የአሜሪካ ባሕር ኃይል መርከበኛ ለቻይና በመሰለል ጥፋተኛ ተባለ

የፎቶው ባለመብት, US Justice Department
በካሊፎርኒያ የሚገኘው የአሜሪካ ባሕር ኃይል መርከበኛ የጦሩን ሚስጥሮች በማኅበራዊ ሚዲያ ለመለመለው ቻይናዊ በመሸጥ በስለላ ወንጀል ጥፋተኛ ተባለ።
የ25 ዓመቱ ጂንቻኦ ዌይ በስድስት ወንጀሎች የተከሰሰ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ስለላ፣ ስለላ ለመፈጸም በማሴር እና ስለ የአሜሪካ የባሕር ኃይል መርከቦች ሚስጥራዊ መረጃዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ በመላክ የሚሉ ናቸው።
የአሜሪካ አቃቤ ሕግ አደም ጎርደን ብይኑ ከተነበበ በኋላ በሰጡት መግለጫ "የተከሳሹ ድርጊት የአሜሪካ ጦር አባል ሆኖ በተሰጠው እምነት ላይ ከባድ ክህደት መፈጸሙን ያሳያል" ብለዋል።
"ወታደራዊ ሚስጥሮችን ለቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ በገንዘብ በመሸጥ የባልደረቦቹን ሕይወት ብቻ ሳይሆን የመላ አገሪቱን እና የአጋሮቻችንን ደህንነት አደጋ ላይ ጥሏል።"
ፓትሪክ ዌይ በሚልም የሚታወቀው ተከሳሹ እኤአ በነሐሴ 2023 በዩኤስኤስ ኤሴክስ መርከብ ላይ ለሥራ በመጣበት ወቅት በስለላ ተወንጅሎ በቁጥጥር ስር ውሏል።
በቅርቡ የዩናይትድ ስቴትስ ዜግነት ያገኘው ዌይ የማሽን ባለሙያ ሲሆን የደህንነት ይለፍ ያለው እና ስለ መርከቧ እና ሌሎች በፓስፊክ ስለሚገኙ መርከቦች ጥብቅ የሆኑ መረጃዎችን የማግኘት ዕድል ነበረው።
ሳምንታት በፈጀው የፍርድ ሂደት፣ አቃብያነ ሕጎች ዌይ ከቻይና ሰላይ ጋር የተለዋወጠቸውን የስልክ ምልልሶች፣ የኤሌክትሮኒክስ እና የድምጽ መልዕክቶችን በማስረጃነት አቅርበዋል።
ዌይ ቻይናዊውን ግለሰብ "ቢግ ብራዘር አንዲ" ብሎ የሚጠራው ሲሆን ግንኙነታቸው ሚስጢራዊ ለማድረግ መልዕክትን የሚደብቁ መተግበሪያዎችን ለመጠቀም ትዕዛዝ ተቀብሏል።
ዌይ በቻይናዊው መልማይ የተሰጠውን አዲስ ኮምፒውተር እና ስልክም ተጠቅሟል።
ዌይ የስለላ ተግባር እንደሚፈጽም መረዳቱን ለማሳየት በዌይ እና በእናቱ መካከል የተደረገ የጽሑፍ መልዕክት ልውውጥ ቀርቧል።
"በአሜሪካ የባሕር ኃይል ውስጥ የሚያገለግሉ ሌሎች ቻይናውያን አሁንም ተጨማሪ ገንዘብ እንዴት ማግኘት እንደሚችሉ ለማወቅ እየሞከሩ ነው። እና ታክሲዎችን እየነዱ ነው። እኔ ግን ሚስጥሮችን እያሾለኩ ነው" ሲል ዌይ ለእናቱ መልዕክት ልኳል።
እሷም "ጥሩ ስራ!" ስትል መልሳለች።
ዌይ የአሜሪካ ዜጋ ለመሆን እየተቃረበ በነበረበት እአአ በየካቲት 2022 በቻይና ሰላይ መመልመሉ ተገልጿል።
በቻይና የስለላ ባልደረባ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የተመለመለ ሲሆን እሱም በመጀመሪያ በመንግሥት ባለቤትነት በተያዘው በቻይና የመርከብ ግንባታ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ውስጥ እንደሚሰራ የባሕር ኃይል አፍቃሪ አድርጎ ራሱን አቅርቧል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ዌይ የኤሴክስ ፎቶግራፎችን እና ቪዲዮዎችን ልኳል፣ የተለያዩ የባሕር ኃይል መርከቦች የሚገኙበትን ቦታ ለኃላፊው ምክር ሰጥቷል።
እንዲሁም በኤሴክስ ተሳፍሮ የነበረውን የመከላከያ መሣሪያዎችን ገልጿል። በመርከቧ እና በሌሎች መርከቦች ላይ ያሉ ችግሮችንም ገልጿል።
ይህን መረጃ ለማግኘት የቻይናው የስለላ መኮንን ለ18 ወራት ከ12,000 ዶላር በላይ ከፍሏል::
ዌይ ታህሳስ 1 የፍርድ ውሳኔ እንዲሰጠው ቀጠሮ የተያዘ ሲሆን የዕድሜ ልክ እስራት ሊጠብቀው ይችላል።
ቢቢሲ የዌን ጠበቃ አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
ዌይ እአአ በ 2023 14,800 ዶላር በመቀበል ለቻይና የስለላ መኮንን ፎቶዎችን፣ ቪዲዮዎችን በመላክ ከተከሰሰ ከሌላ ባልደረባው ጋር በቁጥጥር ስር ውሏል።
ይህ ባልደረባው ባለፈው ዓመት ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ሲሆን የ27 ወራት እስራት ተፈርዶበታል።















