የዳይኖሰር ቅሪተ አካል ለጨረታ ቀርቦ በ 44.6 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአንድ ትልቅ የዳይኖሰር ቅሪተ አካል በኒውዮርክ ከተማ በሶቴቢ የጨረታ ተቋም ለጨረታ ቀርቦ በ 44.6 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠ።
ዋጋው ለአንድ ቅሪተ አካል የተከፈለ ከፍተኛ ዋጋ ነው ተብሏል።
እፅዋትን ይመገብ የነበረው ዳይኖሰር አፔክስ የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶታል።
አፔክስ 3.4 ሜትር ቁመት እና ከአፍንጫው እስከ ጭራው ደግሞ 8.22 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን "እስከ ዛሬ ከተገኙት የተሟሉ ቅሪተ አካሎች መካከል የተሟላ ደረጃ ላይ ይገኛል" ሲል የጨረታ አቅራቢው ተናግሯል።
“አፔክስ አሜሪካ ውስጥ የተወለደ በመሆኑ አሜሪካ ውስጥ ሊቆይ ነው” ሲል ማንነታቸው ያልተጠቀሰ ገዥ ተናግረዋል።
ለአሜሪካ ተቋም በውሰት ሊሰጥ እንደሚችል ፍንጭ ተደርጎ ታይቷል።
አፔክስ በአውሮፓውያኑ 2022 በአንድ ፓሊዮንቶሎጂስት በአጋጣሚ የተገኘው በምዕራብ አሜሪካዋ ኮሎራዶ ግዛት ውስጥ የዳይኖሰር ከተማ በሚባለው ቦታ አቅራቢያ ነው።
“ለጨረታ የቀረበው አፔክስ ዛሬ በ44.6 ሚሊዮን ዶላር በመሸጥ ታሪክ የሠራ ቅሪተ አካል ሆኗል" ሲል ድርጅቱ በመግለጫው ተናግሯል።
ቅሪተ አካሉ ከሽያጭ በፊት ከነበረው ግምት በ11 እጥፍ በልጦ መሸጡንም የጨረታ ተቋሙ አስታውቋል።
እስካሁን ከተገኘው ትልቁ ነው ለተባለው የዳይኖሰር ቅሪተ አካል ሰባት ገዥዎች በጨረታው ሂደት ተሳትፈዋል።
አፔክስ የተገኘው ጄሰን ኩፐር በተባሉ ቅሪተ አካል አዳኝ ነው።
አፔክስ ከ 150 ሚሊዮን ዓመታት በፊት በኋለኛው የጁራሲክ ዘመን እንደኖረ ላይ ይታመናል።
የቀድሞው የዳይኖሰር ቅሪተ አካል ሽያጭ ክብረወሰን በአውሮፓውያኑ 2020 የተሸጠው እና 31.8 ሚሊዮን ዶላር ያስገኘው ነበር።












