በብራዚል አክራሪ የቦልሶናሮ ነውጠኛ ደጋፊዎች ፓርላማውን ተቆጣጠሩ

በብራዚል አመጸኞቹ በዋና ከተማዋ የሚገኙ ቁልፍ መንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ተቆጣጥሯል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በብራዚል አመጸኞቹ በዋና ከተማዋ የሚገኙ ቁልፍ መንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ተቆጣጥረዋል

በቅርቡ ተሸንፈው ሥልጣን የለቀቁት የቦልሶናሮ አክራሪ ደጋፊዎች ናቸው የተባሉ በሺህ የሚቆጠሩ ብራዚላዊያን ነውጥ በመፍጠር የአገሪቱን ፓርላማ ጥሰው ገቡ።

ነውጠኞቹ ትናንት ቀትር ላይ ቁልፍ የዴሞክራሲ ምሶሶ ናቸው ወደሚባሉት የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የአገሪቱ ፓርላማና ሌሎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በማቅናት ቅጥሩን በኃይል በመጣስ ተቆጣጥረዋል፤ ንብረት አውድመዋል።

የአገሪቱን ቤተ መንግሥትን ደግሞ በቅርብ ርቀት በመክበብ ከፍተኛ ነውጥ አስነስተዋል።

ይህ ድርጊት በጃንዋሪ 6፣ 2020 ዓ/ም የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች የፈጸሙትን ድርጊት አርአያ በማድረግ የተፈጸመ የአክራሪ ነውጠኞች ተግባር ነው ተብሏል።

ዶናልድ ትራምፕ ከሁለት ዓመት በፊት በጆ ባይደን መሸነፋቸውን ባለማመናቸው ደጋፊዎቻቸው አመጽ እንዲቀሰቅሱና ኮንግረስን እንዲቆጣጠሩ አበረታተዋል በሚል በኮንግረስ አባላት የተዋቀረ አጣሪ ኮሚቴ ጥፋተኛ መባላቸው አይዘነጋም።

የብራዚሉ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዣየር ቦልሶናሮ ደጋፊዎቻቸው ይህን አመጽ በሚቀሰቀስበት ወቅት አሜሪካ ነበሩ።

ዋሽንግተን ፖስት በጻፈው ልዩ ዘገባ ደግሞ የቦልሶናሮ ወንድ ልጅ ኤድዋርዶ በኅዳር ወር ከትራምፕ አማካሪዎች ጃሰን ሚለር እና ስቲቭ ባነን ጋር መገናኘቱን እና ምናልባትም የነውጥ ሐሳቡ የተጎነጎነው ያን ጊዜ ሳይሆን እንደማይቀር ጠቁሟል።

የአክራሪ አመጾች ሸራቢ የሚባሉት ስቲቭ ባነን የሉላ ዳ ሲልቫ ፕሬዝዳንት ሆኖ መመረጥ ተቀባይነት እንደሌለው በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ለተከታታይ ጊዜ ሲጽፉ ቆይተዋል።

ዣየር ቦልሶናሮም ከተሸነፉ በኋላ በሉላ ዲ ሲልቫ በዓለ ሲመት ላለመገኘት በሚል ወዲያውኑ ወደ አሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት አቅንተው እዚያ እየኖሩ ነው።

ዶናልድ ትራምፕ መኖርያ ቤታቸው በዚያ ግዛት እንደሆነ ይታወቃል። ሁለቱ የቀድሞ መሪዎች በፍሎሪዳ የትራምፕ ቤት ‘ሻይ ቡና’ ማለታቸውም ተዘግቦ ነበር።

የዶናልድ ትራምፕ ሶሻል ሚዲያ የሆነው ‘ትሩዝ ሶሻል’ የዶናልድ ትራምፕ ቁልፍ ደጋፊዎች “ነውጡን ግፉበት! ማድረግ ያለባችሁንም አድርጉ! በርቱልን” ሲሉ ለአመጸኞቹ የብርታት መልእክት ሲልኩ ነበር።

ትናንት እሑድ በተቀሰቀሰው ነውጥ በሺህ የሚቆጠሩት የዣየር ቦልሶናሮ ደጋፊዎች ከወታደራዊ እዝ ጣቢያዎች ደጅ በመሆን ድምጻቸውን ሲያሰሙ ነበር።

