አሜሪካ "በማርስ ወረራ" እንድትሸበር ያደረጋት የራዲዮ ፕሮግራም

ስቱዲዮ ውስጥ የሬዲዮ ፕሮግራሙ ሲቀረጽ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እአአ በ1938፣ አንድ ሳይንሳዊ ልብወለድ ለራዲዮ ስርጭት እንዲስማማ ተደርጎ ከከተረከ በኋላ በጣም ሰፊ ድንጋጤ አስነስቷል፤ ይህም በታሪክ ውስጥ እጅግ ዝነኛ ከሆኑት ስርጭቶች አንዱ ሆነ።

ከዚህ ሁሉ ጀርባ ያለው ሰው የ23 ዓመቱ ኦርሰን ዌልስ ሲሆን ከሶስት ዓመታት በኋላ ሲቲዘን ኬን ፊልም ላይ አዘጋጅ፣ ተባባሪ ጸሐፊ እና ተዋናይ ሆኖ ሰርቷል። ይህ ፊልም እስካሁን ከተሰሩ እጅግ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ፊልሞች አንዱ እንደሆነ ይታሰባል።

ስርጭቱ የተላለፈው እአአ በ1918 ተፈጥራ በ1993 የፈራረሰችው ቼኮዝሎቫኪያ በናዚ ጀርመን ከተወረረች ከአንድ ወር በኋላ ነው።

ይህ ዘመን በፋሺዝም ማነሰራራት እና በጦርነት ስጋት የተሸፈነ ዘመን ነበር።

ዌልስ እና የሜርኩሪ ቲያትር በኤችጂ ዌልስ የተጻፈውን እና "The War of the Worlds" (የዓለማት ጦርነት) የሚል ርዕስ ያለውን ከማርስ ሊመጣ ስለሚችል የወረራ ስጋት የሚገልጽ ልብ ወለድ በራዲዮ አቀረቡ።

እስከ ስድስት ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በወቅቱ አዳምጠውታል፤ ግን ብዙዎቹ ከራዲዮናቸው የሚንቆረቀረው ድምጽ የሚተርከው ልብ ወለድ መሆኑን አያውቁም ነበር።

ይህን ተከትሎም በሰዎች ዘንድ ሽብር እንዲናኝ አደረገ።

"በድንገት ሁሉም ሰው በሰዓት 210 ኪ.ሜ መንዳት ጀመረ" ሲል ኦርሰን ዌልስ በ1970 ለቢቢሲ ተናግሯል፤ ሰዎች እውነተኛ ምንነታቸው ያልታወቁ አካላት (ኤሊየንስ) ወረራ ነው ብለው ካሰቡት ነገር ለማምለጥ ወደ ኮረብታዎች እንዴት እንደሸሹ ያስታውሳል።

'የሚያናውጥ' ውርስ ትርጉም

ምንነታቸው የማይታወቁ አካላት ማሽን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እአአ በ1897 ለመጀመሪያ ጊዜ በታተመው የኤችጂ ዌልስ ልብ ወለድ ውስጥ፣ ከማርስ የሚወጡ የብረት ሲሊንደሮች በዩኬ ውስጥ በሰሪ ገጠራማ መሬት ላይ ይወድቃሉ። የብሪታንያ ጦር እነዚህን ባለ ሶስት እግር ገዳይ ጨረሮች የታጠቁ ተዋጊ ማሽኖችን ለመከላከል ተጠርቷል።

በ1938፣ ሃዋርድ ኮች የተባለ ወጣት ጸሐፊ የታሪኩን ውርስ ትርጉም የራዲዮ ትረካ ለማድረግ እየሰራ ነበር።

"ከዌልስ ልብ ወለድ የተረፈ ምንም ነገር አልነበረም፣ ስለ ፍጥረታቱ፣ ስለ መሳሪያዎቻቸው እና በእርግጥ ወረራ መኖሩን የሚገልጸው አጠቃላይ ሀሳብ" ኮች በኋላ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከዚያም፣ ድራማውን የበለጠ ቀልብ ሳቢ ለማድረግ፣ የፕሮዳክሽን ቡድኑ መቼቱን ለማሻሻል እና ከማርስ የመጡት አካላት በአሜሪካ በኒው ጀርሲ እንዲያርፉ ወሰነ።

