ህንዳዊው የ13 ብር የባቡር ቲኬት ጭማሬ ከ22 አመት የፍርድ ቤት ክርክር በኋላ አሸነፈ

ህንዳዊው በባቡር ቲኬት ላይ የተጣለበትን የዋጋ ጭማሬ በመቃወም ከ22 አመት የፍርድ ቤት ክርክር በኋላ አሸነፈ።
በሙያው ጠበቃ የሆነው ቱንኛት ቻቱርቬዲ ከ22 አመት በፊት ለገዛቸው ሁለት የባቡር ቲኬቶች ተጨማሪ 20 ሩፒ (13 ብር) እንዲከፍል በመደረጉም ነበር የከሰሰው።
ይህ ክስተት የተፈጠረው በሰሜናዊ ህንድ ኡታር ፕራዴሽ ግዛት ማቱራ ካንቶንመንት የባቡር ጣቢያ ነው።
የሸማቾች ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ለጠበቃ ቱንኛት ቻቱርቬዲ የፈረደለት ሲሆን የባቡር ጣቢያው ገንዘቡን እስከ ወለዱ እንዲመልስከለትም ብያኔ ተላልፏል።
“ከዚህ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ከ100 በላይ ችሎቶችን ተካፍያለሁ” ሲ የ66 አመቱ ቱንኛት ለቢቢሲ ተናግሯል።
አክሎም “ነገር ግን ይህንን ጉዳይ ለመታገል ያወጣሁትን ጉልበትና ያባከንኩትን ጊዜ በዋጋ መተመን አይችሉም” ብሏል።
በህንድ ውስጥ ያለው የሸማቾች ፍርድ ቤቶች በተለይ ከአገልግሎቶች ጋር የተያያዙ ቅሬታዎችን ያስተናግዳሉ። ነገር ግን በርካታ ቅሬታዎችን ስለሚያስተናግዱ መደራረብና ጫና ስለሚበዛ አንዳንድ ጊዜ ቀላል ጉዳዮችን እንኳን ለመፍታት አመታት ሊወስድ ይችላል።
በኡታር ፕራዴሽ ይኖር የነበረው ቻቱርቬዲ ከማቱራ ወደ ሞራዳባድ በመጓዝ ላይ እያለ አንድ የባቡር ቲኬት ሰራተኛ ለገዛቸው ሁለት ትኬቶች ከልክ በላይ አስከፈለው።
ትኬቶቹ እያንዳንዳቸው 35 ሩፒ የሚያወጡ ሲሆን 100 ሩፒ ለሰራተኛው ሲሰጠው 30 ሩፒ በመመለስ ፋንታ የመለሰለት 10 ሩፒ ነበር።
ከዋጋው በላይ እንዳስከፈለው ለቲኬት ሰራተኛው ቢነግረውም ገንዘቡ ሊመለስለት አልቻለም።
በዚህም የባቡር ጣቢያውንና ሰራተኛውን በመክሰስ ጉዳዩን ወደ ሸማቾች ፍርድ ቤት ወሰደው።
በወቅቱም ባቡር ጣቢያው ለሚነሱበት ቅሬታዎች በባቡር ቅሬታ ሰሚ እንጂ በሸማቾች ፍርድ ቤት መቅረብ የለበትም በማለት ጉዳዩን ውድቅ ለማድረግ ሞክሯል።
ሆኖም ግን ጉዳዩ በሸማቾች ፍርድ ቤት እንዲታይም ለማድረግ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ተወስዷል።
ከረዥም ጊዜ ትግል በኋላ ባቡር ጣቢያው አስር ሺህ ብር ቅጣት እንዲከፍል እንዲሁም 20 ሩፒ (13 ብር) ከ22 አመት 12 በመቶ ወለድ እንዲመልሱለት ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አስተላልፏል። ገንዘቡ በተጠቀሰው 30 ቀናት ካልተከፈለ የወለድ መጠኑ ተሻሽሎ 15 በመቶ እንደሚሆንም ፍርድ ቤቱ አስጠንቅቋል።
ያገኛውም ካሳ ካደረገው ትግል ጋር ሲነጻጸር ኢምንት የሚባል ቢሆንም ዋናው ገንዘቡ አይደለም ይላል።
“ዋናው ጉዳይ ገንዘቡ አይደለም። ሁሌም ለፍትህ መታገል እና ሙስናን ለመዋጋት የተደረገ ትግል ስለሆነ ከፍተኛ ዋጋ አለው” ሲል ተናግሯል።












