በአደጋ ውስጥ ሆነው መድኃኒት እና ሕክምና ፍለጋ ወደ ሜክሲኮ የሚጓዙት አሜሪካውያን

በቅርቡ በአሜሪካውያን ላይ ጥቃት በተፈጸመባት ማታሞሮስ ውስጥ ለጥበቃ የተሰማሩ ፖሊሶች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በቅርቡ በአሜሪካውያን ላይ ጥቃት በተፈጸመባት ማታሞሮስ ውስጥ ለጥበቃ የተሰማሩ ፖሊሶች

የዓለማችን ኃያል አገር አሜሪካ ዜጎች ርካሽ መድኃኒት እና ሕክምና ለማግኘት ወደ ጎረቤት ሜክሲኮ ይጓዛሉ። ነገር ግን ይህ ጉዞ በአደጋ የታጀበ ነው።

ባለፈው ሳምንት አራት አሜሪካውያን ከአገራቸው በስተደቡብ ወደምትገኘው ሜክሲኮ ውስጥ በዕፅ አዘዋዋሪዎች ታፍነው ታስደዋል።

ክስተቱ የተፈጠረው በሜክሲኮ ታማውሊፓስ ግዛት ማታሞሮስ ከተማ ነው።

አራቱ አሜሪካውያን ለኮስመቲክ (ውበት) ቀዶ-ሕክምና ተሽከርካሪያቸውን ይዘው ወደ ድንበር ከተማዋ ያቀናሉ።

ነገር ግን ከየት መጣ ሳይሉ የነበሩበት ተሽከርካሪ የጥይት ዝናብ ይወርድበታል። ከአራቱ አሜሪካውያን መካከል ሁለቱ ሲሞቱ ሁለቱ ተርፈዋል።

ፖሊስ ጉዳዩን ካጣራ በኋላ ወንጀሉን የፈፀሙት የአካባቢው ዕፅ አዘዋዋሪዎች መሆናቸውን ደርሶበታል።

የወደብ ከተማዋ ማታሞሮስ በጣም አደገኛ ከሚባሉ የሜክሲኮ ከተማዎች አንዷ ናት። ዕፅ አዘዋዋሪዎች አብዛኛውን ታማውሊፓስ ይቆጣጠሩታል። አንዳንዴ ከአካባቢው ባለሥልጣናት የላቀ ኃይል አላቸው።

ነገር ግን መሰል ከተሞች በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ርካሽ ሕክምና ፈላጊ አሜሪካዊያን መዳረሻ ናቸው። አብዛኞቹ አሜሪካ ውስጥ በአቅማቸው መታከም ስለማይችሉ ነው ወደ ሜክሲኮ የሚያቀኑት።

ወደ ሜክሲኮ መመላለስ የለመዱት አሜሪካውያን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያውቃሉ። ለምሳሌ ወደ ሜክሲኮ ሲዘልቁ መኪናቸውን አስመዝግበው የአገሪቱን ታርጋ መግጠም እና በእግር አለመጓዝ።

ሜክሲኮ ለዩናይትድ ስቴትስ ቅርብ ከመሆኗ አልፎ መድኃኒት በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረቧ ለአሜሪካውያን ተመራጭ ስፍራ ሆናለች።

“ይሄ ኢኮኖሚ ነው” ይላሉ የቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ የፍልሰት ጥናት ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ኔስተር ሮድሪጌዝ።

“መድኃኒት እና የሕክምና አገልግሎት ሜክሲኮ ውስጥ ርካሽ ነው። በተለይ ደግሞ የጥርስ ሕክምና። አሜሪካ ውስጥ የሚከፈለውን ሩብ ያክል ከፍሎ ጥርስ አሳጥቦ አሊያም ንቅለ-ተከላ አስደርጎ መመለስ ይቻላል” ይላሉ።

ምንም እንኳ የአሜሪካ የበሽታ ቁጥጥር እና መከላከል ማዕከል (ሲዲሲ) ሜክሲኮ ውስጥ የሚሰጠው ሕክምና ጥራት ይጎድለዋል ቢልም ፕሮፌሰሩ አሜሪካ ውስጥ የሚገኘው ሕክምና ሜክሲኮ ውስጥም ይገኛል ይላሉ።

