የፕሪሚዬር ሊጉ ሩጫ፡ አርሰናል እና ሊቨርፑል ዋንጫውን ለሲቲ አሳልፈው ሰጥተዋል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አርሰናል ወሳኝ በሚባለው ጨዋታ በሜዳው ሽንፈት ቀምሷል። ሌላኛው የዋንጫ ተፎካካሪ ሊቨፑልም እንዲሁ በአንፊልድ ነጥብ ሳይዝ ወጥቷል።
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ትላንት እሑድ በነበሩ ሁለት ጨዋታዎች ብቻ አቅጣጫውን የቀየረ ይመስላል።
ከአርሰናል ቀድሞ በሜዳው ክሪስታል ፓላስን ያስተናገደው ሊቨርፑል 1- 0 ተሸንፏል። ሊቨርፑል በገዛ ሜዳው ከተሸነፈ በርካታ ቀናት ተቆጥረው ነበር።
ከዚህ በኋላ አመሻሹን የተደረገው ጨዋታም እንዲሁ በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ የሚባል ነበር።
በኤሜሬትስ ስታድየም አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን አስተን ቪላ ለማስተናገድ ወደሜዳ የገባው በተስፋ ቢሆንም፣ ጨዋታው 90ኛ ደቂቃ ሲደፍን የአርሰናል ደጋፊዎች ስታድየሙን ለቀው ወጥተዋል።
የማይክል አርቴታ ቡድን በቀድሞው የአርሰናል አሠልጣኝ ኡናይ ኤምሪ አስተን ቪላ 2 - 0 ተሸንፏል።
እርግጥ ነው የዋንጫ ፉክክሩ ገና አልተጠናቀቀም። ሦስቱን ቡድኖች የሚለያቸው ሁለት ነጥብ ብቻ ነው። ነገር ግን ማንቸስተር ሲቲ የሰንጠረዡ አናት ላይ መሆኑ ሊቨርፑል እና አርሰናል ላይ ጫና እንደሚያሳድር ይጠበቃል።
ተንታኞች አርሰናል እና ሊቨርፑል ራሳቸውን ጠልፈው የሚጥሉ ቡድኖች ናቸው ይሏቸዋል። ሁለቱም ቡድኖች ሦስት ነጥብ ከምንም ጊዜውም በላይ በሚያስፈልጋቸው ሰዓት ባዶ እጃቸውን ወጥተዋል።
አሁን ትልቁ ጥያቄ ሊቨርፑል እና አርሰናል አሁን ከደረሰባቸው ሽንፈት ያገግማሉ ወይስ ዋንጫውን ለሲቲ አሳልፈው ይሰጣሉ? የሚለው ነው።
የአርሰናል ደጋፊዎች ከጨዋታው በፊት ወደ ሜዳ የገቡት በተስፋ ታጅበው ነበር። ክሪስታል ፓላስ ወደ አንፊልድ ተጉዞ ሊቨርፑልን ማሸነፉ ደግሞ የበለጠ ደስታ እና ተስፋ ሰጥቷቸው ታይተዋል።
ሊቨርፑል ባለፈው ሳምንት በኦልድ ትራፈርድ ከዩናይትድ ጋር አቻ ከተለያየ በኋላ በሳምንቱ አጋማሽ በአውሮፓ ሊግ በሜዳው በአታላንታ 3 - 0 መሸነፉ ብዙዎችን ያስገረመ ዜና ነው።
ቀያዮቹ ከፓላስ ጋር በነበራቸው ጨዋታ እንደ ወትሮው አስፈሪ የሚባል እንቅስቃሴ አላሳዩም። አብዛኞቹ ተጫዋቾች ጥርስ የሌለው አንበሳ ሆነው፤ ድካም ተጫጭኗቸው እንደነበር በግልፅ ታይተዋል።
የሊቨርፑል ተጫዋቾች ለአራት ዋንጫዎች ለመፎካከር ያደርጉት የነበረው ትግል ድካም እንዳላበሳቸው መገመት አያዳግትም።
ወደ ኤሜሬትስ እንመለስ...
