ከክፍያ ውዝግብ ጋር በተያያዘ በማሊ የተያዙበትን ሰራተኞች ለማስለቀቅ አውስትራሊያዊው ኩባንያ 160 ሚሊዮን ዶላር ሊከፍል ነው

የወርቅ ማዕድን ሰራተኛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አውስትራሊያዊው የወርቅ ማዕድን ኩባንያ ለማሊ መንግሥት የሚገባውን ክፍያ ካለመፈጸም ውዝግብ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉበትን ሰራተኞች ለማስለቀቅ 160 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማማ።

በማሊ በማዕድን ቁፋሮ የተሰማራው ይህ ኩባንያ ለአገሪቱ መንግሥት ግብርን ጨምሮ ሌሎች ክፍያዎችን ባለመክፈላቸው እንግሊዛዊ ዜግነት ያለው ዋና ስራ አስፈጻሚው እና ሁለት ሰራተኞች ከአስር ቀናት በፊት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

ሪዞሉት የተሰኘው የማዕድን ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ቴሬንስ ሆሎሃን እና ሌሎች ሁለት ሰራተኞች በማሊ መዲና ባማኮ በግብር እና ሌሎች ቀሪ ክፍያዎችን በተመለከተ ከመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ተወያይተው ሲወጡ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ሪፖርቶች አመላክተዋል።

በምዕራባዊቷ አፍሪካዊት አገር ማሊ ውስጥ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ያለው ሪዞሉት 80 ሚሊዮን ዶላር ካለው የገንዘብ ክምችት ወዲያውኑ እንደሚከፍል እሁድ እለት አስታውቋል።

ቀሪውን ክፍያ ደግሞ በሚቀጥሉት ወራት ውስጥ እፈጽማለሁ ብሏል።

ማሊ በአፍሪካ ውስጥ ካሉ በወርቅ ማዕድን ሃብታም ከሆኑ አገራት አንዷ ናት።

ሶስቱ የኩባንያው ሰራተኞች መቼ እንደሚፈቱ እስካሁን ግልጽ አይደለም።

ከእስር እንዲፈቱ ከተደረሱ ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ የቀረበላቸውን የመግባቢያ ሰነድ መፈረም እና የመጀመሪያውን ክፍያ ማጠናቀቀ እንደሆኑ የፈረንሳይ ብሮድካስቲንግ አርኤፍአይ ዘግቧል።

የማሊ ወታደራዊ ገዥዎች ሶስቱን የሪዞሉት ስራ አስፈጻሚዎች በቁጥጥር ስር ያዋለው በህዝብ ንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ እንዲሁም በማጭበርበር ወንጀሎች ነው።

ከሶስት ዓመታት በፊት በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን የተቆጣጠረው የማሊ ወታደራዊ መንግሥት በፖለቲካው እና የንግዱ ዘርፍ ከአለም አቀፍ አጋሮች ጋር ያለውን ግንኙነት እንደገና ለማዋቀር እየሞከረ ይገኛል። ባለፈው ዓመት ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች የማዕድን ድርሻቸውን ከ20 ወደ 35 በመቶ ከፍ የሚያደርግ አዲስ መመሪያ ፈርመዋል።