ካማላ ወይስ ትራምፕ? ለክሪፕቶ ከረንሲ የተሻሉ የሚሆኑት ፕሬዝደንት ማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የክሪፕቶፕ ኢንደስትሪው “በማጭበርበሮች፣ በወንበዴዎች እና በማታለሎች የተሞላ ነው” ሲሉ አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ የፋይናንስ ተቆጣጣሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በዓለም ዙሪያ ኢንቨስት የሚያደርጉ ሰዎች በጣም ብዙ ገንዘብ አጥተዋል” ምክንያቱም ደግሞ የክሪፕቶ ኩባንያዎቹ የምናወጣቸውን መመሪያዎች ባለመከተላቸው ነው ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ ሴኩሪቲስ ኤክስቼንጅ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ጋሪ ጌንስለር ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪው አንቀሳቃሾች ለወደፊት ምቹ ሕጎችን ያወጡልናል በማለት የአሜሪካ ምርጫ ላይ ተጽእኖ ለማሳረፍ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እየለገሱ ነው።
በዶናልድ ትራምፕ እና በካማላ ሃሪስ መካከል ካለው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በተጨማሪ የተወካዮች ምክር ቤት 435 አውራጃዎች ለዳግም ምርጫ ተዘጋጅተዋል። የአገሪቱ ሴኔት ካሉት 100 መቀመጫዎች መካከል በ33ቱ ላይም ምርጫ ይደረጋል።
በዓለም ላይ በጣም አከራካሪ ከሆኑት ቴክኖሎጂዎች አንዱ የሆነው የክሪፕቶፕ ዕጣ ፈንታ በዶናልድ ትራምፕ እና በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዘንድ በተለያየ ዓይን ይታያል።
አሜሪካን “የዓለማችን ክሪፕቶ ዋና ከተማ” ትሆናለች ሲሉ ትራምፕ ቃል ገብተዋል። ከአሜሪካ መንግሥት የወርቅ ክምችት ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ “የቢትኮይን ክምችት” እንደሚኖር በመግለጽ የክሪፕቶ አድናቂዎችን ልብ እያቀለጡ ቆይተዋል።
በቅርቡም ዎርልድ ሊበርቲ ፋይናንሻል የሚባል አዲስ የክሪፕቶ ንግድ ሥራ አስጀምረዋል። ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም “እኔ እንደማስበው ክሪፕቶ ትኩረት ልንሰጣቸው ከሚገቡን ነገሮች አንዱ ነው” ሲሉ አክለዋል።
ትራምፕ ከሦስት ዓመታት በፊት ከነበራቸው አቋም አንጻር ትልቅ ለውጥ ያሳዩበት ነው። በወቅቱ ቢትኮይንን “እንደ ማጭበርበሪያ” እና ለአሜሪካ ዶላር ስጋት እንደሆነ አድርገው አጣጥለውት ነበር።
የትራምፕ አዲስ ሃሳብ ካማላ ሃሪስን በምክትል ፕሬዝዳንትነት ካቀፈው ከባይደን አስተዳደር ጋር ፍጹም ተቃርኖ ያለው ነው። ዋይት ሐውስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በክሪፕቶ ኩባንያዎች ላይ ከፍተኛ ዘመቻ አከናውኗል።
