ዶናልድ ትራምፕ የሪፐብሊካን ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ለመሆን ኒኪ ሄሊን በግዛታቸው አሸነፉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዶናልድ ትራምፕ በደቡብ ካሮላይና ኒኪ ሄሊ ላይ ትልቅ ድል ካስመዘገቡ በኋላ የሪፐብሊካን ፓርቲ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ለመሆን አንድ እርምጃ መቃረባቸው ተሰምቷል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ተቀናቃኞቻቸውን በግዛታቸው በ20 ነጥብ ልዩነት አሸንፈዋል። ይህም አራተኛ ተከታታይ ድላቸው ሆኖ ተመዝግቧል።
ትራምፕ ድላቸውን ባበሰሩበት ወቅት ስለተቀናቃኛቸው ምንም አስተያየት አልሰጡም። ይልቁንም በሚቀጥለው ዓመት ኅዳር ወር በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ትኩረት አድረገዋል።
“ጆ ባይደን ጋር ፊት ለፊት እንገናኛለን። አገራችንን እያፈራረሰ ነው። እኛ ደግሞ ‘ጆ ውጣ፣ ተባረሃል’ ልንል ነው” ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።
ትራምፕ ከቅዳሜው ውጤት በኋላ የፓርቲያቸውን “አንድነት” አድንቀዋል፤ “እንዲህ ያለ መንፈስ አልነበረም፣ የሪፐብሊካን ፓርቲ ይህን የመሰለ አንድነት ሲኖረው አይቼ አላውቅም” ብለዋል።
ትራምፕ ባለፈው ወር በኒው ሃምፕሻየር የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ለመሆን ከተደረገው ውድድር በኋላ ሄሊ “ያደረገችው ንግግር ያሸነፈች የሚያስመስላት ነው” ካሉበት ተቀይሯል ተብሏል።
በአንድ ወቅት የደቡብ ካሮላይና ገዢ ሆነው ያገለገሉት ሄሊ ተቀናቃኛቸውን ስላስመዘገቡት ድል እንኳን ደስ አልዎት ብለዋል።
በውድድሩ ለመቀጠል ቃል ከመግባት ባለፈ ያገኘኙት 40 በመቶ ድምጽ “ጥቂት አይደለም” ሲሉም ተናግረዋል።
“በሪፐብሊካን የዕጩዎች ምርጫ አማራጭ እንፈልጋለን የሚሉ እጅግ በጣም ብዙ መራጮች አሉ” በማለት ተሳትፏቸው የራሳቸው የፖለቲካ ፍላጎት ብቻ እንዳልሆነ አጽንዖት ሰጥተው ሄሊ ተናግረዋል።
“አብዛኞቹ አሜሪካውያን ዶናልድ ትራምፕን እና ጆ ባይደንን በሚቃወሙበት በዚህ ወቅት ይህንን ፉክክር አልተውኩትም” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የትራምፕ ቡድን ቅዳሜ ዕለት በሰጠው መግለጫ “ግራ መጋባት ውሳኔዋን እያየጋረደባት ነው። እውነታውን እየኖረች አይደለም” በማለት የሄሊን በውድድሩ የመቆየት ጥረት ውድቅ አድርጎታል።
ቡድኑ የቀድሞው ፕሬዝዳንት በሚቀጥለው የፈረንጆች ወር ዕጩ ሆነው ለመጨረስ በቂ ድምጽ እንደሚያገኙ ተንብዮ ነበር።
ሄሊ ግልጽ ዕቅድ ያላቸው አይመስልም። ተቀናቃኛቸው በከፍተኛ ድምጽ ከመምራታቸውም በላይ በቀጣይ ውድድሮችም ቀዳሚ እንደሚሆኑ ግምቶች አሉ።
የሄሊ የምርጫ ዘመቻ አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን፣ ይህም በአብዛኛው ለጋሾች ባደረጉት አስተዋፅዖ ነው ተብሏል። ብዙ መሰናከሎች ቢገጥሟቸውም የሚያገኙት ገንዘብ ቀጥሏል።
ሄሊ በጥር ወር ብቻ 16.5 ሚሊዮን ዶላር ሰብስበዋል ሲሉ የምርጫ ዘመቻ ባለሥልጣናት ተናግረዋል። ይህም እስካሁን ካገኙት ትልቁ ወርሃዊ ድጋፍ ሲሆን፣ ከትራምፕ ቁጥሮችም የበለጠ ነው።
ትራምፕ ውድድሩ ከተደረገ በኋላ ንግግራቸውን ለማድረግ ጊዜ አላጠፉም። በዚህም ሄሊ በኒው ሃምፕሻየር እንዳደረጉት ቀድመዋቸው ሃሳባቸውን እንዳያካፍሉ አድርገዋል።
ትራምፕ አብዛኞቹ የግዛቲቱ የፖለቲካ መሪዎችን ጨምሮ ከሃያ በላይ በሚሆኑ አጋሮቻቸው ተከበው “ይህ ከምንጠብቀው በላይ ትንሽ ፈጥኗል” ብለዋል።
ትራምፕ በዚህ ድል ምክያት ብዙ የሚኮሩበት ነገር አላቸው ተብሏል። በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ውጤት እንደሚያሳየው የቀድሞው ፕሬዝዳንት በወንዶች እና በሴቶች እንዲሁም በሁሉም የዕድሜ ክልል በሚገኙ ሰዎች የበላይነት ይዘዋል።
ለድጋፋቸው ያመሰገኑት የ77 ዓመቱ ትራምፕ ታዳሚዎቻቸውን “ከፊታችን ብዙ ሥራዎች አሉን” ሲሉ አስታውሰዋል።
ይህም ሆኖ ሙሉ ለሙሉ ፊታቸውን ወደ ጠቅላላ ምርጫው ማዞር የሚችሉ አይመስሉም።
ሄሊ ቢያንስ በ16 ግዛቶች ውስጥ ያሉ መራጮች በተመሳሳይ ቀን ድምጻቸውን እስከሚሰጡበት ውድድር ድረስ ለመቆየት ቃል ገብተዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ የቀድሞ አምባሳደር የነበሩት ሄሊ “እኔ በቃሌ የምገኝ ሴት ነኝ። ቀጥለን ወደ ሚሺጋን እያመራን ነው። እና በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ ወደ 16ቱ ግዛቶች ምርጫ እናመራለን" ብለዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት በበርካታ ጉዳዮች ተከሰው ፍርድ ቤት እየተመላለሱ ነው።
ትራምፕ በጾታዊ ጥቃት እና በስም ማትፋት ተከሰው ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሆነ ገንዘብ እንዲከፍሉ የተፈርዶባቸዋል።
በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ በጣም ውድ በሆነው ፕሬዚዳንታዊ ውድድር ላይ ፕሬዝዳንት ባይደን ከፍተኛ ገንዘብ አሰባስበዋል። ትራምፕ እየጨመረ የመጣውን የሕግ ወጪያቸውን ለመሸፈን በሚያገኙት ልገሳ ላይ ተንጠልጥለዋል።
ሪፐብሊካን ፓርቲ ትራምፕን እንደሚደግፋቸው ይጠበቃል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images












