የሴኔጋል ባሕር ኃይል ሦስት ሺህ ኪሎ ግራም ኮኬይን በቁጥጥር ስር አዋለ

ሦስት ቶን የሚመዝን ኮኬይን ጭና የተያዘችው መርከብ

የፎቶው ባለመብት, DIRPA/X

የምስሉ መግለጫ, ሦስት ቶን የሚመዝን ኮኬይን ጭና የተያዘችው መርከብ

የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ሴኔጋል ባሕር ኃይል ሦስት ሺህ ኪሎ ግራም የሚጠጋ ኮኬይን የተባለውን አደንዛዥ ዕጽ የጫነችን መርከብ ከአገሪቱ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ መያዙን አስታወቀ።

ይህ ሦስት ቶን የሚመዝነው የዕጽ ሲያዝ በሴኔጋል ባሕር ኃይል ታሪክ በጣም ከፍተኛ መጠን ያለው ነው ተብሏል።

አካባቢው የላቲን አሜሪካ የዕጽ አዘዋዋሪዎች ወደ አውሮፓ እና ወደ ሌሎችም አካባቢዎች ሕገወጥ ዕጾችን ለማሸጋገር የሚጠቀሙበት ነው።

የሴኔጋል ባሕር ኃይል በመርከቧ ላይ 10 ሰዎች መያዙን እና ከመካከላቸውም አንደኛው የሴኔጋል ዜጋ መሆኑን ከመግለጽ ውጪ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥቧል።

ዕጹን ጭና የነበረችው መርከብ ከሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር የባሕር ዳርቻ 105 ኪሎ ሜትሮች ርቆ ከሚገኘው የዓለም አቀፍ የውሃ ክልል ውስጥ ስትቀዝፍ ነበር በባሕር ኃይሉ የተያዘችው።

ትናንት ማክሰኞ የተያዘችው መርከብ የተያዘባትን ዕጽ አይነት እና መጠንን “ለመለየት እንዲሁም ለመመዝገብ” ወደ ባሕር ኃይሉ መደብ መወሰዷ ተገልጿል።

ቢሆንም ግን ከፍተኛ መጠን ያለውን ዕጽ የጫነችው መርከብ ባለቤት ማን እንደሆነ፣ መነሻዋ ከየት እንደሆነ እና ከአንደኛው ሴኔጋላዊ ውጪ የተያዙት ሰዎች ማንነት እና ዜግነት አልተገለጸም።

ባሕር ኃይሉ በኤክስ ገጹ ላይ ባሰራጨው ፎቶ ላይ ከባሕር ዳርቻ ላይ የቆመች የዛገች መርከብ፣ የተያዘባት ጭነት እና የባሕር ኃይል መኮንኖች በዙሪያዋ ሆነው አሳይቷል።

ነገር ግን ባሕር ኃይሉ ከመርከቧ የዕጽ ጭነት ጋር የተያዙት አስር ሰዎች ላይ ክስ ተመሥርቶባቸው እንደሆነ ያለው ነገር የለም።

ባለፈው ዓመት ጥር ላይ ከሴኔጋል የባሕር ዳርቻ ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ ላይ ስትቀዝፍ የነበረች አንዲት መርከብ ላይ ከ800 ኪሎ ግራም በላይ የኮኬይን ዕጽ ተይዞ ነበር።

ከሦስት ዓመታት በፊት ደግሞ ከደቡብ አሜሪካዊቷ ብራዚል የተነሳች ናት በተባለች መርከብ ላይ በተጫኑ መኪኖች ውስጥ ተደብቆ የነበረ 750 ኪሎ ግራም ኮኬይን መያዙ ተገልጿል።

የተያዘው ሕገወጥ ዕጽ ወደ ተለያዩ አገራት ሊሻጋገር የነበረ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ የአውሮፓ አገራት ይገኙበት እንደነበር ተገልጿል።