በመጋቢት ወር የኤፍቲኤክስ መሥራች እና መሪ የሆነው ሳም ባንክማን-ፍሪድ በዓለም ዙሪያ ካሉ ደንበኞች በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላሮችን ከሰረቀ በኋላ በማጭበርበር ወንጀል ተከሶ 25 ዓመታት እንዲታሰር ተፈርዶበታል። አብዛኞቹ ደንበኞቹ አሁንም ገንዘባቸውን ለማግኘት በሙከራ ላይ ናቸው።
በሚያዝያ ወር ደግሞ የዓለማችን ትልቁ የክሪፕቶ መገበያያ የሆነውን ባይናንስን የመሠረተው ቻንግፔንግ ዣሆ የአራት ወራት እስራት ተፈርዶበታል። ኩባንያው ደግሞ የ4.3 ቢሊዮን ዶላር ቅጣት ከፍሏል።
የዩናይትድ ስቴትስ የፍትህ ቢሮ በባይናንስ ላይ በከፈተበት ክስ ወንጀለኞች፣ ሕጻናት ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ እና አሸባሪዎች ገንዘብ እንዲያሸሹ መፍቀዱን አምኗል።
ባይናንስ በፍርድ ቤት የሚታይ ሌላም ክስ አለበት። ይህም ተቆጣጣሪው አካል ባለፈው ዓመት ብቻ ገና ብቅ እያሉ ካሉት ቴክኖሎጂዎች ትርፍ ለማግኘት በሚሞክሩ ድርጅቶች ላይ ከወሰዳቸው 46 የሕግ ማስፈጸም እርምጃዎች አንዱ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“ይህ አብሮ የመጣ መስክ በመሆኑ የክሪፕቶ ንብረቶቻቸውን [በስህተት] በአዲስ የሂሳብ መዝገብ ላይ ስለሚመዘግቡ ብቻ 'በጊዜ ሂደት የተሞከሩትን ሕጎች ማክበር አንፈልግም'” ይላሉ ሲሉ ጌንስለር ተናግረዋል።
ኢንቨስተሮችን ለመጠበቅ በማሰብ ከሕዝብ ገንዘብ ለመሰብሰብ የሚፈልጉ ኩባንያዎችን “አንዳንድ መረጃዎች እንዲያጋሩ” የሚያስገድዱ ሕጎች ተቋማቸው ከተመሠረተ ጀምሮ ሥራ ላይ እንደዋለ አብራርተዋል።
ይህ የሆነው እአአ በ1934 ሲሆን በ1929 በታዋቂው የዎል ስትሪት ኪሳራ ምክንያት ታላቁን የኢኮኖሚ ድቀት ተከትሎ የመጣ ነው።
“ክሪፕቶ ከአሜሪካ እና ከዓለም አቀፍ የካፒታል ገበያዎች አንጻር አነስተኛ ቢሆንም፣ ባለሀብቶች በካፒታል ገበያዎች ላይ ያላቸውን እምነት ሊያሳጣው ይችላል” ብለዋል ጌንስለር።
ክሪፕቶ ፈጣን፣ ርካሽ እና ደኅንነቱ በተጠበቀ መንገድ ፈንዶችን ለማንቀሳቀስ ይረዳል ሲሉ ደጋፊዎቹ ይከራከራሉ። የአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ ክሪፕቶን የሚጠቀሙ የአሜሪካውያን ቁጥር እአአ በ2021 ከነበረበት 12 በመቶ ባለፈው ዓመት ወደ 7 በመቶ ዝቅ ብሏል።
ካማላ ሃሪስ ስለ ክሪፕቶ ብዙም አልተናገሩም። ከአማካሪዎቻቸው አንዱ “በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና እንደዚህ ዓይነት ኢንዱስትሪዎች እያደጉ መሄዳቸውን የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎችን እንደሚደግፉ” መናገራቸውን ባለፈው ወር ገልጸዋል።
በቅርብ ጊዜ በአማካሪዎቻቸው እና በኢንዱስትሪው ሥራ አስፈፃሚዎች መካከል የተደረጉ ስብሰባዎች መተማመንን ለመፍጠር የሞከሩ ነበሩ። የክሪፕቶ አለቆችም በቀጣዩ ምርጫ ማንም ያሸንፍ ማን መጪው ጊዜ ብሩህ ስለመሆኑ ተስፋን እንዲሰንቁ አድርገዋል።
