እርጅና እየተጫናቸው ነው የተባሉት ዶናልድ ትራምፕ 'ፍጹም' ጤነኛ መሆናቸውን ተናገሩ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጤንነታቸውን በተመለከተ በሰጡት ዘለግ ያለ ቃለ ምልልስ ሐኪሞች ከሚመክሩት በላይ አስፕሪን እንደሚወስዱ፤ በእጆቻቸው ላይ የሚደርሰውን ቁስል ለመሸፈን ሜካፕ እንደሚጠቀሙ እና "አሰልቺ" ነው ብለው ስለሚያስቡ መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንደማያደርጉ ተናግረዋል።

ትራምፕ ለዎል ስትሪት ጆርናል እንደተናገሩት በጥቅምት ወር የሲቲ ስካን እንደተደረገላቸው ገልጸዋል። በወቅቱ ዝርዝር የኤምአርአይ ምርመራ ማደረጋቸውን በስሀተት ለጋዜጠኞች ተናግረው ነበር።

የ79 ዓመቱ ትራምፕ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ከተሾሙት ፕሬዝዳንቶች በዕድሜያቸው አንጋፋው ሲሆኑ የእርጅና ምልክቶች እያሳዩ ነው። አንዳንድ ጊዜ በስብሰባዎች ላይ እንቅልፍ እንደሚወስዳቸው እና ጥያቄዎችን መስማት ሳይችሉ መቅረታቸው ታይቷል።

ዘ ጆርናል እንደዘገበው ትራምፕ "ስለ ጤንነታቸው የተፈጠረውን ክርክር በብስጭት ፍጹም [ጤነኛ ነኝ]" ሲሉ ምላሽ ሰጠዋል።

"ስለ ጤንነቴ ለ25ኛ ጊዜ እንደገና እንነጋገር" ሲሉ ጋዜጣው ስለ ትራምፕ ጤንነት ዘገባ ለመስራት ያደረገላቸውን "ያልተጠበቀ የስልክ ጥሪ" ሲጀምሩ ተናግረዋል።

"ፍጹም ጤነኛ ነኝ" ሲሉ አክለዋል።

ትራምፕ ምንም እንኳን በቀላሉ እንዲጎዱ ቢያደርጋቸውም ባለፉት 25 ዓመታት ከሚመከረው በላይ አስፕሪን እንደወሰዱ ተናግረዋል።

"አስፕሪን ደምን ለማቅጠን ጥሩ ነው ይላሉ፣ እናም ወፍራም ደም በልቤ ውስጥ እንዲፈስ አልፈልግም" ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሐኪሞች አንዳንድ ጊዜ የሚመክሩትን 81 ሚግ መጠን ከመውሰድ ይልቅ 325 ሚግ አስፕሪን በየቀኑ ይወስዳሉ።

"ትንሹን እንድወስድ ይፈልጋሉ" ሲሉ ትራምፕ አክለዋል።

ነገር ግን ከዓመታት በኋላ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የለመዱትን ነገር መቀየር አይፈልጉም። "ትንሽ የለመድኩትን የማስቀጠል አጉል እምነት አለብኝ" ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ቀደም ሲል የኤምአርአይ ስካን ነው ብለው በዋልተር ሪድ ብሔራዊ የሕክምና ማዕከል ስለተደረገላቸው የሲቲ ስካን ምርመራም ተናግረዋል።

"ኤምአርአይ አልነበረም" ሲሉ ትራምፕ "ከዚያ ያነሰ ስካን ነበር" ሲሉ ገልጸዋል።

የትራምፕ ሐኪም የሆኑት የባህር ኃይል ካፒቴን ሾን ባርባኤላ ለጋዜጣው በሰጡት መግለጫ ትራምፕ "ምንም ዓይነት የልብና የደም ቧንቧ ችግር እንደሌለባቸው ለማረጋገጥ" የሲቲ ስካን እንደተደረገላቸው እና ምርመራው ምንም ዓይነት ችግሮችን እንዳላሳየም ተናግረዋል።

ትራምፕ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ላይ የተለመደው ሥር የሰደደ የደም ሥር እጥረት እንዳለባቸው ከታወቀ በኋላ ሰውነታቸውን ጠበቅ አድርገው የሚይዙ ካልሲዎችን እንዲለብሱ ቢመከሩም ፈቃደኛ አልሆኑም።

"አልወደድኳቸውም" ሲሉ የተናገሩት ትራምፕ አሁን ከጠረጴዛቸው በተደጋጋሚ እንደሚነሱ አክለው፣ ይህም የእግሮቻቸውን እብጠት እንዳሻሻለ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ከጎልፍ ጨዋታ ውጪ ምንም ዓይነት መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግን እንደማይመርጡ ተናግረዋል።

"አልወደድኩትም። አሰልቺ ነው" ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል። "እንደ አንዳንድ ሰዎች ለሰዓታት በመሮጫ ማሽን ላይ መራመድ ወይም መሮጥ ለእኔ የሚሆን አይደለም።"

ፕሬዝዳንቱ በስብሰባዎች ወቅት አንዳንድ ጊዜ "ዘና የሚያደርግ" ሆኖ ስላገኙት ዓይኖቻቸውን እንደሚጨፍኑ ተናግረዋል። በአንዳንድ ፎቶዎች ላይ በእጆቻቸው ላይ የሚታየውን ቁስል በተመለከተ እጃቸው "ሊጎዳ" ስለሚችል ሜካፕ እንደሚይዙ ተናግረዋል።

"ለመቀባት 10 ሰከንድ ብቻ የሚወስድ ቀላል የሆነ ሜካፕ አለኝ" ብለዋል።

ትራምፕ የመስማት ችግር እንደሌለባቸው እና ፎቶ አንሺዎች እንቅልፍ ላይ እያሉ እያስመሰሉ የሚያነሱት ፎቶግራፍ "አንዳንድ ጊዜ ዓይናቸው ከድነው በሚከፍቱበት አጋጣሚ ነው" ብለዋል።

ባርቤላ ለጆርናሉ በሰጡት መግለጫ ትራምፕ "በጥሩ ጤንነት ላይ እንዳሉ እና የጦር ኃይሎች አዛዥነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ፍጹም ጤነኛ" እንደሆኑ ተናግረዋል።