ኔታኒያሁ የፈረንሳዩ ማክሮን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ይጣል ማለታቸው ‘አስነዋሪ ነው’ ሲሉ ቁጣቸውን ገለፁ

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ የፈረንሳዩ ማክሮን ለእስራኤል የሚሰጠው የጦር መሣሪያ ላይ ማዕቀብ መጣል አለበት ማለታቸውን ተችተዋል።

ፕሬዝደንት ማክሮን ፍራንስ ኢንተር ለተሰኘው ራዲዮ በሰጡት ቃለ-ምልልስ “አሁን ፊታችንን ወደ ፖለቲካዊ መፍትሔ ማዞር ግድ ይለናል፤ በጋዛ ላለው ጦርነት የጦር መሣሪያ መላክ ማቆም አለብን” ሲሉ ተናግረዋል።

ቅዳሜ ዕለት በፓሪስ በተካሄደ ስብሰባ ላይ የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ምንም እንኳ የተኩስ አቁም ጥሪ ቢደረግም በጋዛ ያለው ግጭት መቀጠሉ እንዳሳሰባቸው ገልፀዋል።

ፕሬዝደንቱ አክለው እስራኤል ወደ ሊባኖስ እግረኛ ጦር መላኳ ትክክል አይደለም ሲሉ ትችታቸውን አሰምተዋል።

ለዚህ ንግግር ምላሽ የሰጡት ኔታኒያሁ “ሀፍረተኞች ናችሁ” ሲሉ ማክሮን እና ሌሎች የጦር መሣሪያ ማዕቀብ መጣል አለበት ያሉ ምዕራባዊያን መሪዎችን ወርፈዋል።

ኔታኒያሁ በቢሯቸው በኩል በተለቀቀ የቪድዮ መልዕክት “እስራኤል የእናንተ ድጋፍ መጣም አልመጣም ማሸነፏ አይቀርም” በማለት ማዕቀብ ይጣሉ መባሉን “አስነዋሪ” ብለውታል።

ባለፈው ማክሰኞ ነው ኢማኔኤል ማክሮን ለፈረንሳዩ ራዲዮ ቃላቸውን የሰጡት። ነገር ግን ቃለ-ምልልሱ የተላለፈው ቅዳሜ ዕለት ነው። ማክሮን ሀገራቸውን “ፈረንሳይ ለእስራኤል ምንም ዓይነት የጦር መሣሪያ እየላከች አይደለም” ብለዋል።

አክለው “እኔ እንደሚመስለኝ የምንለው ነገር ሰሚ ጆሮ እያገኘ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።

የፈረንሳዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢማኔኤል ማክሮን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“እኔ ስኅተት ነው ብዬ ነው የማስበው። ለእስራኤል ደኅንነትም ቢሆን ይህ ተገቢ አይደለም” ያሉት ማክሮን በቀጣናው ያለው ግጭት እስራኤል “እንድትጠላ” ምክንያት እየሆነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አክለው አሁን “ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው” ጉዳይ በሊባኖስ ያለው ግጭት መሆኑን አውስተው “ሊባኖስ ሌላኛዋ ጋዛ ልትሆን አይገባም” ብለዋል።

ለማክሮን ንግግር ምላሽ የሰጠው የኔታኒያሁ ቢሮ ከእስራኤል ጋር የማይቆም የትኛውም ሀገር ከኢራን እና ከአጋሮቿ ጋር እንደቆመ ነው የሚቆጠረው ብሏል።

“ፕሬዝደንት ማክሮን እና አንዳንድ ምዕራባዊያን መሪዎች ወደ እስራኤል የሚላከው የጦር መሣሪያ ላይ ማዕቀብ መጣል አለበት እያሉ ነው። ሀፍረት ይደርባቸው።”

የማክሮን ቢሮ ከዚህ ምላሽ በኋላ በለቀቀው መግለጫ ፈረንሳይ “የእስራኤል የምን ጊዜም ወዳጅ ናት” ብሎ ነገር ግን ኔታኒያሁ የሰጡት ምላሽ “ቁጣ ያዘለ እና ከእስራኤል እና ፈረንሳይ የወዳጅነት መንፈስ ያፈነገጠ” መሆኑን ጠቅሷል።

ፓሪስ በሚገኘው ግራንድ ፓሌይ በተዘጋጀው 19ኛው የፍራንኮፎኒ ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት ማክሮን ሀገራቸው እና ዩናይትድ ስቴትስ በሊባኖስ የተኩስ አቁም እንዲደረስ ጥሪ ማቅረባቸውን አሳውቀዋል።

“ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ሌላ አማራች መፈለጋቸው ያሳዝናል። በተለይ ደግሞ በሊባኖስ ምድር ላይ የመሬት ለመሬት ኦፕሬሽን መጀመራቸው ይቆጨኛል” ብለዋል።

ቢሆንም እስራኤል ራሷን የመከላከል መብት አላት ሲሉ ያስረገጡት ማክሮን በጋዛ ታግተው የተወሰዱ ፈረንሳዊያን እስራኤላዊያን ቤተሰቦችን ሰኞ ዕለት አግኝተው እንደሚያነጋግሩ ገልፀዋል።

በአውሮፓውያኑ ሰኞ ጥቅምት 7፤ 2024 ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈፀመው ጥቃት አንደኛ ዓመት ይዘከራል። ባለፈው ዓመት ጥቅምት 7 ነው የፍልስጤሙ ሚሊሻ ቡድን ሐማስ 1200 እስራኤላዊያንን ገድሎ 251 ገደማ አግሮ የወሰደው።

ይህን ተከትሎ እሰራኤል በጋዛ በከፈተችው ጦርነት ከ40 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።