“ይህ ለአሜሪካ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በበቂ ሁኔታ ማስረዳት አልችልም” ሲሉ በስብሰባው ላይ ተገኙት እና ኮይን ቤዝ በተባለ የክሪፕቶ ኩባንያ ዋና የሕግ ባለሙያ የሆኑት ፖል ግሬዋል ተናግረዋል።
“አሜሪካ ለክሪፕቶ ገበያ ብቻ ሳይሆን ተያያዥ የሆኑ አብዛኞቹን ቴክኖሎጂዎችም እዚህ የተዘጋጁ ናቸው። የተቀረው ዓለም ዩናይትድ ስቴትስ እንቅስቃሴ እስክትጀምር እየጠበቀ እንዳልሆነ ልንዘጋው የሚገባን አይመስለኝም።”
ለዋይት ሐውስ የሚደረገው ፉክክር ጠንካራ ከመሆኑ አንጻር “እያንዳንዱ ድምጽ ወሳኝ ነው። ይህ ለክሪፕቶም ይሠራል” ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዚህ ዓመት በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኙ ክሪፕቶዎች ላይ የተወሰደው እርምጃ በአውሮፓም ተንጸባርቋል። የአውሮፓ ኅብረት በወንጀለኞች ጥቅም ላይ የሚውለው ክሪፕቶ የሚያደርሰውን አደጋን ለመቀነስ አዳዲስ ሕጎችን ለማውጣት በሚያዝያ ወር ተስማምቷል።
አንዳንድ አገራት እርምጃ ለመውሰድ ዘግየት ብለዋል። የቡድን 20 አባል አገራት ለክሪፕቶ አነስተኛ የሚሉትን መስፈርት ለማውጣት እየሠሩ ነው። ሆኖም ግን ሕጎቹ አስገዳጅ አይደሉም። አቀባበሉም አዝጋሚ ነበር።
ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ስንመለስ ክሪፕቶዎችን የሚቆጣጠር ሕግ በምክር ቤቱ ቢጸድቅም ሴኔቱ ግን አላሳለፈውም። ለተጠቃሚዎች አነስተኛ ጥበቃ ያደርጋል የሚል ትችት እየቀረበበት ነው።
የኮይን ቤዝ ባልረደባ የሆኑት ግሬዋል ሃሳቡን ይደግፋሉ። “ይህ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ኢንዱስትሪ አይደለም” በማለት ዘርፉ ልክ በሌሎች ላይ እንደሚተገበሩ ሕጎች በክሪፕቶ ላይ የሚተገበሩትም ተመሳሳይ መመዘኛዎች እንዲኖረው እንደሚፈልግ አክለው ተናግረዋል። በአጠቃላይ “የጠነከረም የላላም መሆን የለበትም” ብለዋል።
የክሪፕቶ ኢንደስትሪ አንቀሳቃሾች በመጪው የአሜሪካ ምርጫ ለንግድ ሥራው ስሱ ልብ ያላቸው ሕግ አውጭዎች እንዲመርጡ ለመርዳት ዕድል ፈጥሮላቸዋል።
ባለፈው ወር ብቻ ዘርፉ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ 119 ሚሊዮን ዶላር በልገሳ መልክ መስጠቱን ለትርፍ ያልተቋቋመው የፐብሊክ ሲቲዝን ጥናት አመልክቷል።
ገንዘቡ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው “የፖለቲካ ታሪኩ ምንም ይሁን ምን ክሪፕቶ የሚደግፉ ዕጩዎች እንዲመረጡ እና ክሪፕቶ ተቺዎችን ለማጥቃት ነው” ሲሉ የሸማቾች ተሟጋች የሆነው ድርጅት የምርምር ዳይሬክተር ሪክ ክሌይፑል ተናግረዋል።
ከኩባንያዎች ልገሳ አንጻር ከታየ ከየትኛውም ኢንዱስትሪ የበለጠ ወጪ አድርገዋል። ምክንያቱም “የአሜሪካ ኮንግረስ በጥያቄዎቻቸው ዙሪያ አነስተኛ ቁጥጥር እንዲያደረግ ተጽእኖ ለማሳደር እና የተጠቃሚዎችን ጥበቃን ለማዳከም እየሞከሩ ነው” ሲል አክለዋል።












