ለአሜሪካ ጥቁሮች መኖሪያ እንድትሆን የተፈጠረችው አፍሪካዊት አገር ውስብስብ ታሪክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በ19ኛው ክፍለ ዘመን በሺዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ ባሮች የነጻነት አገር ፍለጋ አሜሪካን ለቅቀው አትላንቲክ ውቅያኖስን አቋርጠው ቅድመ አያቶቻቸው ሳይወዱ በግድ ወደ ለቀቁት አህጉር ተጓዙ።
የመጀመሪያዎቹ ጥቁር አሜሪካውያን ከ200 ዓመታት በፊት በአፍሪካ ምዕራባዊ የባሕር ዳርቻ ሲደርሱ በግዳጅ ወደ አሜሪካ ባርነት የሄዱ የቀድሞ አባቶቻቸውን የተገላቢጦሽ መንገድ በመከተል ነበር።
እነዚህ ፈር ቀዳጆች፣ ብዙዎቹ ከባርነት በቅርቡ ነፃ የወጡ እና ሌሎችም በባርነት ተይዘው ከነበሩ የተወለዱ ልጆች ነበሩ።
እነርሱም የደረሱበትን የባሕር ዳርቻ ላይቤሪያ ወይም "የነጻነት ምድር" በሚል አዲሱን የመኖሪያ አገራቸውን ሰየሙ።
በዩናይትድ ስቴትስ ከባሪያ አሳዳሪዎቻቸው ነፃ ከወጡ በኋላም ጭፍን ጥላቻ፣አድልዎ እና ስፍር ቁጥር የሌላቸው እንቅፋቶችን የተጋፈጡት እነዚህ ጥቁር አሜሪካውያን አገሪቱን ለቅቀው ወደ አባቶቻቸው አህጉር ተመለሱ።
በአዲሱ ቤታቸው የተሻሉ ዕድሎች እና የፖለቲካ መብቶች የተሟላበት ሕይወት ለመገንባት ፈለጉ።
ነገር ግን ይህችን የሚያስቧትን አገር በአፍሪካ ውስጥ የመመሥረት ታሪካቸው ውስብስብ ነው።
ብዙ ነጻ ጥቁር አሜሪካውያን ወደ አፍሪካ የመመለስ እንቅስቃሴያቸውን ከብዙ አሥርት ዓመታት በፊት ሲጀምሩ፣ ድጋፍ የተደረገላቸው በቀድሞ የባሪያ አሳዳሪ ነጮች እና እነርሱ ባሉበት ማኅበር በኩል ነበር።
በማሳቹሴትስ ክላርክ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር እና በቅኝ ግዛት ዙሪያ በርካታ መጽሐፍ የጻፉት የታሪክ ምሁሩ ኦስማን ፓወር ግሪን "ወደ አፍሪካ የመመለስ እንቅስቃሴ የተጀመረው በጥቁር ሕዝቦች ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ እንቅስቃሴውን የተቀላቀሉት ለማባረር (ጥቁር አሜሪካውያንን ነፃ ለማውጣት) በመፈለጋቸው ነበር። ጥቁሮችን (በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ) ሰዎችን ማባረር በሚለው ሃሳብ በጣም ተደስተዋል" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, LIBRARY OF CONGRESS, USA
የአሜሪካ ቅኝ ግዛት ማኅበር
በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በአሜሪካ የባርነት ማብቂያ ተደርጎ የሚወሰደው የእርስ በርስ ጦርነት (1861-1865) ከመጀመሩ ከብዙ አሥርት ዓመታት በፊት በአገሪቱ ውስጥ ይህ ተቋም ቢፈርስ ነጻ የሚሆነው ጥቁር ሕዝብ ምን ሊደረግ ይችላል በሚለው ዙሪያ ይከራከሩ ነበር።
ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት በ1816 በዋሽንግተን በዴቪስ ሆቴል የተሰበሰቡ ነጮች የአሜሪካ ቅኝ ግዛት ማኅበርን - ኤሲኤስ (American Colonization Society) አቋቋሙ።
በአገሪቱ ባርነት ከመወገዱ ግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት የተመሠረተው ኤሲኤስ፣የወቅቱን ፕሬዝዳንት ጄምስ ማዲሰን (1809-1817) የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ቶማስ ጄፈርሰን (1801-1809) እና የወደፊት ፕሬዝዳንቶች ጄምስ ሞንሮ (1817-1825) እና አንድሩ ጃክሰንን (1829-1837) ድጋፍ አግኝቷል።
የኤሲኤስ አባላት ባርነትን በተመለከተ የተለያዩ እና ብዙ ጊዜ የሚጋጩ አመለካከቶች ነበሯቸው።
አንዳንዶቹ ባርነት እንዲወገድ የሚፈልጉ እና ጥቁሮች በአፍሪካ የተሻለ ኑሮ እንዲመሠረቱ ለመርዳት ልባዊ ፍላጎት ነበራቸው።
ሌሎች ግን ባርነትን የማስወገድ ሃሳብን ውድቅ አድርገው ነፃ ጥቁር ሕዝቦች በአሜሪካ መኖር እንደሌለባቸው ያምኑ ነበር።
ለዚህም ምክንያታቸው የባርነት ተቋምን አደጋ ላይ ሊጥሉ ይችላሉ ብለው ያምኑ ስለነበር ነው።
በጊዜው የነበሩ በርካታ ባሪያ አሳዳሪዎች፣ ብዙ ጥቁሮች ነፃ የሚወጡ ከሆነ በባርነት ላይ ያሉትን ሊያሳምፁ ይችላሉ ሲሉ በመፍራት አብረው እንዳይኖሩ ለመከላከል ሞክረዋል።
በአንዳንድ ሁኔታዎች የባሪያ አሳዳሪዎች አዲስ ነጻ የወጡትን ወደ አፍሪካ ለመውሰድ ተስማምተው ነበር።
ሌሎች የማኅበሩ አባላት ባርነት ቀስ በቀስ እንዲወገድ ደግፈዋል፤ ነገር ግን የውህደት ውጤቱን በመፍራት ነጻ ጥቁሮች እና ነጮች ጎን ለጎን ሊኖሩ ይችላሉ የሚለውን ሃሳብ ውድቅ አድርገዋል።
የአሜሪካ ቅኝ ግዛት ማኅበር አባላት በጉዳዩ ላይ ልዩነት ቢኖራቸውም በአፍሪካ ባለው የቅኝ ግዛት ፕሮጀክት ላይ ተስማምተዋል። በዚህም መሠረት በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ከባርነት ነጻ የወጡ አፍሪካውያንን ቁጥር ለመቀነስ ነፃ ለወጡ ጥቁሮች መኖሪያ ይመሠረታል።
ሃሳቡ ተቀባይነት እና ተወዳጅነት እያገኘ በመምጣቱ ብዙም ሳይቆይ በርካታ የቅኝ ገዥ ማኅበራት ተመሳሳይ ዓላማን በመከተል በመላ አገሪቱ ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ።
የአሜሪካ ቅኝ ግዛት ማኅበር ባለፉት አሥርት ዓመታት በበርካታ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፉን በማስታወስ "የዘረኝነት ድርጅት ነውን? ፀረ ባርነት ነው? መልሱ የበለጠ ውስብስብ ነው" ይላሉ ፓወር ግሪን።

የፎቶው ባለመብት, LIBRARY OF CONGRESS, USA
ወደ አፍሪካ የመመለስ ንቅናቄ