"እንደ ሰካራም ጄኔራል ከማርስ በመጡት ወራሪዎች እና በእኛ መካከል ዘመቻ በማቀድ ትንሽ ተዝናናሁ" ሲል ኮች ያስታውሳል። "ብዙ ጊዜ አልነበረኝም፣ እና ካርታውን ዘርግቼ ዓይኖቼን ጨፍኜ እርሳሱን ስወረውረው በግሮቨርስ ሚል ላይ አረፈ።"

በኒው ጀርሲ የሚገኘው ያ ትንሽ ማህበረሰብ በራዲዮ ስርጭቱ ወቅት ከማርስ የሚመጡት ወራሪዎች ማረፊያ ተደርጎ ቀረበ።

የጋዜጣ የፊት ገጽ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የራዲዮ ፕሮግራሙ የፈጠረው ሽብር የአሜሪካ ጋዜጦች ርዕሰ አንቀጽ ሆኖ ነበር

የስርጭቱ ምሽት… ተዋናዮቹ በኒውዮርክ በሚገኝ የሬዲዮ ስቱዲዮ ውስጥ ተሰብስበው ኦርሰን ዌልስ ታሪኩን መተረክ ጀመረ።

ትርኢቱ ከተጀመረ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ፣ ሌላ የራዲዮ ፕሮግራም ሲያደምጡ የነበሩ አድማጮች ጆራቸውን ወደዚህኛው ትርኢት ቀሰሩ።

መግቢያውን አምልጧቸው የደረሱት አንድ ኦርኬስትራ ሙዚቃ ሲጫወት ነበር። ነገር ግን ሙዚቃው በተደጋጋሚ በሚነገሩ ዜናዎች ይቋረጣል።

ኦርሰን ዌልስ አድማጮቹን በእውነት ያሸበረው የትኛው ክፍል እንደሆነ ሲጠየቅ እርግጠኛ እንዳልነበረ አምኗል። "አላውቅም፤ ምናልባት ብዙ ነገሮች" ብሏል።

ከእነዚህ ብዙ ነገሮች አንዱ በስልጣን ላይ ያለው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የፍራንክሊን ዲ ሩዝቬልት ድምጽ ሊሆን ይችላል።

"የሮዝቬልትን ድምጽ በጣም ጥሩ አድርጎ ማስመሰል የሚችል ተዋናይ ነበረን" ሲል ዌልስ ያስታውሳል።

በአንድ ወቅት ተዋናዩ "የሀገሪቱ ዜጎች፣ አገሪቱን የሚያጋጥማትን ሁኔታ ክብደት ለመደበቅ አልሞክርም" ሲል ልክ ማንኛውም ፕሬዝዳንት እንደሚያደርገው አገሪቱን ለማረጋጋት ሞከረ።

ኦርሶን ዌልስ ማይክራፎን ፊት ቆሞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዌልስ ድንጋጤው በትክክል የተሰማው ያኔ እንደሆነ ያምን ነበር። "ያኔ ነው ሰዎች ወደ ጎዳናዎች የሮጡት ብዬ አስባለሁ" ብሏል።

የፕሮዳክሽን ቡድኑ ድራማውን ትክክለኛ ለማድረግ ብልህ ዘዴዎችን ተጠቅሟል። አንድ አማተር ኦፕሬተር ስለተከሰተው ስለዚህ አስከፊ ነገር ከሌሎች ሰዎች ጋር ሲነጋገር ይሰማ ነበር፤ ከዚያም ከማርስ ስለመጡት ወራሪዎች በዝርዝር የሚገልጽ የብሮድካስት ጋዜጠኛ "ጫካው ወደ ነበልባል እየተለወጠ ነው… በየቦታው እየተሰራጨ ነው… አሁን በዚህ መንገድ እየመጡ ነው።" ሲል ይደመጣል።

ከዚያም ከሁሉም በጣም የሚያስፈራው ልብ የሚያርድ ጸጥታ ተከተለ።

"ያደረግነው እውነተኛው ዘዴ ሙሉ ጸጥታ እንዲሰፍን ማድረግ ነበር፣ ምንም ድምፅ የለም" ይላል ዌልስ። "ከዚያም ማይክሮፎኑ ሲወድቅ ትሰማለህ… ከዚያም የበለጠ ጸጥታ ይሆናል።"

