የአሜሪካዋ ሞንታና ግዛት ቲክቶክን ግለሰቦች እንዳይጠቀሙ ልታገድ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካዋ ሞንታና ግዛት ነዋሪዎቿ በግል የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ቲክቶክን እንዳይጠቀሙ ለማገድ የተዘጋጀች ሲሆን ይህን እርምጃ የምትወስድ የመጀመሪያዋ የሀገሪቱ ግዛት ትሆናለች።
የግዛቲቱ ገዢ ግሬግ ጃንፎቴ ይህንን እገዳ የያዘው ህግ ላይ ትላንት ረቡዕ ፈርመዋል።
ይህ ህግ ከቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል።
እገዳውን ተከትሎ ቲክቶክ በሰጠው አስተያየት እርምጃው የሞንታና ነዋሪዎችን መሰራታዊ መብት የሚጥስ ነው ብሏል።
ቲክቶክ መረጃዎችን ለቻይና መንግሰት አሳልፎ ሊሰጥ ይችላል በሚል በተለያዩ ሀገራት ባለስልጣናት ከፍተኛ ክትትል እየተደረገበት ነው።
ሪፐብሊካን የሆኑት የሞንታና ገዢ ይህ ሰፊ እርምጃ ቅደሚያ የምንሰጠው የሞንታናን ደህንነት ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ስለላ ለመታደግ የሚደረገውን ጥረት ያጠናክራል ሲሉ ለህግ አውጪዎች ተናግረዋል።
ቲክቶክ ይህንን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ማህበራዊ ትስስር ገጹን በሞንታና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይጠቀሙታል ብሏል።
“በሞንታናም ይሁን ከዚያ ውጪ ያሉ የተጠቃሚዎቻችንን መብት ለማስጠበቅ እየሰራን ባለንበት በዚህ ሰዓት የሞንታና ነዋሪዎች ቲክቶከን በመጠቀም ራሳቸውን መግለጽ፣ ኑሯቸውን ለማሸነፍና ከህብረተሰብ ጋር ለመተሳሰር ቲክቶክ መጠቀማቸውን መቀጠል እንደሚችሉ ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን” ሲልም አክሏል።
ቲክቶክ ውሳኔውን ህጉን በመቃወም ወደ ፍርድ ቤት እንደሚያመራ ይጠበቃል።
ባለፈው ወር የሞንታና ምክር ቤት ቲክቶክ ከግለሰብ የቴክኖሎጂ ቁስ እንዲታገድ የሚጠይቀውን ረቂቅ ህግ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።
ህጉ የሞባይል መተግበሪያ ከሚገኙባቸው ድረገጾች ቲክቶከን መጫን ህገ ወጥ የሚያደርግ ቢሆንም ቀደም ብለው ጭነው እየተጠቀሙ ያሉ ሰዎችን አይመለከትም ብሏል።
ከ1 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ያሏት ሞንታና ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ ቲክቶክን መንግሥታዊ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ላይ ጥቅም ላይ እንዳይውል እገዳ ጥላለች።
ቲክቶክ በአሜሪካ 150 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች እንዳሉት ገልጿል። መተግበሪያ ከቅርብ አመታት ወዲህ በተላይ በአስራዎቹ እድሜ በሚገኙ ልጆች ዘንድ ያለው ተቀባይነት እየጨመረ መጥቷል።
ሆኖም ቲክቶክ የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት አደጋ ነው የሚል ስጋትም አለ።
ቲክቶክን በባለቤትነት የያዘው ባይትደናስ የተሸኘው የቻይና ተቋም ነው።
ከሁለት ወራት በፊት የቲክቶክ ዋና ስራ አስፈጻሚ በአሜረካ ኮንግረስ ቀርበው የቻይና መንግሥት መረጃን በቲክቶክ አማካኝነት መውሰድን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥዋል።
ኃላፊው በተደጋጋሚ ቲክቶክ አሜሪካን እንደማይሰልል ተናግረዋል።
ከዚያ ቀደም ብሎ የአሜሪካ መንግሥት ባይትዳንስ መሸጥ አለበት ያለ ሲሆን። ያ የማይሆን ከሆነ ግን ከሀገሪቱ ሊታገድ እንደሚችል አሰጠንቅቋል።
ከቀጣዩ የፈረንጆች አዲስ አመት ጀምሮ በሞንታና ቲክቶክን ከመተግበሪያዎች መጫኛ ማውረድ ቅጣት ያስከትላል።
የሚቀጡት ያወረዱት ግለሰቦች ሲሆን እንዲያወርዱ የሚፈቅዱት እንደ አፕስቶር ወይም ጉግል ፕለይ ያሉ ተቋማት ሲሆን 10 ሺህ ዶላር ይቀጣሉ።
ባይትዳንስ በተደጋጋሚ የቻይና መንግሥት እንደማይቆጣጠረው ይገልጻል።