የአሜሪካ ቅኝ ግዛት ማኅበር የተመሠረተው በነጮች ቢሆንም፣ ወደ አፍሪካ የመመለስ እንቅስቃሴ በወቅቱ በጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ታዋቂ ነበር።
ባርነት ከመወገዱ በፊትም ቢሆን በመላ አገሪቱ የተለያዩ ነጻ ጥቁር አሜሪካውያን ማኅበረሰቦች ብቅ ብቅ እያሉ ነበር።
በባልቲሞር የሞርጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር እና የአፍሪካ ዲያስፖራ ባለሙያ የሆኑት የታሪክ ምሁር ኸርበርት ብሬወር "ወደ አፍሪካ የመመለስ እንቅስቃሴ የሚካሄደው በእነዚህ ማኅበረሰቦች ውስጥ ነው፣ እነዚህ ሃሳቦች የዳበሩት እዚህ ውስጥ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ወደ አፍሪካ የመመለስ እንቅስቃሴ ከኤሲኤስ በፊት የነበረ መሆኑን መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው" ይላሉ ብሬወር።
"በ18ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ጥቁር ሕዝቦች ትውልደ አፍሪካውያንን ወደ አፍሪካ ለመመለስ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እያሰቡ እና እየጻፉ ነበር።"
አንዳንድ ጥቁር አሜሪካውያን ወደ ቅድመ አያቶቻቸው አህጉር ወደ አፍሪካ በመመለስ ከአድልዎ ማምለጥ እንደሚችሉ እና እውነተኛ፣ ነፃ እና የበለጸገ ሕይወት መምራት እንደሚችሉ ያምኑ ነበር።ብዙዎቹ በአፍሪካዊ ማንነታቸው ይኮሩ ነበር።
"በ1820ዎቹ ዩናይትድ ስቴትስ ለጥቁሮች ልዩ ቦታ ነበረች" ሲሉ ብሬወር ይገልጻሉ። "በሕግም ሆነ በቴክኒክ ደረጃ ነጻ ነበሩ። ነገር ግን በእውነታው እና በወቅቱ በነበሩት የተለያዩ የሕግ ዓይነቶች ላይ በመመሥረት፣ ከሕዝብ ሕይወት የተገለሉ ናቸው።"

የፎቶው ባለመብት, LIBRARY OF CONGRESS, USA
ነገር ግን ብዙዎቹ የተወለዱበትን እና በላባቸው የገነቧትን አገር ለቅቀው የመውጣትን ሃሳብ ውድቅ በማድረግ ሙሉ ዜግነት ለማግኘት መብት ተሟገቱ።
በዚህ ምክንያትም የአሜሪካ ቅኝ ግዛት ማኅበር መፈጠር በነጻው ጥቁር ሕዝቦች መካከል መከፋፈል አጋጠመው።
በርካቶች ፕሮጀክቱ በባሪያ ባለቤቶች የተደገፈ፣ ውህደትን ለማስቀረት፣ ጥቁሮችን ለማፈናቀል እና የባርነት ተቋምን የበለጠ አስተማማኝ ለማድረግ ያለመ የዘረኝነት ዕቅድ ነው ሲሉ ተችተዋል።
ከአገር ለመውጣት ከተስማሙ ጥቁሮች መካከልም በኤሲኤስ አባላት እውነተኛ ዓላማ ላይ እምነት ማጣት ነበር።
ሌሎች ግን በድርጅቱ ውስጥ ወደ አፍሪካ ለመመለስ የነበራቸውን የረዥም ጊዜ ዕቅድ ለማሳካት ያለውን ዕድል እና የገንዘብ አቅም ተመልክተዋል። "ለእነሱ ይህ አመቺ ጥምረት ነበር" ይላሉ ብሬወር።
"ይህ ጉዳይ ምን ያህል ውስብስብ እንደሆነ ለማስረዳት ከባድ ነው" ይላሉ የታሪክ ምሁሩ።
"አንዳንድ ሰዎች ወደ አፍሪካ ለመሄድ ከወሰኑ በኋላ አቋማቸውን ቀይረዋል። አንዳንዶቹ ወደ አፍሪካ መሄድ ፈልገው ከዚያም ተስፋ ቆርጠዋል። ሌሎች ደግሞ ሃሳቡን ይቃወማሉ፤ ከዚያም ለመሄድ ወስነዋል።"