በሊቨርፑል ሽንፈት ደስታ እና ተስፋ ሰንቀው ወደ ሜዳ የገቡት አርሰናሎች በመጀመሪያው አጋማሽ በተደጋጋሚ ወደ ጎል ቢቀርቡም ኳስን ከመረብ ማገናኘት ተስኗቸው አምሽተዋል።
ባለፈው የውድድር ዘመን እስከ መጨረሻዎቹ ጥቂት ሳምንታት ድረስ ከሲቲ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ ዋንጫው ያመለጣቸው የአርሰናል ደጋፊዎች በሁለተኛው አጋማሽ ፊታቸው ላይ ጭንቀት ይነበብ ያዘ። ፍርሀት እንደወረራቸው የቴሌቪዥኑ ስክሪን አሳበቀ።
ፍርሀታቸው እውን ሆነ። የአስተን ቪላው ቤይሊ በ84ኛው ደቂቃ የመጀመሪዋን ጎል አስቆጠረ። ከ4 ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ኦሊ ዋትኪንስ ሁለተኛውን ጎል በማከል የአርሰናል ቅስም ሰበረ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፔፕ ጉዋርዲዮላ እና የሲቲ ተጫዋቾች መልካም እሑድ አሳለፉ። ቅዳሜ ዕለት ሉተን 5 - 1 የረቱት ሲቲዎች ለዋንጫ የሚፎካከሯቸው አርሰናል እና ሊቨርፑል በገዛ ሜዳቸው ሲረመረሙ ተመለከቱ።
ሊቨርፑል በያዝነው የውድደር ዘመን በበርካታ ጨዋታዎች ቀድሞ ጎል ቢገባበትም ውጤት ቀልብሶ በማሸነፍ ዝና አፍርቶ ነበር። ይህ አደገኛ አጨዋወታቸው ግን እሑድ ዋጋ አስከፈላቸው።
ኤቤሬቼ ኤዜ ለፓላስ ጎል አስቆጠረ። የኤዜ ጎል ሊቨርፑል በዘንድሮው የውድድር ዘመን ቀድሞ የተቆጠረበት 14ኛ ጎል ነው።
የርገን ክሎፕ በውድድሩ ዘመን መጨረሻ ሊቨርፑልን እንደሚሰናበቱ አሳውቀዋል። የፕሪሚዬር ሊጉን ዋንጫ በማንሳት ለዓመታት ያሠለጠኑት ክለብ ለመሰናበት የወጠኑት ህልም እውን የመሆኑ ጉዳዩ አጠራጣሪ ሆኗል።
ለክሎፕ የሚያሳዝነው ጉዳይ አስፈሪ የአጥቂ መስመር አለው የሚባለው ቡድናቸው በወሳኙ ወቅት መዳከሙ ነው። ሊቨርፑል በሁሉም ውድድሮች ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች 2 ግብ ብቻ ነው ያስቆጠረው።
ክሎፕ ይህን ቀልብሰው ስንብታቸውን ያሳምሩ ይሆን? እጅግ ከባድ ሥራ ይጠብቃቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አርሰናል ለመጨረሻ ጊዜ ሽንፈት የቀመሱት የአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት ዋዜማ በፉልሀም 2 - 1 በተረቱበት ወቅት ነበር። ለወትሮው ንቁ የነበረው የአርሰናል የአጥቂ መስመር መዳከም ይታይበታል።
በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ ከሙኒክ ጋር በነበረው ጨዋታ ታይቶ የነበረው የአርሰናል ተከላካይ መስመር ክፍተት ከቪላ ጋር በነበረው ጨዋታ ተጋልጧል።
መድፈኞቹ በገዛ ሜዳቸው እንዲህ ደካማ አቋም ካሳዩ ሰነባብተዋል። እንዲያውም ቪላ ጎል ለማስቆጠር እስከ 80ኛው ደቂቃ ድረስ መቆየቱ አስገራሚ ነው።
የቪላው አሠልጣኝ ኡናይ ኤምሪ በአውሮፓውያኑ 2019 አርሰናልን ይዘው 18 ወራት መንበራቸው ላይ ከቆዩ በኋላ ነበር የተባረሩት። እነሆ ቪላን ይዘው በአንድ የውድድር ዘመን አርሰናልን ሁለት ጊዜ መርታት ችለዋል።
አስተን ቪላ አራተኛ ደረጃን ተቆናጦ የያዘ ይመስላል። ይህ ማለት ቪላ በሚቀጥለው ዓመት የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ተሳታፊ ሊሆን ይችላል ማለት ነው። ኡናይ በቪላ ቤት የሠሩት ሥራ ብዙ አድናቆት እያተረፈላቸው ነው።
ሚያዚያ 6 አርሰናል እና ሊቨርፑል ዋንጫውን ለሲቲ አሳልፈው የሰጡባት ቀን ብለን እናስታውሳት ይሆን ወይስ ውጤቱ ይቀለበሳል?
መልሱን ጊዜ ይፈታዋል። ነገር ግን አርሰናልም ሆነ ሊቨርፑል ውጤቱን ቀልብሰው ሲቲን ከመንበሩ ለመፈንቀል አሁን እያሳዩ ካለው አቋም እጅግ የላቀ ነገር እንዲያሳዩ ይጠብቅባቸዋል።












