ከባድ ቅዝቃዜ እና ጥቅጥቅ ደመና ሕንድ ውስጥ እንቅስቃሴዎችን አስተጓጎለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሰሜናዊ ሕንድ በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው ከባድ ቅዝቃዜ የነዋሪዎችን መደበኛ የዕለት ከዕለት ሕይወት ማስተጓጎሉ ተነገረ።
በአካባቢው በተከሰተው ጥቅጥቅ ደመና የተነሳም ከአንድ መቶ በላይ በረራዎች እና በርካታ የባቡር ጉዞዎች እንዲዘገዩ በመደረጋቸው፣ በአየር ማረፊያዎች እና በባቡር ጣቢያዎች ከፍተኛ ግርግር ተፈጥሯል።
በሕንድ ዋና ከተማ ዴልሂ ያሉ ባለሥልጣናትም ለእረፍት የተዘጉት የአገሪቱ ትምህርት ቤቶች የእረፍት ጊዜውን እንዲያራዝሙ እና እየተካሄዱ ያሉ ትምህርቶች ለጊዜው እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
ትናንት እሁድ በዋና ከተማዋ ባሉ አንዳንድ ክፍሎች ውስጥ ያለው ዝቅተኛው የሙቀት መጠን ወደ 1.9 ሴሊሺየስ አሽቆልቁሏል።
ሌሎች የሕንድ ሰሜናዊ ግዛቶችም በከባድ ቅዝቃዜ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ በሕንድ ስር በምትተዳደረው የካሽሚር ግዛት ውስጥ ያለው ቅዝቃዜ ከዜሮ በታች -6 ሴሊሺየስ ሆኗል።
የሕንድ የአየር ሁኔታ መከታተያ መሥሪያ ቤት እንደሚለው የአየር ሙቀት መጠኑ ከ4 ሴሊሺየስ በታች ከሆነ ከባድ የቅዝቃዜ ሁኔታ ሊባል እንደሚችል ገልጿል።
የአየር ሁኔታን የሚከታተለው ተቋም እንደሚለው አሁን ያለው የቅዝቃዜ ሁኔታ አስኪስተካከል ድረስ ነዋሪዎች “ከቤት ውጪ እንዳይንቀሳቀሱ ወይም እንቅስቃሴያቸውን የተወሰነ እንዲያደርጉ” መክሯል።
በተጨማሪም ጥቅጥቅ ያለ ጭጋግ በሚሆንበት ጊዜ አሽከርካሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስጠንቅቋል።
ይህ ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ በአሁኑ ወቅት ከባድ የአየር ብክለት ባለባት በዋና ከተማዋ ዴልሂ ውስጥ በሚገኙ ነዋሪዎች ላይ ከባድ የጤና ችግርን ሊያስከትል ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
በጣም ከፍተኛ የሆነው ቅዝቃዜ በተለይ በመንገድ ዳር እና በባቡር ጣቢያዎች ውስጥ ተጠልለው ለሚኖሩ ቤት አልባ ሰዎች ከባድ ይሆናል ተብሏል።
እሁድ ዕለት ዴልሂ ከተማ በዚህ ወቅቱ አስካሁን አጋጥሟት የማያውቅ ጭጋጋማ ቀን ሆኖ ነበር። ለበርካታ ሰዓታት ጥቅጥቅ ጭጋግ ከተማዋን ሸፍኗት ቆይቷል።
ጭጋጉ በከተማዋ ያለውን ሁኔታ ለመመልከት አስቸጋሪ በማድረጉ የተነሳ ከአንድ መቶ በላይ ከዴልሂ የሚነሱ በረራዎች እንዲዘገዩ የተደረጉ ሲሆን፣ በርካታ አውሮፕላኖች ደግሞ ለማረፍ ባለመቻላቸው ወደ ሌሎች ቦታዎች እንዲሄዱ ተገደዋል።
በየዕለቱ 23 ሚሊዮን ሰዎችን የሚያጓጉዘው የሕንድ የባቡር አገልግሎት እንዳለው፣ ባለው የአየር ሁኔታ ምክንያት በሰሜናዊ ሕንድ 29 ባቡሮች እንዲዘገዩ ተደርገዋል።
ጭጋጋማው ሁኔታ ዛሬ ሰኞም ባለበት የቀጠለ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት ዴልሂ ውስጥ ተሽከርካሪዎች ዝግ ብለው ሲጓዙ ታይተዋል።
የአገር ውስጥ የበረራ አገልግሎት የሚሰጠው “ኢንዲጎ” የተባለው አየር መንግድ በትዊተር ገጹ ላይ፣ ዴልሂ ውስጥ ያለው “ጭጋጋማው ሁኔታ ዕይታን አስቸጋሪ” ስላደረገው የበረራ ጊዜ ላይ ለውጥ እንደሚኖር እና ተጓዦች ወደ አየር ማሪፊያ ከማቅናታቸው በፊት ለውጦችን እንዲያጣሩ መክሯል።












