የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ደመዛቸውን 40 በመቶ እንደሚቀንሱ አስታወቁ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ቦአካይ ደመወዛቸውን 40 በመቶ እንደሚቀንሱ አስታወቁ።
ፕሬዚዳንቱ እንዲህ አይነት እርምጃ የወሰዱት ተጠያቂ አስተዳደር በመፍጠር አርዓያ ለመሆን እና ከላይቤሪያውን ጋር ያላቸውም አጋርነት ለማሳየት እንደሆነም ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል።
በኑሮ ውድነት ምሬት የገባቸው ላይቤሪያውያን አንደኛው ቅሬታ የሚያነሱት ጉዳይ የመንግሥት ሰራተኞች ደመወዝ ነው።
በላይቤሪያ ውስጥ በአማካኝ ከአምስቱ አንዱ ሰው ከ2 ዶላር ባነሰ ዕለታዊ ገቢ ኑሯቸውን ለመግፋት ተገደዋል።
ፕሬዚዳንቱ ከጥቂት ወራት በፊት ዓመታዊ ደመወዛቸው 13 ሺህ 400 ዶላር እንደሆነ ገልጸው አሁን ባቀረቡት 40 በመቶ ቅነሳ ወደ 8ሺህ ዶላር ያደርሰዋል።
ከሳቸው በፊት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዊሃ ደመወዛቸውን 25 በመቶ ቀንሰው ነበር።
አንዳንዶች የፕሬዚዳንቱን እርምጃ ቢያደንቁም ሌሎች ግን እንደ ዕለታዊ አበል እና የህክምና ሽፋን ጥቅማጥቅሞችን እንደሚያገኙ የጠቀሱ በበኩላቸው ይህ በእውነት መስዋዕትነት ነው ወይ ሲሉም ይጠይቃሉ።
የፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት የዚህ ዓመት በጀት ወደ 3 ሚሊዮን ይጠጋል።
ሴንተር ኦፍ ትራንስፓረንሲ ኤንድ አካውንተብሊቲ ኢን ላይቤሪያ የተባለው ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት የፕሬዚዳንቱን የደመወዝ ቅነሳ መልካም ተግባር እንደሆነ ገልጿል።
“የተቀነሰው ደመወዝ የት እንደሚሄድ እና ማህበረሰቡን በበጎ ለመጥቀም ይውላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ሲል ማዕከሉ ለቢቢሲ ገልጿል።
ድርጅታቸው የመንግሥት ግልጽነት እንዲሰፍን ዘመቻ እያካሄደ የሚገኘው ደብሊው ላውረንስ ያሉ በበኩላቸው የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ “በጣም የሚያስመሰግን ነው” ሲሉ ገልጸው “አመራር መሰጠት ያለበት ከላይ ነው” ብለዋል።
አክለውም የፕሬዚዳንቱ ጥቅማጥቅሞች በመጪው ዓመት በጀት ለግምገማ እንደሚቀርቡ ተስፋቸውን አጋርተዋል።
ደመወዛቸውን ከመቀነስም በተጨማሪ ፕሬዚዳንቱ የመንግሥት ሰራተኞች “ለአገሪቱ እያደረጉት ላለው አስተዋጽኦ ፍትኃዊ ክፍያ እንዲያገኙ” ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
ባለፈው ሳምንት የዕለት ተግባራቸውን ለመከወን የሚያስፈልጋቸውን መኪኖች እንዳልተሰጣቸው የፓርላማ አባላቱ ቅሬታ አቅርበው ነበር።
ተቃውሟቸውንም ለማሳየት በላይቤሪያ “ኬህ ኬህ” ተብለው በሚጠሩት ባጃጆች ወደ ፓርላማ አቅንተው ነበር።
የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዊሃን በምርጫ አሸንፈው በጥር ወር ወደ ስልጣን የመጡት ጆሴፍ ቦኣካይ ሙስናን እና የገንዘብ ምዝበራን ለመዋጋት ቃል ገብተዋል።
ፕሬዚዳንቱ ያላቸውን ንብረት ለህዝብ ይፋ ከማድረግ በተጨማሪ የፕሬዚዳንቱ ቢሮ ኦዲት እንዲደረግ አዘዋል። የኦዲቱ ውጤት እስካሁን ለህዝብ አልተገለጸም።












