የ‘አንድ ቻይና’ ፖሊሲ ምንድን ነው?

የቻይና ሰንደቅ ዓላማ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

‘አንድ ቻይና’ (ዋን ቻይና) ፖሊሲ፤ በሕጋዊው የቻይና መንግሥት ስር የምትዳደር ታይዋንን ያጠቃለለች አንዲት ሉዓላዊት ቻይና ብቻ መኖሯን የሚያረጋገጥ ፖሊሲ ነው።

አሜሪካንን ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያን አገራት ይህን ‘የአንድ ቻይና’ ፖሊሲን አይገዳደሩም።

አሜሪካ እውቅና የምትሰጠውም ይሁን ይፋዊ ግንኙነት ያላት ከቻይና ጋር እንጂ ከራስ ገዝ ግዛቷ ታይዋን ጋር አይደለም።

ምንም እንኳ ታይዋን እራሷን እንደ ሉዓላዊ ግዛት ብትቆጥርም፤ ቻይና ግን አንድ ቀን ከታላቋ ቻይና ጋር መልሳ የምትደመረ ተገንጠይ ግዛቷ አድርጋ ትቆጥራታለች።

በቻይና-አሜሪካ ግንኙነት ውስጥ የአንድ ቻይና ፖሊስ ቁልፍ ጉዳይ ነው። ቻይናም ከተቀረው ዓለም ጋር ባላት ግንኙነት ሁሉ የአንድ ቻይና ፖሊሲ መከበር መሠረታዊ ጉዳይዋ ነው።

አሜሪካ ለታይዋን እውቅና አትሰጥም፤ ቤይጂንግ ታይዋንን በተመለከት ለምታራምደው ፖሊሲም ማረጋገጫ አትሰጠም።

በሌላ በኩል ደግሞ ዋሽንግተን ዲሲ፤ ሉዓላዊት አገር ነኝ የምትለው ታይዋን እራሷን መከላከል እንድትችል በሚል የጦር መሳሪያ በሽያጭ መልክ ታቀርብላታለች።

የቻይና ሪፐብሊክ

ታይዋን ሉዓላዊ አገር ነኝ ትላለች። ይፋዊ መጠሪያዬም ‘ሪፓብሊክ ኦፍ ቻይና’ [የቻይና ሪፐብሊክ] ነው ትላለች።

ከቤይጂንግ ጋር ማለትም፤ ከፒፕልስ ሪፓብሊክ ኦፍ ቻይና [ከቻይና ሕዝባዊት ሪፐብሊክ] ጋር ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማድረግ የሚሻ አገር፤ ከታይዋን ጋር ይፋዊ ወዳጅነት ሊኖረው አይችልም።

ይህ ጠንካራ የቤይጂንግ የአንድ ቻይና ፖሊሲ ታይዋን ከተቀረው ዓለም ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እጅጉን የሳሳ እንዲሆን አድርጎታል።

የታይዋን ሰንደቅ ዓላማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የታይዋን ሰንደቅ ዓላማ

ይህ ፖሊሲ ከየት መጣ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በቻይና የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት ተሸናፊ የነበረው የብሔርተኛው ቡድን ከዋናዋ የቻይና ግዛት ሸሽቶ በታይዋን ደሴት ላይ ከተመ።

በእርስ በእርስ ጦርነቱ ድል የተቀዳጀው ኮሚኒስት ፓርቲ 'ፒፕልስ ሪፓብሊክ ኦፍ ቻይናን' ማስተዳደር ሲጀምር፤ ተሸናፊው ቡድን ደግሞ ሸሽቶ የገባባትን ታይዋን መምራት ጀመረ።

ሁለቱም ቡድኖች መላዋን ቻይና የምንወክለው እኛ ነን ይሉ ነበር።

ቀደም ሲል ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው አገራት ለታይዋን እውቅና ይስጡ ነበር። ይሁን እንጂ የቻይና ምጣኔ ሃብት እና ተጽእኖ ፈጣሪነት እያየለ ሲመጣ ጀርባቸውን ለታይዋን ፊታቸውን ደግሞ ወደ ቻይና ማዞር ጀመሩ። 

አሜሪካም ብትሆን ያደረገችው ይህንኑ ነው። አሜሪካ ለታይዋን እውቅና ሰጥታ ነበር። እአአ 1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት እያደገ ሲመጣ በታይዋን መዲና የነበራትን ኤምባሲ ለመዝጋት ተገዳለች።

እአአ 1979 ላይ አሜሪካ በታይፒ የነበራትን ኤምባሲ ትዝጋ እንጁ፤ በዚያው ዓመት ታይዋን ሪሌሽን አክት የተሰኘ ከታይዋን ጋር ያላትን ግንኙነት የምትመራበትን ሕግ አውጥታ ነበር።

ይህ ሕግ አሜሪካ ታይዋን ራሷን እንድትከላከል የማገዝ ግዴታ አለባት የሚል አንቀጽን አካቷል። በዚህም መሠረት አሜሪካ የጦር መሳሪያዎችን ለታይዋን ትሸጣለች።

ታይዋን ጠንካራ ምጣሄ ሃብት ያላት ግዛት ናት። ከ300 ሺህ ያላነሰ የጦር ሠራዊት አባላትም አላት።

መሪዎቿም ከቻይና በተለየ ሁኔታ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጡ መሆናቸው ይነገራል።

ለዚህም አገራት ከታይዋን ጋር ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባይኖራቸውም፣ በንግድ እና በባህል ጽ/ቤቶች አማካይነት ይፋዊ ያልሆነ ግንኙነታቸውን እንዳስቀጠሉ ናቸው።

አሁን ላይ ለታይዋን እንደ አገር እውቅና የሚሰጡት ጥቂት አገራት ከመሆናቸውም በተጨማሪ፣ በተጽእኖ ፈጣሪነታቸው እዚህ ግቡ የሚባሉ አገራት አይደሉም።

ለታይዋን እውቅና ከሚሰጡ አገራት መካከል የመካከለኛው አሜሪካ አገራቱ ጓቲማላ፣ ሆንዱራስ፣ ኒካራጓ እና አፍሪካዊቷ ኢስቲዋኒ ይገኙበታል።