የ44 ቢሊዮን ዶላር የግዥ ስምምነትን ያፈረሱት ኤሎን መስክ በትዊተር ተከሰሱ

ኤሎን መስክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ግዙፉ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ትዊተር ከኤሎን መስክ ጋር ደርሶት የነበረው የሽያጭ ስምምነት ተፈጻሚ እንዲሆን ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወሰደ።

የዓለማችን ቁጥር አንድ ቱጃር ኤሎን መስክ ትዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት ስምምነት ደርሰው ነበር። ነገር ግን ባለፈው ሳምንት መስክ ስምምነቱን “አፍርሻለሁ” ብለዋል።

ይህንን ተከትሎ ትዊተር ግዥውን በሕግ አስገድዶ ለማስፈጸም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶታል።

መስክ ስምምነቱን ለማፍረስ በምክንያትነት የጠቀሱት ትዊተር ምን ያክል ሐሰተኛ ተጠቃሚዎች እንዳሉት በቂ መረጃ ሊሰጠኝ አልቻለም የሚል ነው።

ትዊተር ግን የተስማሙትን በአንድ የትዊተር የድርሻ ገበያ የሚከፈለውን 54̀.2 ዶላር መስክ እንዲፈጽሙ ፍርድ ቤትን ጠይቋል።

“ትዊተር ብዙ የሕዝብ መነጋገሪያ እንዲሆን በማድረግ የግዥ ፍላጎት አሳይተው እና ውልም ፈጽመዋል። ቢሆንም ግን መስክ ኩባንያውን ካከሰሩ፣ ሥራውን ካስተጓጎሉ፣ የባለድርሻዎችን ሃብት ዋጋ ቢስ ካደረጉ በኋላ ማንኛውም የውል ፈራሚ አካል ውሉን ለማቋረጥ ነጻ ነው ብለው ያምናሉ” ይላል ክሱ።

የትዊተር ሊቀ መንበር ብሬት ቴይለር “ኤሎን መስክ ለኮንትራት ግዴታቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ እናደርጋለን” በማለት ትዊተር ላይ አስፍረዋል።

የክሱ ይዘት እንደሚያሳየው መስክ ከስምምነቱ ያፈገፈጉት “ለግል ፍላጎታቸው ስምምነቱ ከዚህ በኋላ ስለማይጠቅማቸው ነው” ብሏል።

መስክ የቴስላ ኤሌክትሪክ መኪና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው።

በፎርብስ መጽሔት መረጃ መሠረት 273.6 ቢሊዮን የሚገመት የተጣራ ሃብት ያላቸው ኤሎን መስክ የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ ናቸው።

ይህም በዋነኝነት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራች በሆነው ቴስላ ውስጥ ባላቸው ድርሻ እና ስፔስ ኤክስ የተባለውን የህዋ በረራ ፕሮግራም ተቋም በኩል በሚያገኙት ገቢ ነው።

ትዊተር “በስምምነታችን መሠረት መስክ ግዥውን እንዲፈጽሙ እና የገባናቸውን ስምምነቶች እንዲያከብሩ በሕግ ለማስከበር ቁርጠኛ ነን” ብሏል።

መጀመሪያ ስምምነታቸው ላይ የውል ማፍረሻ 1 ቢሊዮን ዶላር ተቀምጦ ነበር።

መስክ ትዊተርን ሊገዙ ያቀረቡት ዋጋ አሁን ካለው ዋጋ ጋር ሲነጻጸር የተጋነነ ነው።

መስክ ስምምነቱን የጣሰው ትዊተር መሆኑን ማሳየት ይኖርባቸዋል። ይህንን ካላደረጉ ግን የዓለማችን ባለጸጋው ሰው የማይፈልጉትን ነገር እንዲገዙ የሚያስገድድ ክስ ገጥሟቸዋል።

ሌላም ነገር ሊከሰት ይችላል። ለምሳሌ መስክ ክሱን ሊያሸንፉ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ለትዊተር የከፋ ኪሳራ ያስከትላል።

ይህ ከመሆኑ በፊት ጉዳዩ በስምምነት እንዲቋጭ ትዊተር ጫና ሊያደርግ ይችላል። ምናልባትም መስክ ይህንን ተከትሎ ዋጋውን አሻሽለው አዲስ ዋጋ ሊያቀርቡ የይችላሉ።