ኒው ሲቲ ሜዲካል ፕላዛ የተባለው የሕክምና ማዕከል ሜክሲኮን ከአሜሪካ በሚለየው የድንበር አጥር አቅራቢያ ይገኛል

የፎቶው ባለመብት, AFP VIA GETTY IMAGES

የምስሉ መግለጫ, ኒው ሲቲ ሜዲካል ፕላዛ የተባለው የሕክምና ማዕከል ሜክሲኮን ከአሜሪካ በሚለየው የድንበር አጥር አቅራቢያ ይገኛል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሜክሲኮ የሕክምና ቱሪዝም ምክር ቤት ባወጣው መረጃ መሠረት አንድ ሚሊዮን ገደማ አሜሪካውያን በየዓመቱ ለሕክምና ወደ ሜክሲኮ ያቀናሉ።

ሜክሲኮ የተወለደችው የ58 ዓመቷ አሜሪካዊት ታይዴ ራሚሬዝ ከአስር ዓመት በላይ ወደ ሜክሲኮ እያቀናች ላለባት የጤና እክል ሕክምና ስታገኝ ኖሯለች።

ራሚሬዝ ከምትኖርበት ሳን አንቶኒዮ እስከ ኤግል ፓስ ድረስ ያለው የመኪና ጉዞ ከሁለት ሰዓት ተኩል በላይ ይወስዳል።

የምትሠራበት መሥሪያ ቤት የሕክምና ወጪዋን ቢሸፍንላትም እሷ የምታዋጣው ገንዘብ በጣም ብዙ ስለሆነ ነው ወደ ትውልድ አገሯ የምታቀናው።

ለቢቢሲ እንደተናገረችው ብዙውን ጊዜ አንድ ቀን መድባ ወደ ሜክሲኮ ብታቀናም እስካሁን አደጋ አጋጥሟት አያውቅም።

ሊያጋጥማት የሚችለው አደጋ ግን ሳያሳስባት ቀርቶ አይደለም። በምሽት ተጉዛ አታውቅም። ቀጥታ ወደ ሕክምና ሄዳ ወዲያውኑ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ትመለሳለች።

“በፍፁም ብቻዬን አልሄድም። ከአህቴ አሊያም ከልጄ ጋር ነው የምሄደው” ትላለች።

ለአብዛኛዎቹ የሜክሲኮ የድንበር ከተሞች የሕክምና ቱሪዝም በፍጥነት እያደገ የመጣ መስክ ሆኗል።

ከማታሞሮስ ጥቂት ሰዓታት ጉዞ ርቃ የምትገኘው ኑዌቫ ላሬዶ በርካታ የጥርስ ሕክምና ክሊኒኮች የሚገኙባት ስትሆን ለጎብኚዎች ተብሎ የተዘጋጁ ሆቴሎችም ተደርድረዋል።

ከሳን ዲዬጎ ድንበር የሦስት ደቂቃ የመኪና መንገድ ርቃ በምትገኘው ቲሁዋና ባለፈው ኅዳር 33 ፎቅ ያለው የሕክምና ጣቢያ ተከፍቷል።

ኒውሲቲ ሜዳካል ፕላዛ ተብሎ የተሰየመው ይህ ግዙፍ ሕንፃ፤ የውበት ቀዶ ሕክምናን ጨምሮ 30 ዓይነት ሕክምናዎችን ይሰጣል።

አልፎም ሆቴል እና የገበያ ማዕከል አካቷል።

ወንጀል፣ አፈና እና የሕዝብ ትራንስፖርት ላይ አደጋ ይደጋገማል በማለት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ዜጎች ወደ ታማውሊፓስ እንዳይጓዙ ይመክራል።

ሌሎች የሜክሲኮ የድንበር ከተሞችም ተመሳሳይ አደጋ ሊያጋጥም ይችላል በማለት መሥሪያ ቤቱ ያስጠነቅቃል።

ምንም እንኳ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለመሻገር የሚመጡ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ብዙ መከራ ቢገጥማቸውም፣ ለሕክምና ወደ ሜክሲኮ የሚሄዱ አሜሪካውያን ላይ የሚደርሰው አደጋ በቁጥር ትንሽ ነው።

“ይህ ያልተለመደ ጉዳይ ነው” የሚሉት ፕሮፌሰር ኔስተር ሮድሪጌዝ፣ “ነገር ግን የድንበር ከተማዎች ድኅንነት አስጊ እንደሆነ ማሳያ ነው። እኔ መሄድ አቁሚያለሁ” ይላሉ።