እስራኤል መፍጠር የምትፈልገው መካከለኛው ምሥራቅ ምን ይመስላል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ‘አዲስ መካከለኛው ምሥራቅ’ ሲሉ ይሰማል።
እስራኤል ከቀድሞውም በቀጠናው አዲስ የኃይል አሰላለፍና ካርታ ትሻለች።
ከሐማስ የጥቅም 7 ጥቃት በኋላ ያለውን ቀውስ በማጣቀስ “ይህም ከመቼውም በላይ ቅርብ ነው” ብለው የሚያምኑ አሉ።
አወዛጋቢው የእስራኤል ካርታ
እስራኤላውያን ባለሥልጣናት በዓለም አቀፍ መድረኮች ይዘው የሚታዩት የእስራኤል ካርታ ፍልስጤምን ያላካተተ ነው።
በመንግሥታቱ ድርጅት ውይይት ኔታንያሁ ንግግር ሲያደርጉ ሁለት ካርታ አሳይተዋል።
አንደኛው ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት ያደረጉና በማድረግ ላይ ያሉ አገራትን ማለትም ግብፅ፣ ሱዳን፣ ዩኤኢ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ባሕሬን እና ዮርዳኖስን በአንረጓዴ ቀለም የሚያሳይ ነው።
ሁለተኛው ካርታ ኔታንያሁ “የተረገመ” ያሉት ሲሆን ይህም ኢራን፣ ሶርያ፣ ኢራቅ፣ የመን እና ሊባኖስን በጥቁር የሚያሳይ ነው።
የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ተይፕ ኤርዶዋን የእስራኤልን “አደገኛ አካሄድ” በቅርቡ ኮንነዋል።
“በታይግረስና ኤፍራጠስ ያለውን ቤታችንን ያፈርሱታል። ጋዛን ማውደም ብቻ አይበቃቸውም” ብለዋል።
በኬምብሪጅ ሚድል ኢስት ሴንተር የሚሠራው ያዚድ ሳይግ እንደሚለው፣ የኔታንያሁን አጀንዳ የሚያሳይ ንግግር ነው።
“አዲሱ ኔታንያሁ የሚፈልገው መካከለኛው ምሥራቅ ፍልስጤምን ቅኝ ግዛት ውስጥ የሚያስገባ ነው” ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል በተለይ በዌስት ባንክ የግዳጅ ይዞታዋን እንደምታስፋፋ የምትናገረው በግልጽ ነው።
የአረብ አገራትና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ትችት ቢሰነዝርም የመስፋፋት ዕቅድን በይፋ አስታውቃለች።
በዋሽንግተን ኢንስቲትዩት ፎር ኒር ኢስት ፖሊሲ የሚሠራው ዴቪድ ሸንከር እንደሚለው፣ በእስራኤል ቀኝ ዘመም መንግሥት ውስጥ እስራኤልና ፍልስጤም ሁለት አገራት ሆነው መቀጠላቸውን የማይደግፉ ብዙ ሚኒስትሮች አሉ።
“ከ1993 የኦስሎ ስምምነት በኋላ አሁን ነገሮች የበለጠ እየጠበቡ ይመስለኛል። አሜሪካ ፍልስጤምን ላላካተቱ ለእስራኤል ካርታዎች ይሁንታ ትሰጣለች ብዬ አላስብም። የእስራኤል አዲስ መካከለኛው ምሥራቅ የኢራን ስጋት የሌለበት ነው” ይላል።
‘ኢራን ስጋት የማትሆንበት’ መካከለኛው ምሥራቅ
የቀድሞ የእስራኤል የደኅንነት ባለሙያ ሚሪ ኢሰን “እስራኤል አዲስ መካከለኛው ምሥራቅ መፍጠር አትሻም። ግን ኢራን የቀጠናውን አሰላለፍ እንድትወስን አትፈልግም” ይላል።
ያዚድ በበኩሉ “የጥቅምት 7 ጥቃት ካሳደረው ሀፍረት አንጻር ኔታንያሁ የኢራንን ኒውክሌር ፕሮግራም ማቆም ይፈልጋል” ይላል።
የሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስረላ መገደል የአካባቢውን ፖለቲካ የለወጠ ነው።
ኢራን በምላሹ ባለስቲክ ሚሳዔል ተኩሳለች። ለሐማስ የፖለቲካ ኃላፊ ኢስማዔል ሐኒያ ግድያም ምላሽ ነው። ምዕራባውያኑ ስጋት ገብቷቸዋል።
እስራኤል ለኢራን ባሻት ጊዜ የመልስ ምት እንደምትሰጥ አስታውቃለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ወታደራዊ መፍትሄ
