የካናዳ ፖሊስ በግጭት ተሳትፈዋል ያላቸውን 16 ኤርትራውያን ምስል ይፋ አደረገ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የካናዳዋ ከተማ ካልጋሪ ፖሊስ በኤርትራውያን ማኅበረሰብ መካከል በተፈጠረው ግጭት ተሳትፈዋል ያላቸውን 16 ግለሰቦች እየፈለገ ነው።
የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ በካልጋሪ ከተማ ሰሜን ምስራቅ በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት በርካታ ተቋማት ወድመዋል።
እንደ ፖሊስ ከሆነ በግጭቱ 150 የሚሆኑ ግለሰቦች የተሳተፉ ሲሆን አብዛኞቹ መሣሪያ የታጠቁ ናቸው።
ከሦስት ሳምንታት በፊት በከተማዋ በተከሰተው ግጭት 11 ሰዎች ተጎድተው ወደ ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን፣ ሁሉም ለሕይወታቸው አስጊ ባልሆነ የጤንነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት ገልጿል።
የካልጋሪ ፖሊስ አዛዥ በግጭቱ ተሳታፊ ባልነበሩ ተሽከርካሪዎች እና የንግድ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን አስታውቀው ነበር።
የፖሊስ አዛዡ ማርክ ኒውፌልድ እንዳሉት ግጭቱ በከተማዋ ሊካሄዱ በታቀዱ ሁለት የተለያዩ ሁነቶች ላይ ነበር የተከሰተው።
ግጭቱን ተከትሎም የከተማዋ ፖሊስ በከተማዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከሰተ “አስከፊ ግጭት” ያለውን ክስተት የሚመረምር ግብረ ኃይል አቋቁሞ ምርመራ እያካሄደ ነው።
የኤርትራውያን ማኅበረሰብ በሁለት ጎራ ተከፍለው በፈጠሩት በዚህ ግጭት የተሳተፉ ተጠያቂ እንደሚደረጉም የፖሊዝ አዛዡ ገልጸው ነበር።
ትናንት ሐሙስ ፖሊስ ግጭቱን በተመለከተ እያካሄደ ያለው ምርመራ እንደቀጠለ ገልጾ፣ በግጭቱ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ 16 ግለሰቦችን ማንነት መለየቱን አስታውቋል።
በዚህም የ16ቱን ተፈላጊ ግለሰቦች ፎቶግራፍ ይፋ አድርጓል።
ይፋ በተደረጉት ፎቶግራፎች ላይ የሚታዩ ግለሰቦችን የሚያውቅ አሊያም ግጭቱን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ያለው ማንኛውም አካል ለካልጋሪ ፖሊስ ጥቆማ እንዲሰጥም ተጠይቋል።

የፎቶው ባለመብት, Global News
ከቅርብ ግዜ ወዲህ የኤርትራ የባሕል ፌስቲቫል ዝግጅትን ምክንያት በማድረግ በኤርትራውያን መካከል በካናዳ፣ በአውሮፓ እና አሜሪካ ከተሞች ግጭት ሲፈጠር መመልከት አዲስ ነገር አይደለም።
በዚህ ዓመት ብቻ ካናዳን ጨምሮ በጀርመን፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ እና በእስራኤል ብዙዎችን ለጉዳት የዳረገ ግጭት ተከስቷል።
ባለፈው ሳምንት በጀርመኗ ስቱትጋርት ከተማ የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚዎች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን በቁጥጥር ሥር መዋላቸው አይዘነጋም።
ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይም ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች በቴል አቪቭ ከባድ ሁከት ፈጥረው በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ከደረሰ በኋላ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር አፍሪካውያን ስደተኞች በሙሉ ‘በአስቸኳይ’ ከእስራኤል ለማባረር እቅድ እንዲወጣ ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወሳል።