ለመንገደኞቹ ማረፊያ የሚሆን መሬት ፍለጋ
የአሜሪካ ቅኝ ግዛት ማኅበር በተመሠረተበት ወቅት፣ የብሪታንያ ንጉሥ አስቀድሞ በአፍሪካ ምዕራብ ዳርቻ ላይ በምትገኘው ሴራሊዮን የቀድሞ ባሪያዎችን ለመቀበል ግዛት መሥርቷል።
እነዚህ የቀድሞ ባሪያዎች አብዛኞቹ ከአሜሪካ አብዮት በኋላ ወደ ካናዳ የሸሹ ናቸው።
የዚህ ፕሮጀክት ስኬት ለኤሲኤስ ተወዳጅነት አስተዋጽኦ አድርጓል። እናም እንደ አውሮፓውያኑ በ1818 ማኅበሩ ጥቁር አሜሪካውያንን ለማስፈር ተስማሚ ቦታ ለመፈለግ ተወካዮችን ወደ አፍሪካ ላከ።
እነዚህ መልዕክተኞች መጀመሪያ ላይ መሬታቸውን ለመሸጥ ፈቃደኛ ባልሆኑ የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ተቃውሞ ገጠማቸው።
ከሁለት ዓመት በኋላ ሦስት የኤሲኤስ አባላት እና 88 ነፃ የወጡ ጥቁር አሜሪካውያን ከኒው ዮርክ በመርከብ ተሳፍረው አትላንቲክን ተሻገሩ።
በሴራሊዮን የባሕር ዳርቻ በሼርብሮ ደሴት ሰፈሩ።
ነገር ግን ብዙ ችግር የገጠማቸው ሲሆን፣ አብዛኞቹም በወባ ሞቱ።
ኤሲኤስ እስከ 1821 ድረስ ለቅኝ ግዛት የሚሆን ምቹ ቦታ ፍለጋውን ቀጠለ።
በ1821፣ በግምት 58 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው እና 5 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው መሬት በካቦ ሜሱራዶ የባሕር ዳርቻ ከአካባቢው መሪዎች መግዛት ችሏል።
ክፍያ የተፈፀመው ራም (rum) በተሰኘው የአልኮል መጠጥ፣ በጦር መሳሪያዎች፣ በተለያዩ ስጦታዎች እና ሌሎች 300 ዶላር ዋጋ ባላቸው እቃዎች ነው።
የአሜሪካ ቅኝ ግዛት ማኅበር እና የአሜሪካ ሠፋሪዎች መምጣት በአካባቢው ነዋሪዎች፣ ከተለያዩ ጎሳዎች በተውጣጡ እና ከአውሮፓውያን ጋር ለዘመናት ግንኙነት በነበራቸው ማኅበረሰቦች መካከል አለመግባባትን ፈጠረ።
"ላይቤሪያን በመመሥረት ዙሪያ በአፍሪካ ላይ የነበረው አለመቻቻል እና ዘረኝነት ላይ የተመሠረተ ፍረጃ ተጽዕኖ አድርጓል" ይላሉ ብሬወር።
"አንዱ የተዛባው አመለካከት አፍሪካውያን ኋላ ቀር፣ የተነጠሉ ሕዝቦች፣ ለቀሪው ዓለም እውቀት የሌላቸው ናቸው የሚለው ነው።"
"ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ወደ ባሕር ዳርቻው ከሚመጡ መርከቦች ጋር ይገናኙ ነበረ፤ የባሪያ ንግድን ጨምሮ የአትላንቲክ ንግድ አካል ነበሩ" ይላሉ ፓወር ግሪን።
ፓወር ግሪን የኤሲኤስ እና የአሜሪካ ሠፋሪዎች ወደ አካባቢው መምጣት የሰዎችን ዝውውር ብቻ ሳይሆን የምግብ እና ሌሎች ሸቀጦችን ለመርከቦቹ የሚሸጡትን በማስተጓጎሉ በክልሉ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ያስታውሳሉ።
