ኬንያ ነርሶችን ጨምሮ 2500 የተማሩ ሠራተኞችን ወደ ሳዑዲ ልትልክ ነው

የፎቶው ባለመብት, OUH
ኬንያ ክህሎት ያላቸውን ሠራተኞችን ለሥራ ለመላክ ከሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ጋር ከስምምነት መድረሷን ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ አስታወቁ።
ሁለቱ አገራት በደረሱት ስምምነት መሠረት ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ 2ሺህ 500 የተማሩ ሠራተኞችን በመጀመሪያው ዙር ወደ ሳዑዲ እንደምትልክ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
“ከዚህ ቀደም የቤት ሠራተኞችን ነበር ስንልክ የነበረው። አሁን ግን ክህሎት ያላቸውን ሠራተኞች ወደ ሳዑዲ እና ሌሎች አገራት እንልካለን” ሲሉ ትናንት አርብ ተናግረዋል።
ዊሊያም ሩቶ ጨምረው እንደተናገሩት ወደ ሳዑዲ የሚያቀኑት ሠራተኞች በወር ሁለት መቶ ሺህ የኬንያ ሽልንግ (1ሺህ 300 ዶላር) ወርሃዊ ደሞዝ ይኖራቸዋል።
ኬንያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነርሶችን ወደ አውሮፓ እየላከች ነው ወይም ለመላክ ከመንግሥታት ጋር ስምምነት እየፈጸመች ነው።
እአአ 2021 ላይ ኬንያ ከዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ጋር በደረሰችው ስምምነት መሠረት እስካሁን ወደ 100 የሚጠጉ ኬንያዊያን ነርሶችን ወደ ዩኬ አቅንተዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ደግሞ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ለ200ሺህ ኬንያውያን የሥራ ዕድልን ለመፍጠር ለድርድር ወደ ጀርመን አቅንተው ነበር።
ፕሬዝዳንቱ በዓለም ላይ በጠንካራ ሠራተኝነታቸው መልካም ስም ላላቸው ዜጎቻቸው የሥራ ዕድልን ለመፍጠር አማራጮችን ሲያጤኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከዚህ ቀደም የአገሪቱ ዜጎች በውጪ አገራት የሥራ ዕድሎችን በመፈለግ ወደ አገር ቤት የውጭ ምንዛሬ እንዲልኩ እንዲሁም በአገሪቱ ያለውን የሥራ አጥ ቁጥር እንዲቀንሱ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረው ነበር።
በቅርቡም ኬንያ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን በእርሻ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ወደ እስራኤል እንደምትልክ አስታውቃ ነበር።
እስራኤል ከሐማስ ጋር ግጭት ውስጥ መግባቷን ተከትሎ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞች አገሪቱን ጥለው ወጥተዋል። አንዳንድ አሃዞች እንደሚጠቁሙት አብዛኛዎቹ ታይላንዳውያን የሆኑ ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ ስደተኛ የጉልበት ሠራተኞች እስራኤልን ጥለው ወጥተዋል።
በዚህም የተነሳ እስራኤል የጉልበት ሠራተኛ ፍላጋ ፊቷን ወደ አፍሪካ ያዞረች ሲሆን የኬንያ የሠራተኛ ሚንስቴር ከእስራኤል መንግሥት ጋር በደረሰው ስምምነት ለእርሻ ሥራ የሚሄዱት ዜጎች በየሦስት ዓመቱ በሚታደስ ውል በየወሩ የተጣራ 1ሺህ 500 የአሜሪካ ዶላር እየተከፈላቸው እንዲሰሩ ከስምምነት ተደርሷል ብሏል።












