በአሜሪካ 48 በመቶ ኢትዮጵያዊያን ከመንግሥት ይወስዳሉ የተባለው ድጋፍ ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እሁድ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር ገጻቸው ላይ የ120 አገራት ከመጡ ስደተኞች መካከል ምን ያህሉ ከአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ እንደሚያገኙ ይፋ አድርገዋል።
በዚህ ዝርዝር የደቡብ እስያ አገር የሆነችው ቡታን ከ81 በመቶ በላይ ስደተኞች አሜሪካ አቅም ላነሳቸው ሰዎች የምታቀርበውን ድጋፍ (ዌልፌር) ይቀበላሉ።
ላለፉት አስር ዓመታት በእርስ በእርስ ግጭት ከምትታመሰው እና በአሜሪካ ከሚገኙ የየመን ዜጎች መካከል 75 በመቶዎቹ ድጋፉን በመቀበል በዝርዝሩ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
በቅርቡ በኢምግሬሽን እና እርዳታ ማጭበርበር በአሜሪካ ባለሥልጣናት አፍ ውሰጥ ክፉኛ ስትጠራ የሰነበተችው የሶማሊያ ስደተኞች ደግሞ 72 በመቶ ገደማ የመንግሥት ድጋፍን በመውሰድ ሦስተኛ ደረጃ እንድትይዝ አድርገዋታል።
ኑሯቸውን በአሜሪካን አገር ካደረጉ ኢትዮጵያዊያን መካከል 48 በመቶ የሚሆኑት ከመንግሥት የሚሰጠውን ድጎማ እንደሚወስዱ ፕሬዝዳንቱ ያጋሩት የአገራት እና የአሃዝ ዝርዝር ያመለክታል።
የኢትዮጵያ አጎራባች ከሆኑት ውስጥ በአሜሪካ ከሚኖሩ ኤርትራውያን መካከል 52.7 በመቶው፣ ከኬንያውያን 28.5፣ ከደቡብ ሱዳናውያን 52 በመቶ፣ ከሱዳናውያን 56.3 በመቶው የአሜሪካ መንግሥት ድጋፍን እንደሚያገኙ ተጠቅሷል።
ለመሆኑ ይህ ድጋፍ ምንድን ነው? እንዴትስ መጣ?
'ዌልፌር' ምንድን ነው?
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ሰዎች የሚደረግ ድጋፍ (ዌልፌር) በአጭሩ የአሜሪካ መንግሥት ገቢያቸው ከድህነት ወለል በታች ለሆኑ ግለሰቦች እና ለቤተሰቦቻቸው የሚሰጠው እርዳታ ነው።
መርሃ ግብሩ የጤና አገልግሎት፣ የምግብ ድጎማ፣ የቤት ድጋፍ እና ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የልጆች እንክብካቤ አገልግሎትን ያካተተ ነው።
የዚህ እርዳታ ግብ ድህነትን መቀነስ፣ ማኅበራዊ ዋስትና መስጠት እና ተጠቃሚዎች ወደ ሥራ እንዲሰማሩ በማድረግ ራስን ማስቻል ነው።
ድጋፉ ከግዛት ግዛት የሚለያይ ሲሆን፣ አብዛኛው የድጋፍ ገንዘብ ከፌደራል መንግሥቱ ለግዛቶቹ የሚከፋፈል ነው። ግዛቶቹ ደግሞ "ለተቸገሩ ሰዎች ጊዜያዊ ድጋፍ" በሚሉት የድጋፋ ማዕቀፍ ውስጥ የሚያስተላልፉት ነው።
በአሜሪካ የእርዳታ መርሃ ግብሮች ታሪክ አሻሚ እና አወዛጋቢ እንደሆነ ሚያሳዩ መረጃዎች አሉ።
በአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሊንደን ጆንሰን የፀረ ድኅነት መርሃ ግብሮችን በመቅረፅ፤ የምግብ ድጋፍ (ፉድ ስታምፕ) እና የጤና መድኅን የመሳሰሉ ድጋፎችን አስተዋውቀዋል።
ከዚያን ጊዜ ወዲህ ነው "ዌልፌር" የሚል የወል ስም የተሰጠው ድጋፍ ከዋሽንግተን ጋር የተያያዘው።