ይህን ያደረጉትም ወታደሩ መፈንቅለ መንግሥት እንዲያደርግ ለማበረታታት ነው።

የቦልሶናሮ ደጋፊዎች መሪያቸው በፕሬዝዳንት ሉላ ከተሸነፉ ጀምሮ መከላከያ ሠራዊት አገሪቱን እንዲቆጣጠርና መፈንቅለ መንግሥት እንዲያደርግ ሲጠይቁ ነው የቆዩት።

የዶናልድ ትራምፕ አምሳያ ናቸው የሚባሉት ዣየር ቦልሶናሮ ‘የትሮፒካሉ ትራምፕ’ የሚል ቅጽል ስም የተሰጣቸውም ለዚሁ ነው።

ትራምፕና ቦልሶናሮ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ይባላሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ትራምፕና ቦልሶናሮ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ይባላሉ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዣየር ቦልሶናሮ የለየላቸው አክራሪ ብሔርተኛ ሲሆኑ በኮቪድ ወረርሽኝ ጊዜ ከግማሽ ሚሊዯን የሚልቁ ብራዚላዊያን በተህዋሲው ተይዘው ሲሞቱ እርሳቸው ግን ሕይወት እንደ ቀድሞው እንዲቀጥል ሲወተውቱ ነበር።

ክትባትንም አያበረታቱም።

ዣየር ቦልሶናሮ በቅርብ በተደረገ ምርጫ በግራ ዘመሙ የቀድሞ መሪ ሉላ ዳ ሲልቫ በጠባብ ልዩነት መሸነፋቸው አይዘነጋም።

ሉላ ዳ ሲልቫ ብራዚልን በፕሬዝዳንትነት ከመሩ በኋላ የሙስኛ ክስ ተመስርቶባቸው እስር ቤት ነበሩ። በኋላ ግን በነጻ ተለቀው በድጋሚ ለፕሬዝዳንትነት ተወዳድረው አሸንፈዋል።

ከ200 ሚሊዮን የሚልቀው የብራዚል ሕዝብ ከምንጊዜውም በላይ በፖለቲካ አመለካከቱ ተከፋፍሎ ይገኛል።

ይህን ነውጥ ተከትሎም ግራ ዘመም የሉላ ደጋፊዎች አገሪቱን የሚያንቀጠቅጥ የድጋፍ ሰልፍ እናደርጋለን በሚል ዝግጅት መጀመራቸው ተሰምቷል።

ይህ የነውጠኞች ተግባር በቀጠለበት ወቅት ሪዮ በጉብኝት ላይ የነበሩት ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት በመግባት ይህ ተግባር ላይ የተሳተፉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ውለው ጥብቅ ቅጣት እንደሚሰጣቸው ቃል ገብተዋል።

በዋና ከተማዋ ፕራዚሊያም ፖሊስ በሙሉ ኃይል ወጥቶ ሰላምና ጸጥታ እንዲያሰፍን ጠይቀዋል።

ሉላ ፖሊስ ነውጠኞቹን ለመቆጣጠር ያሳየውን ዳተኝነት ክፉና ኮንነዋል።

ነውጠኞቹን “የፋሺስት ርዝራዦች’ ሲሉ የጠሯቸው ሲሆን ‘እነዚህ ፋሺስቶች በብራዚል ታሪክ ሆኖ የማያውቅ ነውር ፈጽመዋል፤ የእጃቸውን ያገኛሉ ሲሉ በተደጋጋሚ ዝተዋል።

ይህን ነውጥ ተከትሎ የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የብራዚሊያን ከተማን ገዥ ኢባኒየስ ሮቻን ከሥልጣናቸው አንስቷል።

እርምጃው የተወሰደው ነውጠኞቹን ለማስቆም የወሰዱት እርምጃ የለም በሚል ነው።

ነውጠኞቹ ፍርድ ቤቶችና ፓርላማ ጥሰው ከገቡ በኋላ መስታወቶችን ሰባብረዋል፤ በሮችንም ገነጣጥለዋል።

እስከ አሁን በመቶዎች የሚቆጠሩ በነውጡ የተሳተፉ ዜጎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

አመጹ ለስድስት ሰዓታት ከዘለቀ በኋላ ዣየር ቦልሶናሮ በትዊተር ብቅ ብለው ድርጊቱን ኮንነዋል።

ይህ በብራዚል የተፈጸመው ተግባር ጆ ባይደንን ጨምሮ በበርካታ የዓለም መሪዎች እየተኮነነ ነው።