የኬንያ ፓርላማ በአገሪቱ ፕሬዝዳንት የሚዘወተረውን ልብስ በምክር ቤቱ እንዳይለበስ አገደ

የፎቶው ባለመብት, PRESIDENCY KENYA/X
በሟቹ የዛምቢያ ፕሬዝዳንት ኬኔት ካውንዳ የተሰየመው ልብስ ምክር ቤቱ ውስጥ እንዳይለበስ የኬንያ ፓርላማ አገደው።
የፓርላማ አፈ-ጉባዔ ሞሰስ ዌታንጉላ እንደገለጹት የካውንዳ ሱፍንም ሆነ የአፍሪካዊያንን ባህላዊ አልባሳት መልበስ አይፈቀድም።
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በይፋዊ ሥነ-ሰርዓቶች ላይ ብዙ ጊዜ ይህን ልብስ ለብሰው ይታያሉ።
የቀድሞ የዛምቢያ ፕሬዝዳንት ኬኔት ካውንዳን ይህን ልብስ ማዘውተራቸው ልብሱ በእርሳቸው ስም ከመሰየሙም በተጨማሪ በፖለቲከኞች ዘንድ ተወዳጅ እንዲሆን አድርጎታል።
ይህ አለባበስ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ መሪዎች ዘንድ ተወዳጅ ለመሆን በቅቷል።
የማኦ ዜዱንግ ሱፍ እየተባለም የሚጠራው ሱፍ ኮሌታ አልባ ሲሆን ብዙ ጊዜም እጅጌ ጉርድ ነው።
አፈ ጉባኤ ዌታንጉላ ልብሱን ለማገድ የወሰኑት ካውንዳ ፋሽን የመሆን አዝማሚያ በማሳየቱ እና የፓርላማ የአለባበስ ስነ-ሰርዓትን አደጋ ላይ በመጣሉ ነው ብለዋል።
ለወንዶች ትክክለኛው የአለባበስ ሥርዓት “ኮት፣ ክራቫት፣ ረጅም-እጅጌ ያለው ሸሚዝ፣ ረጅም ሱሪ፣ ካልሲ፣ ጫማ ወይም ወታደራዊ የደንብ ልበሶች ነው” ብለዋል።
"ለሴቶች ደግሞ መደበኛ ወይም ጥሩ ልብሶች ይሆናሉ። ቀሚሶች ከጉልበት በታች የሚረዝሙ እና ጨዋነት ያላቸው መሆን አለባቸው። እጅጌ የሌላቸው ሸሚዞች የተከለከሉ ናቸው" ብለዋል።
ቀደም ሲል ካውንዳ በፓርላማው ይፈቀድ የነበረ ሲሆን አንዳንድ የፓርላማ አባላትም ይህን ልብስ አዘውትረው በመልበስ ይታወቃሉ።
ዌታንጉላ አክለውም እነዚህን ልብሶች ከዚህ ቀደም “ታግሰው” እንደነበር አስረድተው፤ አሁን ግን በፓርላማ የአለባበስ ደንብ ላይ ስጋት በመፈጠሩ ለማስቆም ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ሩቶ በኦፊሴላዊ ዝግጅቶች ላይ ለብሰው መታየታቸውን ተከትሎ ካውንዳ በኬንያ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በስፋት እየታየ ነው።
እገዳው በማህበራዊ ሚዲያ የተለያዩ አስተያየቶች እንዲሰጡ ምክንያት ሆኗል። አንዳንዶች ለምን "የአፍሪካውያን አለባበስ" በአፍሪካዊቷ አገር ፓርላማ ይታገዳል በማለት ሲጠይቁ ሌሎች ደግሞ ውሳኔውን ደግፈውታል።
አንዳንዶች ደግሞ የካውንዳ ልብስ ለፕሬዚዳንቱ ብቻ የተተወ እንዲሆን ያደረገ ውሳኔ ሲሉ እገዳውን ተሳልቀውበታል።