"የተወሰነው ተቃውሞ የመጣው በባሪያ ንግድ ላይ ከተሰማሩት አፍሪካውያን ነው" ያሉት ተመራማሪው፣ ይህ ገፅታ የላይቤሪያ መሥራቾች የባሪያ አሳዳሪነትን የማስቆም እንቅስቃሴ አካል እንደሆኑ ያሳያል።

የፎቶው ባለመብት, LIBRARY OF CONGRESS, USA
የመጀመሪያ ችግሮች እና ውጥረቶች
በስፍራው ቀድመው የደረሱት አፍሪካ አሜሪካውያን በሚያዝያ 1822 ከዩናይትድ ስቴትስ የመጡ ሰዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀበሉ።
ከሁለት ዓመት በፊት በሸርብሮ ደሴት ላይ የሰፈረው ቡድን ወደ አዲስ አካባቢ ተዛወረ።
ግዛቱ ጥቁር አሜሪካውያንን ለማስፈር የተቋቋመ ቢሆንም፣ ሕዝቡ በመጀመሪያ የሚተዳደረው በአሜሪካ የቅኝ ግዛት ማኅበር ነጭ ተወካይ ስር ነበር።
እአአ በ1824 ለፕሮጀክቱ የገንዘብ ድጋፍ ላደረጉት የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጄምስ ሞንሮ ክብር ሲባል ዋና ከተማዋ ሞንሮቪያ ተባለች።
በቀጣዮቹ አሥርት ዓመታት ውስጥ ከ13 ሺህ በላይ አሜሪካውያንን የተቀበለችው ላይቤሪያ ግዛቷን አስፋፍታለች።
በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የባሪያ ንግድ ዝውውር መከልከሉን ተከትሎ በሕገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ መርከቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል በሺህ የሚቆጠሩ በባርነት የተያዙ አፍሪካውያን ወደዚህች አገር ተልከዋል።
በአሜሪካ ቅኝ ግዛት ማኅበር አነሳሽነት የተለያዩ ግዛት ማኅበሮችም በአቅራቢያው ያሉ መሬቶችን መያዝ እና ጥቁር አሜሪካውያንን ወደ አካባቢው መላክ ጀመሩ፤ በዚህም የላይቤሪያ ግዛት ተስፋፋ።
የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት በብዙ ፈተናዎች የተሞሉ ነበሩ።
በመጀመሪያዎቹ ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በወረርሽኝ እና በታጣቂዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች ተገድለዋል።
ስደተኞቹ የአፍሪካ ዝርያ ያላቸው ቢሆንም አብዛኞቹ የተወለዱት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ስለሆነ የአገሩን ቋንቋ ወይም ልማድ አያውቁም።
በአፍሪካ የተወለዱትም ቢሆኑ በልጅነታቸው ከየት አካባቢ እንደ ተወሰዱ የሚያስታውሱት ጥቂቶች ነበሩ።
በተጨማሪም ከአህጉሪቱ ስፋት እና ልዩነት አንጻር አሁን የሚኖሩበት አካባቢ ቅድመ አያቶቻቸው የተወሰዱበት ስፍራም አይደለም።
አሜሪካዊው ዊሊያም በርክ በ1858 በጻፈው ደብዳቤ ላይ "ወደ አፍሪካ የሚመጡ ሰዎች፣ በአዲስ አገር እንደሚያጋጥመው (የመጀመሪያዎቹ ሠፋሪዎች) ብዙ ችግሮች እንደሚገጥሟቸው መጠበቅ አለባቸው" ብለዋል።