በመጨረሻም፣ አንድ "ሃሎ ይሰማል? ሃሎ ይሰማል?" የሚል ድምጽ ተከተለ።

ዌልስ ውጤቱን ሲያስታውስ ይስቃል "ያኔ ነው [ነዋሪዎቹ] ፎጣዎችን በራሳቸው ላይ አድርገው እግሬ አውጪኝ ያሉት። ፎጣዎችን በራሳቸው ላይ ለምን እንዳደረጉ አላውቅም - ግን አደረጉ።"

'ከማርስ በመጡት አካላት ምክንያት'

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እሁድ ምሽት ነበር፣ እና መኪኖች በሰዓት ከ200 ኪ.ሜ በላይ ሲጓዙ በሞተር ሳይክል ላይ ያሉ የትራፊክ ፖሊሶች ግራ ተጋብተዋል። "'አቁሙ' አሏቸው። 'አናቆምም' [አሽከርካሪዎቹ] መለሱ፣ 'ወደ ኮረብታዎች እሄዳለሁ' አሉ" ሲል ዌልስ ሁኔታውን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ነገር ግን ለግሮቨርስ ሚል ነዋሪዎች አስፈሪ የነበረው ይህ ክስተት አስቂኝ አልነበረም።

"ከማርስ ስለመጡ ወራሪዎች በተሰማ ቅጽበት ነበር ነገሩ አስፈሪ እየሆነ የመጣው። መሸሽ እንዳለብን ወሰንን" ሲል አንድ ነዋሪ በ1988 የቢቢሲ ቃለ ምልልስ ላይ አስታውሷል።

"ስለዚህ መኪናው ውስጥ ገባን፣ እና የኤሌክትሪክ መብራት ስላልነበረን የኬሮሲን መብራት እንደያዝን እና በስሱ ደብዘዝ አድርገን እንደለኮስነው አስታውሳለሁ። በአእምሮዬ ውስጥ በጣም ግልጽ የሆነው ትዝታ ይህንን ቦታ ተመልክቼ ለራሴ፣ 'እንደገና ወደዚህ እመለሳለሁ ወይ ብዬ አስባለሁ። ምናልባት አንድ የአርኪኦሎጂ ማህበረሰብ መጥቶ ይህንን አይቶ፣ እነዚህ ሰዎች ከማርስ በመጡ ወራሪዎች ምክንያት ሄዱ' እንደሚል አስባለሁ።"

ሌላ ነዋሪ "አንዳች ነገር" ተኩሰው ለመጣል በማሰብ ጠመንጃ እንደያዙ ተናግረዋል።

"ግሮቨርስ ሚልስ ወደሚገኘው ሐይቅ አጠገብ አቀናን። ቦታው በሰው ተሞልቶ መርፌ መጣያ እንኳን አልነበረውም። 30 ሜትር የሚረዝሙ የማርስ ወራሪዎች አይታዩም። በዚያን ጊዜ የት ሄዱ ብለን አሰብን? ለምን ያህል ጊዜ እንደቆየን አላውቅም፣ ግን ተመልሰን እንደመጣን አውቃለሁ፣ እና ሁሉም ተበሳጭቶ ነበር።"

ታዋቂው ስርጭት ትርምስ እና ጥቂት ጥቃቅን ጉዳቶችን አስከትሏል፣ ነገር ግን ከፕሮዲዩሰሮቹ አንዱ እንደገለጸው ምንም ሞት አልደረሰም። ሆኖም የአሜሪካ የፌዴራል ሕግ አውጪዎች በአየር ሞገዶች ላይ የወንጀል ወይም የአደጋ ዘገባዎችን እንዲከለክሉ አነሳስቷቸዋል።

ከድራማው ጀርባ ያለውን ቡድን በተመለከተ፣ ታሪክ መስራት ቀጠሉ። ኦርሰን ዌልስ ከሲቲዘን ኬን ጋር በሲኒማ ውስጥ ካሉት ታላላቅ ዳይሬክተሮች አንዱ ሲሆን፣ ሃዋርድ ኮች ደግሞ የሆሊውድ ብሉይ የሆነው ካዛብላንካ የፊልም ጽሁፍ ላይ አስተዋጽኦ አድርገዋል።