለተወሰነ ጊዜ ሰርታለች።
ቀነኒ በሞዴሊንግ፣ በማስታወቂያ እና በመዝናኛ ስራዎቿ ትታወቃለች።