እአአ በ1853 ነፃ ከወጡ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በርክ እና ባለቤቱ ሮዛቤላ ከባልቲሞር ሜሪላንድ ከአራት ልጆቻቸው ጋር ወደ ላይቤሪያ ለመጓዝ በመርከብ ተሳፈሩ።
አንጥረኛ ሆኖ የሰለጠነው በርክ በአዲሱ ቤቱ የላቲን እና የግሪክ ቋንቋ አጥንቶ የፕሬስባይቴሪያን ሃይማኖት አገልጋይ ሆነ።
በኮንግረስ ቤተ መጻሕፍት ተጠብቀው የቆዩት የእርሷ ደብዳቤዎች የላይቤሪያ መሥራች አባቶች ያጋጠሟቸውን ችግሮች ብቻ ሳይሆን በአዲሱ ሕይወታቸው ያላቸውን እርካታ ይገልፃሉ።
ሮዛቤላ በ1859 "አፍሪካን እወዳታለሁ፤ እናም በአሜሪካ አልለውጣትም" ስትል ጽፋለች።
በርክም እንዲህ ሲል ጽፏል፤ "ማንኛውንም ነገር ጠብቄያለሁ እና አልተከፋሁም ወይም ተስፋ አልቆረጥኩም። በአፍሪካ ከኖርኩበት ጊዜ ጀምሮ ጌታ አብዝቶ ባርኮኛል፤ ለዚህም መቼም በበቂ ሁኔታ ማመስገን እንደማልችል ይሰማኛል።"
እነዚህ ቀደምት ስደተኞች በዩናይትድ ስቴትስ የለመዱትን የእንግሊዝኛ ቋንቋ፣ አለባበስ እና የሥነ ሕንጻ ዘይቤ በመጠበቅ ላይቤሪያ ውስጥ ብዙ የአሜሪካን ማኅበረሰብ ገፅታዎችን ፈጥረዋል።
የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የሚታወሱት በግዛት ማስፋፋት ምክንያት በተከሰቱ ግጭቶች ብቻ ሳይሆን፣ በአገሬው ተወላጆች እና በአዲስ መጤዎቹ መካከል በተፈጠረ ውህደት፣በትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ በቤተ ክርስቲያን ምሥረታ እና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ባለ ግንኙነት ጭምር ነው።
ይህ ውህደት በባህል፣ በቋንቋ፣ በምግብ እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ድብልቅ የሆነ ማኅበረሰብ እንደፈጠረ ብሬወር ይናገራል።

የፎቶው ባለመብት, U.S. LIBRARY OF CONGRESS
ነጻነት እና የእርስ በርስ ጦርነት
እአአ በ1847 ቅኝ ግዛቱ ከአሜሪካ የቅኝ ግዛት ማኅበር ነፃ መውጣቱን አውጆ በዓለም ላይ ከሄይቲ ቀጥሎ ሁለተኛው የጥቁር ሪፐብሊክ ሆነ።
በ1829 ላይቤሪያ የገባው እና በቨርጂኒያ የተወለደ ጥቁር አሜሪካዊ ጆሴፍ ጄንኪንስ ሮበርትስ ፕሬዝዳንት ሆኖ ተመረጠ።
ዋሽንግተን ላይቤሪያን በመፍጠር ረገድ ሚና ቢኖራትም በዩናይትድ ስቴትስ ባለው ባርነት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተጽእኖ በመፍራት አዲሲቷን አገር ወዲያውኑ እውቅና አልሰጠችም።
ሁለቱ አገራት በ1862 በአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሥርተዋል።
በዩናይትድ ስቴትስ ቀደም ሲል በባርነት የተያዙ ሰዎች በፈቃደኝነት ወደ አፍሪካ ይመለሱ የሚለው ሃሳብ ለብዙ አሥርት ዓመታት ድጋፍ አግኝቶ የቆየ ነበር።
