ባየር ሊቨርኩሰን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የጀርመን ቡንደስሊጋ ሻምፒዮን ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትላንት ዕሁድ በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሊቨርኩሰን ዌርደር በርሜን ማሸነፉን ተከትሎ አምስት ቀሪ ጨዋታዎች እያሉት የሊጉ ዋንጫ አሸናፊ መሆኑን አረጋግጧል።
ሊቨርኩሰን 5 ለምንም የረታበትን የዚህን ጨዋታ ፍጻሜ ተከትሎ አሰልጣኙ ዣቪ አሎንዞ በሰጠው አስተያየት ስሜቱ እጅግ ልዩ ነው ብሏል።
ይህንን ዋንጫ ላለፉት 11 ዓመታት ያነሳው ባየርን ሙኒክ ባለፈው ቅዳሜ ተጋጣሚውን ቢረታም የሊቨርኩሰንን ድል ተከትሎ ከዋንጫ ፉክክሩ ውጪ ሆኗል።
ትላንት ባይር ሊቨርኩሰን በሜዳው ባይአሬና ተጋጣሚውን አሸንፎ የዋንጫው አሸናፊ መሆኑን ሲያረጋግጥ በስታዲየም ውስጥ ደጋፊዎች በከፍተኛ ደስታ ውስጥ ሆነው ታይተዋል።
ከድሉ በኋላ በጀርምን ባህል መሰረት ቢራ ይዞ የታየው አሎንዞ “ዛሬን ከቤተሰቦቻችን፣ ከጓደኞቻችን እና ደጋፊዎቻችን ጋር ልንደሰት ይገባል። እንደ አስልጣኝ ሙሉ የውድድር ዘመን ሳሳልፍ ይህ የመጀመሪያ ነው። ስሜቱ በጣም ልዩ ነው” ሲል አስተያየት ሰጥቷል።
ሊቨርኩሰንን አሸናፊ ባደረገው ጨዋታ ቪከተር ቦንፌስ በፍጹም ቅጣት ምት በ25ተኛው ደቂቃ የመጀመሪያውን ጎል አስቆጥሯል።
በመቀጠል ግራኒት ዣካ ሁለተኛውን ጎል ያስቆጠረ ሲሆን ፍሎሪያን ዎርትዝ የቀሩትን ሶስት ጎሎች አግብቶ ሀትሪክ ሰርቷል።
ባለፈው ነሀሴ አርሰናልን ለቆ ሊቨርኩሰንን የተቀላቀለው ዣካ “እርግጥ ነው፣ በውድድር ዘመኑ መጀመሪያ ይህንን መገመት አንችልም ነበር” ሲል ገልጿል።
ሀትሪክ የሰራው ዎርትዝ ደግሞ “ይህ ነገር እውነት ሆኗል ብዬ አላመንኩም። ምን እንዳሳካን መልበሻ ክፍል ገብቼ ጥቂት ጊዜ ማሰብ ይኖርብኛል” ብሏል።
የሊቨርኩሰን የዋንጫ ድል ላለፉት 11 ዓመታት ዋንጫ ያነሳው እና ቡንደስሊጋው ላይ ሃያል የሆነውን የሙኒክ ዘመን ማብቂያ ምልክት ተደርጎ ተውስዷል።
በዚህ የውድድር ዘመን በሁሉም ውድድሮች ምንም አይነት ሽንፈት ያልገጠመው ሊቨርኩሰን ከዚህ ዋንጫው በተጨማሪ በጀርምን ዋናጫ እና በዩሮፓ ሊግ ተሳታፊ ነው።
ለአንድ ሙሉ የውድድር ዘመን አስልጣኝ ሲሆን የመጀመሪያው የሆነው አሎንዞ በሳምንታት ውስጥ እያስመዘገበ የመጣው ድል የቡንደስሊጋን ዋንጫ ማንሳቱ እንደማይቀር ብዙዎች ግምታቸውን ሰጥተዋል።
አሰልጣኙ በፈረንጆቹ ጥቅምት 2022 ክለቡን ሲረከብ ሊቨርኩሰን ከሊጉ የመውረድ ቀጠና ውስጥ ነበር።
ሆኖም ከ18 ወራት በኋላ በሊጉ ኃያል ከሆነው ባየር ሙኒክ በ16 ነጥብ ርቆ ሻምፒዮን መሆኑን አረጋግጧል።