እነዚህ መርሃ ግብሮች የተቀረፁት ፕሬዝዳንቱ "በድህነት ላይ ጦርነት" ያሉትን ዘመቻ ከአሜሪካ ለማጥፋት ነበር።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን በ1969 "የቤተሰብ እገዛ ዕቅድ" በሚል ይህን መርሃ ግብር ያሻሻሉት ሲሆን፤ ሥራ መያዝን እንደ አስገዳጅነት በማስቀመጥ፤ ተጠቃሚዎች የሥራ ማበረታቻ እንዲቀርብላቸው አድርገዋል።
በ1980 ደግሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ሬገን ቤተሰብን ለማገዝ ለተቀረፁት መርሃ ግብሮች የሚውለውን የእርዳታ በጀት በመቀነስ፤ ተጠቃሚዎች ወደ ሥራ እንዲሸጋገሩ ትኩረት አድርገዋል።
በ1996 በፕሬዝዳንት ቢል ኪሊንተን የተደረገው ተጨማሪ ማሻሻያ ተጠቃሚዎች ለምን ያህል ጊዜ ድጋፍ ማግኘት እንደሚችሉ የጊዜ ገደብ በማውጣት አሠራሩን ጠበቅ አድርገዋል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በአውሮፓውያኑ 2021 የኮቪድ ወረርሽኝ በተሠራጨበት ወቅት ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሚደገፉበትን መንገድ ዳግም በጊዜያዊነት መልሰዋል።
ጊዜያዊ የገንዘብ ድጋፍ፣ የምግብ ድጋፍ፣ የቤት አቅርቦት እና ከሕፃናት እንክብካቤ አገልግሎት ባሻገር የጤና መድኅን፣ ለአካል ጉዳተኛ ሕፃናት ድጋፍ እና የግብር እፎይታንም ያካተተ ነው።
ድጋፉን ለማግኘት ብቁ የሚሆኑት እነማን ናቸው? እንዴትስ ይሰጣል?
ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው አሜሪካዊያን እና በአሜሪካ የሚኖሩ ሰዎች በመንግሥት ሙሉ ለሙሉ በጀት የሚቀርበው ድጋፍ (ዌልፌር) በቀጥታ የሚሰጥ ነው።
ድጋፉን ለማግኘት ብቁ ሆኑ ሰዎች ከመርሃ ግብር መርሃ ግብር (በገቢ ምክንያት) ቢለያይም የፌደራል መንግሥቱ ከድህነት ወለል በታች ብሎ ከሚያወጣው አሃዝ በታች ገቢ የሚያገኙ የአሜሪካ ዜጋ፣ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው እንዲሁም የስደተኛ ወረቀት የያዙ በአጠቃላይ ብቁ ናቸው።
አንዳንድ ስደተኞች ደግሞ ድጋፉን ለማግኘት ላልተወሰነ ጊዜ መጠበቅ ግድ ይላቸዋል።
ድጋፉን ለማግኘት ግን ተጠቃሚዎች በሚያመለክቱበት ግዛት መኖር አለባቸው።
ድጋፉ የሚሰጠው ለአመልካቾች የሚመደቡ ባለሙያዎች ማመልከቻውን መርምረው ብቁነታቸውን ሲያረጋግጡ ነው።
አንዳንድ የእርዳታ መርሃ ግብሮች ተጠቃሚ ለመሆን መስፈርት ያላቸው ሲሆን ዕድሜ፣ የአካል ጉዳት፣ የቤተሰብ ሁኔታ ወይም የሚፈልጉት የእርዳታ ዓይነት ወሳኝ ናቸው።
ድጋፉ እንደ ተጠቃሚው ሁኔታ እና ብቁነት ከአጭር ጊዜ በድምሩ እስከ አምስት ዓመት ድረስ ሊዘልቅ ይችላል።
ድጋፉን ለማግኘት እንደ ግዴታ አዋቂ ተጠቃሚዎች የሥራ ሥልጠና፣ ትምህርት እና ሥራ መፈለግ የመሰሉ ተግባራት ላይ መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል።