አሜሪካ የእስራኤል ቀንደኛ ደጋፊ ናት። እስራኤል ቀጠናዊ የበላይነት እንድታስጠብቅና በአካባቢው ወታደሮቿን እንድታሰማራ ትረዳለች።
አሜሪካ እርዳታዋን መቀጠል የምትችለው ግን እስራኤል ቀይ መስመር እስካላለፈች ድረስ ነው ስትል አስታውቃለች።
ይህም የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራምን አለመምታትና የእስራኤልና ፍልስጤም ሁለት አገራትነት ዕውቅና አለመንፈግ ነው።
ተንታኙ እንደሚለው፣ የእስራኤል ወታደራዊ እንቅስቃሴ ኢራን የጦር መሣሪያ መላኳንና በቀጠናው ለእስራኤል የደቀነችው አደጋ ምላሽ ነው።
ዴቪድ በበኩሉ፣ እስራኤል ኢራን በቀጠናው ያሏትን የእጅ አዙር አጋሮች ማዳከም ትሻለች ይላል።
አረብ አገራት ድጋፍ ባያደርጉም አዲስ አሰላለፍ ትፈልጋለች።
“ሐማስ ያለ ፍልስጤም ባለሥልጣናትና የአረብ አገራት ጥረት ሲቀጥል ሄዝቦላህም ያለ ሊባኖስ ማኅበረሰብ ጥረት ይቀጥላል” ይላል።
እስራኤል ደኅንነቷን፣ ምጣኔ ሃብቷንና ቴክኖሎጂዋን ማሳደግ እንደምትሻ ያምናል።
ይህንን የምታደርገው “ኢራን ጠላት ናት” ብለው ከሚያምኑ ጋር በመተባበር ነው።
አሜሪካ ግን ምጣኔ ሃብታዊና ወታደራዊ እድገት እንዲመጣ በማገዝ እስራኤል የቀጠናውና የአረብ አገራት ጠላት ሳትሆን ኢራንን ለመዋጋት አጋር አገር ናት የሚል ምሥል ለመፍጠር ትሞክራለች።
እስራኤል ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ግንኙነቷን ለማደስ ሞክራለች።
በኢራን ያለው የሺዓ አብላጫ ያለው አመራር በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ተጽዕኖ በጋራ መቃወም አንደኛው የስምምነቱ መነሻ ቢሆንም፣ ሳዑዲ ግን በይፋ በፋይናንሻል ታይምስ ላይ ከእስራኤል ጋር እንደማትስማማ አስታውቃለች።
ምክንያቷም የፍልስጤም አገር ሆኖ አለመፈጠር ነው።
ከጥቅምት 7 ጥቃት በፊት አረብ አገራት ማለትም ግብፅ፣ ሶርያ፣ ሊባኖስና ዮርዳኖስ የፖለቲካና ምጣኔ ሃበት አካሄዳቸውን እየለወጡ ነበር።
“እነዚህ አገራት ለፍልስጤም እንደሚያዝኑ ጥያቄ የለውም። ሆኖም ችግሩ ከእስራኤል ጋር ብቻ ሳይሆን ከፍልስጤም ውሳኔ ሰጪዎች ጋር መሆኑን ይገነዘባሉ። ስለዚህ በእስራኤልና በፍልስጤም ግጭት ውስጥ የየአገራቸውን ፍላጎት ለማስቀደም መረጡ” ይላል ዴቪድ።
የምጣኔ ሃብት ትስስር
ከጥቅምት 7 በፊት የተደረሱ ስምምነቶች የመከላከያ፣ የበይነ መረብ ደኅንነትና የኃይል አቅርቦትን ይጨምራሉ።
ጦርነቱ እስራኤል ከአረብ አገራት ጋር ያላትን የንግድ ትስስር አቀዛቅዟል።
እስራኤል ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ግብፅ፣ ባሕሬንና ሞሮኮ ጋር ንግድ ጨምራ ነበር።
የእስራኤል ጋዜጣ ማሪቭ እንዳለው፣ እስራኤል ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጋር የንግድ መስመር ለመዘርጋት ተስማምታለች።
መስመሩ በሳዑዲ አረቢያ፣ ዩርዳኖስና ግብፅ ያልፋል።
ግብፅ የኃይል መስመሯን የምትዘውረውም በእስራኤል ነዳጅ ነው።
“እስራኤል ዲፕሎማሲ፣ የምጣኔ ሃብት ትስስርና ወታደራዊ እንቅስቃሴን ተጠቅማ አዲስ ቀጠናዊ አሰላለፍ መፍጠር አለባት” ይላል ዴቪድ።
ያዚድ በበኩሉ “በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄድ ለውጥ ከዓለም ውጥረት ማለትም ከአሜሪካ፣ ሩስያና ቻይና ወይም የአውሮፓ ውስጣዊ ፖለቲካ የተነጠለ አይደለም” ይላል።
ቀጠናዊና ዓለም አቀፍ ስጋቶች አሉት። እነዚህም ዓለም አቀፋዊ ግጭትን ያባብሳሉ ብሎ ይሰጋል።