ነገር ግን ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሄደው ባሪያ ማስተዳደርን በሚደግፉ ሰዎች ምክንያት የአሜሪካ ቅኝ ግዛት ማኅበር ተቀባይነቱን እያጣ መጣ።
በጥቁር ሕዝቦች መካከል ግን ወደ አፍሪካ የመመለስ እንቅስቃሴዎ የበለጠ ትኩረት አገኘ።
ላይቤሪያ እና በርካታ የአፍሪካ አገራት ለበርካታ አሥርት ዓመታት ጥቁር አሜሪካውያንን፣ በዩናይትድ ስቴትስ የሲቪል መብቶች እንቅስቃሴ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት በ1960ዎቹን ጨምሮ ሲቀበሉ ነበር።
"ወደ አፍሪካ የመመለስ ሃሳቦች ተወዳጅነት ተስፋፋ፣ ከሰመ እንደገና አንሰራራ" ይላሉ ብሬወር።
በ1980ዎቹ መገባደጃ ላይ ላይቤሪያ ከ200 ሺህ የሚበልጡ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ የእርስ በርስ ጦርነት ገጠማት። ለግጭቱ መንስዔ ነው የተባለው ከአሥርት ዓመታት በፊት በስደተኞች እና በአገሬው ተወላጆች መካከል የነበረው አለመግባባት እና አድልዎ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።
አሜሪካ የተወለዱ ላይቤሪያውያን የአካባቢው ተወላጆች ብዝበዛን እና አድልዎ የሚፈጽም ልሂቃን ፈጥረዋል የሚል ትችት ይቀርባል።
ነገር ግን ብሬወር፣ፓወር ግሪን እና ሌሎች የታሪክ ተመራማሪዎች ይህ የመጀመሪያዎቹ ሰፋሪዎች ከመጡ ከመቶ ዓመት ገደማ በኋላ እንጂ የአገሪቱ መሥራቾች ውጤት እንዳልሆነ አጽንኦት ይሰጣሉ።
ፓወር ግሪን በ1926 ላይቤሪያ ውስጥ ከዓለም ትልቁ የጎማ ዛፍ እርሻዎችን ያቋቋመውን እና በቀጣዮቹ አሥርት ዓመታት የአገሪቱን ኢኮኖሚና ፖለቲካ ለመቆጣጠር የሞከረውን ኩባንያ በመጥቀስ ሲናገር "አንዳንድ የብዝበዛ ውንጀላዎች በ1920ዎቹ፣ፋየርስቶን በተመሠረተበት ጊዜ የተፈጸሙ ናቸው" ይላል።
"ላይቤሪያውያን (በ19ኛው ክፍለ ዘመን) ብዙ ጊዜ እንደሚባለው የዘር ክፍፍል መፍጠር አልቻሉም።ይህ ደግሞ ትልቅ ትርጉም አለው። አሁን ላይቤሪያዊ ከሆነው አጠቃላይ ሕዝብ ውስጥ ሦስት በመቶውን ብቻ ነው የሚይዙት" ሲል ፓወር ያስረዳል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የታሪክ ተመራማሪዎች እንደሚገልጹት የማኅበራዊ ክፍፍል ሥርዓት የተፈጠረው በ19ኛው ክፍለ ዘመን የአገሪቱ መሥራቾች ሳይሆን፣ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ አገሪቱ በመጡ እና የአገሪቱን የተፈጥሮ ሃብት በበዘበዙ ትላልቅ ኩባንያዎች ነው።
"መሬትን ከላይቤሪያ ሕዝብ የወሰደው ማን ነው? ትላልቅ ከበርቴ ኩባንያዎች ናቸው" ሲሉ ብሬወር ያስረዳሉ።
"ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ከበርካታ አሥርት ዓመታት በኋላ ለተከሰቱት ስህተቶች፣ ክፋቶች፣ ችግሮች፣ እና ጉድለቶች የአገሪቱን መሥራቾች ተጠያቂ ማድረግ ይፈልጋሉ።"















