ቻይና ከአሜሪካ ጋር ተባብራ የምትሰራባቸውን ቁልፍ ጉዳዮች ማቋረጧን አስታወቀች

የቻይና የጦር አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, HANDOUT

የምስሉ መግለጫ, ቻይና በታይዋን ዙሪያ በባሕር እና በአየር የምታካሂደው ወታደራዊ ልምምድ እንደቀጠለ ነው

የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን በታይዋን ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ ቻይና በበርካታ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ከአሜሪካ ጋር ተባባሮ የመሥራት ስምምነቷን ማቋረጧን አሳወቀች።

አሜሪካ እና ቻይና በዓለም የአየር ፀባይ ለውጥ፣ በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ ሊያደርጉ የነበረው ውይይት እና የዓለም አቀፍ ወንጀሎችን በመዋጋት በኩል ተባብሮ ለመሥራት ስምምነት ነበራቸው።

የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሴ ግዛቴ በምትላት ታይዋን ይፋዊ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው ቻይና ከአሜሪካ ጋር ተባብሮ ለመሥራት የነበራትን እቅድ ለመቋረጥ የወሰነችው።

በተጨማሪም ቻይና ሉዓላዊ ግዛቴ ናት በምትላት ታይዋን ላይ ያላትን ይገባኝል በመቃረንም በአፈ ጉባኤ ፔሎሲ እና ቤተሰቦቻቸው ላይ ዕቀባን ጥላለች።

ቻይና እንደተገንጣይ ግዛትዋ የምትመለከታት ታይዋን እራሷን ከቻይና የተለየች ግዛት አድርጋ ትመለከታለች።

ቻይና ውሳኔዋን ያሳወቀችው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ሲሆን፣ በዚህም በአሜሪካ እና በቻይና የመከላከያ ባለሥልጣንት መካከል የሚካሄድ ውይይት ሲሰረዝ፣ ሕገ ወጥ ስደተኞችን የመመለስ ትብብር፣ የአየር ፀባይ ለውጥ፣ በዓለም አቀፍ ወንጀሎች ላይ በጋራ ምርመራ የማድረግ ሥራም እንዲቀቋረጥ ተደርጓል።

ሁለቱ ኃያላን አገራት የዓለም የአየር ፀባይ ለውጥን ለመከላከል በቀጣይ ዓመታት መወሰድ ባለባቸው እርምጃዎች ዙሪያ ዲፕሎማሲያዊ ስምምነት ደርሰው ነበር። ባለፈው ዓመት በተደረገው ጉባኤ ላይም ቻይና የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ከአሜሪካ ጋር በጋራ ለመስራት ቃል ገብታ ነበር።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው ይህ ውሳኔ የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፔሎሲ “የቻይናን ጠንካራ ተቃውሞ ችላ በማለት ባሳዩት ከባድ ምሳሌ” ምክንያት መሆኑን ገልጿል።

ቻይና በአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት የፔሎሲ ጉብኝትን “የከፋ ጠብ አጫሪነት” ነው በማለት ተቃውሞዋን ያሰማች ሲሆን፣ የቻይና የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ በትዊተር ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ላይ ባለፈው ዓመት አሜሪካ ውስጥ በፖሊስ ተንቆ የተገደለውን ጥቁር አሜሪካዊን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

“አሜሪካ የዓለም ፖሊስ እንድትሆንና አገራትን በማስፈራራት እንደ ጆርጅ ፍሎይድ እንድታንቅ አንፈቅድም” ሲሉ ጽፈደዋል።

አርብ ዕለት የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሪን ጂን-ፔሪ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ናንሲ ፔሎሲ ወደ ታይዋን የመሄድ “ሙሉ መብት ነበራቸው” በማለት፣ ቻይና የወሰደችውን እርምጃ “ኃላፊነት የጎደለው” ሲሉ ተቃውመውታል።